ናፖሊ ራሽፈርድን ለማስፈረም ቆርጧል፤ አሌክሳንደር ኢሳክ ወደ ባርሴሎና ሊያቀና ይችላል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ራሽፈርድ ወደ ናፖሊ፤ አሌክሳንደር ኢሳክ ወደ ባርሴሎና፤ ኽቪቻ ክቫራትሽኼሊያ ደግሞ ወደ ፒኤስጂ የሰሞኑ የዝውውር ጭምጭምታዎች ናቸው።
የጣሊያኑ ክለብ ናፖሊ የማንቸስተር ዩናይትዱን የፊት መስመር ተጫዋቹን ማርከስ ራሽፈርድ ለማስፈረም አቅዷል ሲል የዘገበው ሚረር ነው።
በሚረር ዘገባ መሠረት ናፖሊ ጆርጂያዊውን የመስመር ተጫዋች ክቫራትሽኼሊያን ለፓሪ ሳን ዠርማ በመሸጥ የ27 ዓመቱን እንግሊዛዊ ለማስፈረም አስቧል።
የፈረንሳዩ ኃያል ክለብ ለፓሪ ሳን ዠርማ ኽቪቻን ለማስረም ከጫፍ መድረሱን ፉት መርካቶ አስነብቧል። እንደ ዘገባው ከሆነ የ23 ዓመቱ ክቪቻ ከፒኤስጂ ጋር ተስማምቷል።
ፒኤስጂ በተጨማሪ የአስተን ቪላውን አጥቂ ጆን ዱራን ለማስፈረም አስበዋል።
ስፔናዊው የአጥቂ አማካይ ማርኮ አሴንሲዮ ወደ አስተን ቪላ ሊያቀና እንደሚችል ፉት መርካቶ ዘግቧል። ጁቬንቱስ እና ሪያል ሶሲየዳድም ተጫዋቹን ለማስፈረም ከሚሹ መካከል ናቸው።
ባርሴሎና ኤርትራዊ ስዊድናዊው የኒውካስል አጥቂን ለማስፈረም እንደሚሻ ሙንዶ ዲፖርቲቮ ፅፏል።
የ25 ዓመቱ አሌክሳንደር ኢሳክ ወደ ስፔን ያቀናል የሚለው እርግጥ አይደለም። ነገር ግን ባርሴሎና በያዝነው የጥር የዝውውር መስኮት አሊያም በመጪው ክረምታ ሊያዘዋውሩት እንደሚሹ ታውቋል።
በጋርዲያን ዘገባ መሠረት ኤሲ ሚላን እንግሊዛዊውን የማንቸስተር ሲቲ ተከላካይ ካይል ዎከርን ለማስፈረም ፍላጎት አሳይተዋል። የሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ የ34 ዓመቱ ተከላካይ ክለቡን መልቀቅ ይፈልጋል ማለታቸው ይታወቃል።
ባለፈው የክረምት የዝውውር መስኮት በርካታ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ቼልሲ የክሪስታል ፓላሱን ተከላካይ ማርክ ጉዌሂን ለማስፈም አይቻለውም ሲል የዘገበው ሚረር ነው። ክለቡ ባለው ጥብቅ የደመወዝ አከፋፈል ሳቢያ ተጫዋቹን ሊያጣው እንደሚችል ተነግሯል።
የኢንትራክት ፍራንክፈርቱ ግብፃዊ ኦማር ማርሙሽ ወደ ማንቸስተር ሲቲ ሊያቀና እንደሚችል ዘገባዎች ጠቁመዋል። ስካይ ስፖርት ጀርመኒ እንደዘገበው ተጫዋቹ ከሲቲ ጋር ተስማምቷል።
የባርሴሎናው ተከላካይ ሮናልድ አራውሆ ወደ ጁቬንቱስ፤ የቼልሲው ቹኩዌሜካ ወደ ቦርሲያ ዶርትመንድ ሌሎች የዝውውር ጭምጭምታዎች ናቸው።












