ሃላንድ በአንድ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ 5 ጎሎችን አስቆጥሮ አዲስ ታሪክ ጻፈ

ኤሪክ ሃላንድ ቡድኑ በፍጹም የበላይነት የጀርመኑን ክለብ 7ለ0 በሆነ ውጤት ባሸነፈበት ጨዋታ አዲስ ታሪክ ጻፈ።

ሃላንድ በአንድ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ አምስት ጎሎችን ያስቆጠረ ወጣት ተጫዋች ሆኗል።

ሃላንድ በአንድ ጨዋታ አምስት ጎሎችን በማስቆጠር ከሊዮኔል ሜሲ እና ብራዚላዊው አጥቂ ሉዊዝ አድሪያኖ ጋር ሪከርድ ተጋርቷል።

ይህም ብቻ አይደለም ሃላንድ በአውሮፓ ከፍተኛ ሊጎች በለጋ እድሜ በፍጥነት 30 ጎሎችን ያስቆጠራ ተጫዋች ሆኗል።

የ22 ዓመቱ ኖርዌያዊው ተጫዋች በዚህ የውድድር ዘመን ለማንችስተር ሲቲ በሁሉም ጨዋታዎች ያስቆጠራቸውን ግቦች 39 ያደረሰ ሲሆን፤ ይህም በክለቡ ታሪክ በአንድ የውድድር ዘመን ከፍተኛ ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች አድርጎታል።

ሲቲ 7ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ ኢልካይ ጉንዶዋን እና ኬቪን ዲ ብሮይና ቀሪዎቹን ሁለቱን ጎሎች ለሲቲ አስቆጥረው ክለቡን ወደ ሩብ ፍጻሜ አሸጋግረዋል።

ሃላንድ ሦስቱን ጎሎች በመጀመሪያው አጋማሽ አስቆጥሮ ገና በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ‘ሃትሪክ’ የሰራ ሲሆን ቀሪዎቹን ሁለቱን ጎሎች ደግሞ በ53ኛው እና 57ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል።

ትናንት ምሽት በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ ፖርቶ እና ኢንተር ያለ ጎል 0ለ0 የተለያዩ ሲሆን በድምር ውጤት ኢንተር 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

ከሳምንት በፊት የደርሶ መልስ ጨዋታቸውን ያጠናቀቁት ባየር ሙኒክ፣ ቤኔፊካ፣ ቼልሲ እና ሚላን ተጋጣሚዎቻቸውን ረትተው ወደ ቀጣይ ዙር ያለፉ ቡድኖች ሆነዋል።

ዛሬ 8 ቡድኖችን ወደሚያሳትፈው ዙር ለማለፍ አራት ቡድኖች ተፋጠው ይገኛሉ። ናፖሊ የ2ለ0 ውጤትን ይዞ ፍራንክፈርትን በሜዳው ያስተናግዳል።

በአንፊልድ በደጋፊው ፊት 5 ለ 2 የተረታው ሊቨርፑል ደግሞ ወደ ሪያል ማድሪድ ያቀናል።

የቻምፒየንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ድልድል እጣ አወጣጥ የፊታችን አረብ ይደረጋል።