አሜሪካ የሱዳን የሲቪሎች ልዑክ በአዲስ አበባ ያደረጉትን ውይይት እደግፋለሁ አለች

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
በጦርነት ውስጥ ያለችው ሱዳን የሲቪሎች የልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ ያደረጉትን ውይይት የአሜሪካ መንግሥት እንደሚደግፈው ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ድረ ገጽ ላይ ትላንት ሐሙስ ጥቅምት 15፣ 2016 ዓ. ም. የወጣው መግለጫ እንደሚጠቁመው፣ የሱዳን ሲቪሎችና ባለድርሻ አካላት በአዲስ አበባ ያደረጉት ውይይት በአዎንታዊ ይመለከተዋል።
ይህንን ውይይት ተከትሎ ዴሞክራሲን የሚያቀነቅን የሲቪሎች ግንባር ይመሠረታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።
የልዑካኑን ውይይት የዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ እና ኖርዌይ መንግሥታት ጥምረት እንደሚደግፈውም ተመልክቷል።
የሲቪሎች ልዑካኑ በአዲስ አበባ ውይይት የማድረጉ ዜና የተሰማው ተዋጊዎቹ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በማቅናት የሰላም ውይይት እንደሚያደርጉ በተገለጸበት ወቅት ነው።
ከስድስት ወራት በላይ በቀጠለው ጦርነት በሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን የሚመራው ሠራዊትና እና በጀነራል ሃምዳን ደጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ውጊያ እየተካሄደ ነው።
ሁለቱ ተዋጊዎች ከሰሞኑ በሳዑዲ አረቢያ የወደብ ከተማ ጅዳ የሰላም ውይይት እንደሚያካሂዱ ተዘግቧል።
በአውሮፓውያኑ 2019 ሁለቱ መሪዎች ተባብረው መፈንቅለ መንግሥት አውጀው ኦማር ሐሰን አል-በሽርን ከሥልጣን ቢያወርዱም በመካከላቸው የተፈጠረው ሽኩቻ ጦር እንዲማዘዙ አድርጓቸዋል።
እስካሁን ድረስ ከ7ሺህ በላይ ሰላማዊ ሰዎችን የተገደሉ ሲሆን ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ መፈናቀላቸው ተገልጿል።
የሱዳን የሲቪሎች ልዑክ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ውይይት ለማካሄድ መወሰናቸው አገሪቱ ዴሞክራሲ እንዲፍንባት ሕዝቡ ያለውን ፍላጎት እንደሚያሳይ የአሜሪካ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
“ጦርነቱ ተፋፍሞ በቀጠለበት በዚህ ወቅት በሁለቱም ወገኖች በኩል ያሉ እንዲሁም ከሱዳን ውጭ የሚኖሩም ሲቪሎች፣ በታሪክ የተገለሉ ቡድኖችና አካባቢዎች ተወካዮች፣ የትግል ቡድኖች፣ የሠራተኞች ማኅበራት፣ ሙያዊ ማኅበራት፣ ሲቪል ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ብሔራዊ ገለልተኛ አካላት አንድ ላይ ተሰባስበው የመጀመሪያ ውይይታቸውን ማድረጋቸውን” እንደግፋለን ብሏል።
ውይይቱ የጋራ አቋም በመያዝ በስፋት ሌሎችን አካላትን አሳትፎ በቀጣይ ወራት ይቀጥላል ተብሎ እንደሚታመንም ተገልጿል።
ሱዳናውያን ሲቪሎች በሱዳን እንዲሁም በቀጠናው ተሰባስበው ስለ ፖለቲካዊ እጣ ፈንታቸው መወያየት ቀጥለዋል።
የአሜሪካ፣ ዩኬ እና ኖርዌይ ጥምረት፣ የአዲስ አበባው ውይይት የጋራ ዴሞክራሲን የሚያቀነቅን ግንባር ይፈጥራል ብሎ እንደሚያምን ተገልጿል።
“በውይይቱ ስለ ሽግግርና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ተነስቶ ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ይጠቅማል” ሲል መግለጫው አትቷል።
ተዋጊዎቹ ቡድኖች ግጭት አቁመው በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስፈልገው ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ መንገድ እንደሚከፈት እንዲሁም የሽግግር የሲቪል አስተዳደር እንዲመሠረት ይህ ውይይት አስተዋዕኦ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል።
አሜሪካ፣ ዩኬ እና ኖርዌይ በሱዳን ሰፊ የገንዘብ ልገሳ በማድረግ የሚታወቁ ሲሆን፣ አሁንም በሱዳን ጦርነት እንዲቆምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን መሥራት እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።












