የዳጋሎ ኃይል የአገሪቱን ጦር ኃይል ከሱዳን ሁለተኛ ትልቋ ከተማ ማስወጣቱ ተገለጸ

ኛላ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኛላ ከተማ

በጀነራል ሔሜቲ ዳጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የአገሪቱን ጦር ኃይል ከሱዳን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ማስወጣቱ ተገለጸ።

የኛላ ከተማ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት ከወራት ውጊያ በኋላ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሠራዊት የደቡብ ዳርፉር ዋና መዲና ወደሆነችው ኛላ ከተማ ገብተዋል።

ነዋሪዎችም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወደከተማዋ መግባት ለወራት የዘለቀው ግጭት ማብቂያ ሊሆን ይችላል በሚል ተስፋ ደስታቸውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ መውጣታቸውን አንድ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ግጭቱ በዚህች ከተማ ብቻ ከ670 ሺህ በላይ ሰዎችን ያፈናቀለ ሲሆን መሠረተ ልማቶችን አውድሟል።

በከተማዋ የሚገኙ ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን አሁን ላይ የሰዎች አስክሬን በየመንገዱ ወድቆ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ኛላ ከተማን ከአገሪቱ ጦር ነጥቆ የመቆጣጠሩ ዜና የተሰማው ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች በሳዑዲ አረቢያ የሰላም ንግግር ያደርጋሉ በተባለበት ወቅት ነው።

ከስድስት ወራት በላይ በሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን የሚመራው ሠራዊትና እና በጀነራል ሃምዳን ደጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ውጊያ እየተካሄደ ነው።

እስካሁን ድረስ በዚህ ግጭት ከ7ሺህ በላይ ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ መፈናቀላቸው ተገልጿል።

በጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የአገሪቱ ጦር እስካሁን ድረስ ኛላ ከተማን በተመለከተ ያለው ነገር የለም።

የደቡብ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው ኛላ ከተማ ሱዳንን ከመካከለኛዋ አፍሪካ ሪፓብሊክ ጋር የምታገናኝ ቁልፍ ከተማ ናት።

የጀነራል ሃምዳን ደጋሎ ወንድም እንደሆነ የሚገለጸው እና የፈጥኖ ደራሹ ምክትል መሪ የሆነው አብዱልራሂም ዳጋሎ ኛላ ከተማን ለመያዝ የተደረገውን ኦፕሬሽን ስለመምራቱ ተገልጿል።

ይህ ግለሰብ በምዕራብ ዳርፉር በሰላማዊ ዜጎች ላይ በተፈጸመው የዘር ማጽዳት ወንጀል በአሜሪካ መንግሥት ማዕቀብ ተጥሎበት ይገኛል።

የዓይን እማኞች እንደሚሉት የሔምቲ ኃይሎች ኛላ ከተማን ከያዙ በኋላ የነዋሪዎችን ቤት ሰብረው እየገቡ ዘረፋ እየፈጸሙ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሱዳንን ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ ጋር የምታወስነውን ኡም-ዳፎግ የተባለች አነስተኛ ከተማን መያዛቸው ግብዓት ከውጭ ለማስገባት ትልቅ አስተዋጽኦ ስለማበርከቱ ይገለጻል።

የተባባሩት አረብ ኤሜሬቶች ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በቻድ እና በመካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ በኩል የጦር መሳሪያ ድጋፍ እያደረገች ነው በሚል ትወቀሳለች።

አቡ ዳቢ ግን ይህን አስተባብላለች።