ጋዛ ውስጥ ከባድ “የዘር ማጥፋት” አደጋ መደቀኑን የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሙያዎች ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሰባት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወከሉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ጋዛ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ከባድ “የዘር ማጥፋት” አደጋ እንደተጋረጠባቸው እንደሚያምኑ እና ይህንንም ለማስቆም ጊዜው እያበቃ መሆኑን አመልክተዋል።
እስራኤል ግን ጋዛ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሙያዎች አስተያየት የሐማስን ፕሮፓጋንዳ የሚደግም ነው በማለት “ሊወገዝ” የሚገባ ነው ስትል ተቃውሞዋን ገልጻለች።
የባለሙያዎቹ ልዩ ቡድን እንዳለው እስራኤል የጋዛ ሰርጥን ለማውደም ዕቅድ ማውጣቷን በመጥቀስ፣ እስራኤል እና አጋሮቿ በአስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እንዲስማሙ እንዲሁም ሐማስ እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች በአስቸኳይ ያገቷቸውን ሰላማዊ ሰዎች እንዲለቁ ጥሪ አቅርበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ኮሚሽነር ባወጣው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ባለሙያዎቹ “በጋዛ ያለው ሁኔታ ከባድ መቅሰፍትን ከሚያስከትል ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል” ብለዋል።
ይህንን የባለሙያዎች አስተያየትን በተመለከተ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ቃል አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ የዘር ማጥፋትን በተመለከተ ውሳኔ የሚሰጠው የተመድ የሕግ አካል ብቻ መሆኑን መናገራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የባለሙያዎች ቡድን የሰነዘረባትን ክስ አጥብቃ የተቃወመችው እስራኤል በበኩሏ፣ ሐማስ ሰላማዊ ሰዎችን በሰብአዊ ጋሻነት እንደሚጠቀም እና የሚቀርቡ ዕርዳታዎችን ለሽብር ተልዕኮዎች እያዋለ ነው ብላለች።
“እየተካሄደ ያለው ጦርነት በሐማስ ሽብርተኛ ቡድን አማካይነት መስከረም 26 በተፈጸመ ጭፍጨፋ፣ 1,400 ሰዎችን በማረድ እና 243 ሕጻናት፣ ወንዶች እና ሴቶችን በማገት በእስራኤል ላይ የተከፈተ ነው” በጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእስራኤል መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት ገልጿል።
የሐማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል አራት ሳምንት ሊሞላው የተቃረበ ቀን ከሌት ያልተቋረጠ የአየር ድብደባ በጋዛ ላይ እየፈጸመች ሲሆን፣ አስካሁን ከ9 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ አብዛኞቹ ሕጻናት እና ሴቶች ናቸው ተብሏል።
እስራኤል ጦርነቱን እያካሄደች ያለችው ሐማስን በማጥፋት የታገቱ ዜጎቿን ለማስለቀቅ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጻ፣ ካለፈው ሳምንት ማብቂያ አንስታ እግረኛ ሠራዊቷን ወደ ጋዛ በማሰማራት ዘመቻ እያካሄደች ነው።
በሐማስ ታግተው ወደ ጋዛ የተወሰዱት ሰዎች በጋዛ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ስፍራዎች እና ዋሻዎች ውስጥ እንደደበቃቸው ቡድኑ ገልጿል።
ማረጋገጥ ባይቻልም ሐማስ ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀው እስራኤል እያካሄደችው ባለው የአየር ጥቃት ምክንያት ከታጋቾቹ መካከል ቢያንስ 50ዎቹ ተገድለዋል ብሏል።
ትናንት ሐሙስ ቡድኑ እንዳስታወቀው ደግሞ ከጥቂት ቀናት በፊት እስራኤል ጃባሊያ በተባለው የስደተኞች ካምፕ ውስጥ በፈጸመችው ሌላ ጥቃት ሰባት ታጋቾች ተገድለዋል ብሏል።












