ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንቶኒዮ ኮንቴ ‘መባረር ፈልገዋል’ ያስባለው ንግግር እና የሃላንድ የጎል ናዳ
ጣሊያናዊው አሠልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ የቡድናቸውን ተጫዋቾች እና ባለቤቶች የወረፈ ንግግር አሰምተዋል።
ቶተንሃም በሳውዝአምፕተን ሜዳ 3 አቻ ከተለያየ በኋላ ተጫዋቾቼ “ራስ ወዳድ” ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል።
በቶተንሃም ውጤት ድርቅ እጅግ የተበሳጩት አሠልጣኙ “ቡድኑ አሠልጣኝ ቢቀይርም ለውጥ አያመጣም” ብለዋል።
“ይህ የቶተንሃም ታሪክ ነው - 20 ዓመት ሙሉ አንድ ባለቤት ነው ያለው፤ ነገር ግን አንድም ዋንጫ በልቶ አያውቅም። ለምን?”
በሳውዝአምፕተን ስታድየም በሁለት ጎል ልዩነት እየመራ የነበረው ቶተንሃም በ15 ደቂቃ ውስጥ ሁለት ግቦችን አስተናግዶ 3 አቻ ወጥቷል።
“እና ጥፋቱ የክለቡ ብቻ አሊያም ቶተንሃምን ያሠጠኑ ግለሰቦች ነው?” ሲሉ ኮንቴ ጠይቀዋል።
“እስካሁን ድረስ ያለውን ነገር መደበቅ እፈልግ ነበር። አሁን ግን በቃኝ። እደግመዋለሁ፤ ዛሬ ያየሁትን ነገር ማየት አልፈልግም፤ ምክንያቱም በደጋፊዎቻችን ዘንድ ተቀባይነት የለውም።”
በዳንኤል ሌቪ የሚመራው አስተዳደር ቶተንሃምን በፈረንጆቹ 2001 ከተረከበ ጀምሮ ቡድኑ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሊግ ዋንጫን ያነሳው።
በሌቪ አስተዳደር ዘመን 11 አሠልጣኞችን የቀያየረው ቶተንሃም ከማውሪሲዮ ፖቸቲኖ በኋላ ሦስት አሠልጣኞችን አምጥቷል።
ፖቸቲኖ ቶተንሃምን ለአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ማብቃታቸው ይታወሳል።
በሸፊልድ ዩናይትድ ከኤፍ ኤ ዋንጫ፤ ከቻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ በኤሲ ሚላን የተሰናበቱት ቶተንሃሞች በዘንድሮው የውድድር ዘመን እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዞ ከማጠናቀቅ ውጭ ሌላ ተስፋ የላቸውም።
ኮንቴ እንደሚሉት ቡድኑ እና ተጫዋቾች ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል።
“አስተዳደሩ እና ሌሎች ሠራተኞች ሊሳተፉ ይገባል። ተጫዋቾችም መሳተፍ አለባቸው። ቡድኑ መቀየር ከፈለገ ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል።
“እንደዚህ መቀጠል ከፈለጉ አሠልጣኝ መቀየር ይችላሉ። ያሻቸውን ያክል አሠልጣኝ ቢቀያይሩ ለውጥ አይመጣም።”
ቶተንሃም እንዲህ የሆነው ለምን ይሆን ተብለው የተጠየቁት ኮንቴ ቡድኑ ውስጥ ያለውን ልማድ ወርፈዋል።
“ምክንያቱም ተለምዷል። ለትልቅ ነገር መጫወት አልለመዱም። በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መጫወት አልለመዱም። 11 ተጫዋቾች ለራሳቸው ነው የሚጫወቱት።”
ቶተንሃም ሆትስፐርስ የቅዳሜውን ግጥሚያ በድል ቢወጣ ከዩናይትድ በላይ ሆኖ በሊጉ ሦስተኛ ደረጃን ይቆናጠጥ ነበር።
የአሠልጣኙን አስተያየት ተከትሎ በርካታ የስፖርት ተንታኞች ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።
ብዙዎች አሠልጣኙ “መባረር ስለፈገሉ ነው ይህን አይነት ግልብ አስተያየት የሰጡት” ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።
የሃላንድ የጎል ናዳ
በኤፍ ኤ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ በሜዳው በርንሊን ያስተናገደው ማንቸስተር ሲቲ የጎል ናዳ አውርዷል።
ሲቲ ጨዋታውን 6 ለ 0 ሲያሸንፍ አጥቂው ኧርሊንግ ሃላንድ 3 ግቦችን አስቆጥሯል።
ሃላንድ ባለፈው ማክሰኞች በቻምፒየንስ ሊግ ፍልሚያ አርቢ ሊፕዚክ ላይ አምስት ግቦችን ማስቆጠሩ የሚታወስ ነው።
በአንድ ውድድር ዘመን በርካታ ጎሎች ለቡድናቸው በማስቆጠር ክብረ ወሰኑን የያዙት ሩድ ቫን ኒስትልሮይ እና ሞሐመድ ሳላህ ናቸው።
እስካሁን 42 ጎሎች ያስቆጠረው ሃላንድ ከዚህ በኋላ 2 ግቦችን ካስቆጠረ ክብረ ወሰኑን ይሰብራል።
ሃላንድ ወደ እንግሊዙ ክለብ ከመጣ በኋላ ስድስት ጊዜ ‘ሃት-ሪክ’ መሥራት ችሏል።
ለማንቸስተር ሲቲ ለዓመታት የተጫወተው አርጀንቲናዊ ኮከብ ሰርጂዮ አጉዌሮ በ10 ዓመት ቆይታው 12 ጊዜ ‘ሃት-ሪክ’ ሠርቷል።
በቻምፒዮንስ ሊግ፣ ፕሪሚዬር ሊግ እና ኤፍ ኤ ዋንጫ እየተፋለሙ የሚገኙት ሲቲዎች የውድድር ዘመኑ እስኪጠናቀቅ ድረስ በርካታ ጨዋታዎች ይጠብቋቸዋል።
ሃላንድ በዚህ አቋሙ ከቀጠለ በውድድር ዘመኑ መገባደጃ ከ60 በላይ ግቦች ሊያስቆጥር ይችላል።
ፕሪሚዬር ሊግ
በአርብ ምሽት የፕሪሚዬር ሊግ ግጥሚያ ኒውካስትል ዩናይትድ ከሜዳው ውጭ ተጉዞ ሦስት ነጥብ ይዞ ተመልሷል።
ኒውካስትል በትውልደ ኤርትራዊው ስዊድናዊ አሌክሳንደር አይዛክ ሁለት ጎሎች፣ ኖቲንግሃም ፎረስትን 2 ለ 1 ረትቷል።
ቅዳሜ በነበሩ ሌሎች የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች አስተን ቪላ ቦርንመዝን 3 ለ 0 ሲረታ ብሬንትፈርድ ከሌይስ 1 አቻ ተለያይቷል።
ዎልቭስ በሜዳው በሊድስ ዩናይትድ 4 ለ 2 ሲያሸንፍ፣ ቶተንሃም ከሜዳው ውጭ ከሳውዘአምፕተን 3 አቻ ጨርሷል።
ምሽት ላይ በነበረው የቅዳሜ የመጨረሻው ፍልሚያ ቼልሲ በሜዳው ከኤቨርተን ገጥሞ ጨዋታው ሊገባደድ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት በተቆጠረበት ጎል ነጥብ ተጋርቷል።
እስከ 89ኛው ደቂቃ ድረስ ግጥሚያው በቼልሲ 2 ለ 1 መሪነት ቢቆይም ወጣቱ የኤቨርተን አጥቂ ሲምስ ባስቆጠራት ጎል አቻ ተጠናቋል።
እሑድ ከሰዓት 11፡00 በፕሪሚዬር ሊጉ አርሰናል ከክሪስታል ፓላስ ይጋጠማሉ።
በኤፍ ኤ ዋንጫ ደግሞ ምሽት 1፡30 ማንቸስተር ዩናይትድ ከፉልሃም ይፋለማል።