ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አይኤስ በኢትዮጵያ በተመዘገቡት አውሮፕላኖች ላይ ጉዳት ያደረሰበት ጥቃት ምን ነበር?
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ኒጀር ዋና ከተማ አየር ማረፊያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት "በኢትዮጵያ አቪዬሽን ባለሥልጣን የተመዘገቡ" ሁለት አውሮፕላኖች "መጠነኛ ጉዳት" እንደደረሰባቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገለጸ። ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት ቦይንግ 737 አውሮፕላኖች 'አስካይ' የተባለው አየር መንገድ "በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት" የተከራያቸው እንደሆኑም አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰኞ ጥር 25/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የጠቀሰው በአየር ማሪፊያ ላይ ደረሰ ጥቃት የደረሰው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ጥር 21 ሌሊት ነበር።
ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ከኒጀር ዋና ከተማ ኒያሚ ወጣ ብሎ በሚገኘው 'ዲኦሪ ሃማኒ' ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ የተፈጸመውን "ድንገተኛ ጥቃት ማቀነባበሩን" በመግለጽ ኃላፊነት ወስዷል።
የኮትዲቯር አየር መንገድ በአየር ማረፊያው ላይ በደረሰው ጥቃት አንድ ኤርባስ ኤ319 አውሮፕላኑ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት አስታውቋል። የአውሮፕላኑ ዋነኛ አካል እና የቀኝ ክንፉ መጎዳቱንም ገልጿል።
በዚህ ጥቃት ጉዳት ያስተናገደው ሌላኛው አየር ትራንስፖርት አቅራቢ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ የያዘበት 'አስካይ' ነው።
ዋና መቀመጫውን ቶጎ ውስጥ ያደረገው አስካይ፤ ራሱን 'ፓን አፍሪካዊ' አየር መንገድ ብሎ የሚገልጽ ሲሆን፣ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት ይበርራል። የአስካይ "ቴክኒካል እና ስትራቴጂክ አጋር" የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የካፒታል ወጪ በማድረግ ተሳትፎ አለው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2001 ዓ.ም. የተመሠረተው አስካይ አየር መንገድን የ25 በመቶ ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹን አምስት ዓመታም አስተዳድሮታል። በአሁኑ ሰዓት የአስካይ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤልያስ ወልደማርያም ናቸው።
አስካይ አየር መንገድ ጥቃቱ በደረሰ ማግስት ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ ከምሽት እስከ ንጋት የቆየ "የደኅንነት ችግር መከሰቱን" አረጋግጧል። በኒጀሩ አየር ማረፊያ ላይ በደረሰው ጥቃት "ቆመው በነበሩ ሁለት የአስካይ አውሮፕላኖች ላይ መጠነኛ ጉዳት" መድረሱንም ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰኞ ባወጣው መግለጫ ጉዳት የደረሰባቸው ቦይንግ 737 አውሮፕላኖች እንደሆኑ አስታውቋል።
ጉዳት ደረሰባቸው አውሮፕላኖች "የአስካይ አየር መንገድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት ከአውሮፕላን አከራዮች የተከራያቸው" እንደሆኑም አስታውቋል። "በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የተመዘገቡ" እንደሆኑም አክሏል።
በአውሮፕላኖቹ ላይ ደረሰውን ጉዳት ለመገምገም የቴክኒክ ቡድን ወደ ስፍራው መላኩን የገለጸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ቡድኑ "ጉዳቱ መጠነኛ መሆኑን" እንዳረጋገጠ አስታውቋል። "አውሮፕላኖቹ ተጠግነው በቅርቡ ወደ አገልግሎት እንደሚገቡ ለማሳወቅ እንወዳለን" ብሏል።
ጥቃቱን የሚያሳየው የአይኤስ ቪዲዮ
በአየር ማረፊያው ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ አራት ወታደሮች እንደተጎዱ እና 20 ጥቃት አድራሾች እንደተገደሉ የኒጀር መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል። ከተገደሉት መካከል አንድ ፈረንሳይ ዜግነት ያለው እንደሆነም ገልጿል።
በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣኑን የተቆጣጠረው የኒጀር ጁንታ፤ በአየር ማረፊያው ጥቃት ያደረሱትን ኃይሎች ይደግፋሉ ሲል የፈረንሳይ፣ የቤኒን እና የአይቮሪኮስት ፕሬዝዳንቶችን ከስሷል። በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት ለማክሸፍ እገዛ አድርጋለች ላላት ሩሲያ ደግሞ ምስጋና አቅርቧል።
ለክስተቱ ኃላፊነት የወሰደው ኢስላሚክ ስቴት በበኩሉ፤ ጥቃቱ ጥር መጀመሪያ ላይ እንዲፈጸም ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በደኅንነት ምክንያቶች የተነሳ ተራዝሞ መቆየቱን እንደገለጸ ቢቢሲ ሞኒተሪንግ ዘግቧል። ቡድኑ አባላቱ ጥቃቱን ሲፈጽሙ የሚያሳይ የአንድ ደቂቃ ከ37 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ቪዲዮ እሁድ ዕለት በቴሌግራም ገጹ ለቅቋል።
ቪዲዮ ላይ በርካታ ታጣቂዎች የሚታዩ ሲሆን፣ አብዛኞቹም ሞተር ሳይክል እየነዱ ይታያሉ። ታጣቂዎቹ ምሽት ላይ የአየር ኃይል ካምፕ የሚመስል ቦታ ሲያጠቁ እና ጋራዥ ውስጥ የቆሙ ቢያንስ ሦስት አውሮፕላኖችን ሲያቃጥሉ ያሳያል። ሲቃጠሉ የሚታዩት ሁለት ቀላል አውሮፕላኖች፤ አንድ ደግሞ ሄሊኮፕተር እንደሆኑ ተገምቷል።
ቪዲዮው ላይ ታጣቂዎቹ አንድም የሚታይ ተቃውሞ ሳይገጥማቸው በነፃነት ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ። በአንዱ የቪዲዮው ክፍል ላይ ታጣቂዎቹ ሦስት ትላልቅ የንግድ የመንገደኞች አውሮፕላኖች አጠገብ የሚገኝ የአውሮፕላን ማኮብኮቢያ መንገድ ላይ ያለምንም እንቅፋት ሲጓዙ ታይተዋል።
ቪዲዮው ላይ የተኩስ ድምፅ የሚሰማ ቢሆንም በንግድ አውሮፕላኖቹ ላይ የደረሰው ጉዳት በግልጽ አይታይም።
በአንዱ ቪዲዮ ውስጥ አንድ ታጣቂ "እነዚህ ከፈጣሪ ይልቅ የምታመልኳቸው አውሮፕላኖች ናቸው" እያለ ሲጮህ፤ ከዚያም በጋራዥ ውስጥ ባለ አንድ ትንሽ አውሮፕላን ላይ ሲተኩስ ይታያል። በሌላ ቀረጻ ላይ ደግሞ ታጣቂዎች በአንድ ሄሊኮፕተር ላይ አርፒጂ (RPG) ሲተኩሱ እና ተኩሱ ከፍተኛ ፍንዳታ ሲያስከትል ይታያል።
ወታደራዊ የሆኑ የኦፕን ሶስር መረጃዎችን የሚከታተል አንድ ድረ ገጽ በቪዲዮው ላይ ሲቃጠሉ የሚታዩት የአሜሪካ እና የኦስትሪያ ወታደራዊ አውሮፕላኖች እንዲሁም ሩሲያ ሠራሽ ወታደራዊ ሄሊኮፕተር እንደሆኑ ገልጿል። ተኩስ ቢከፈትበትም ከፍተኛ ጉዳት ያልደረሰበት ደግሞ ቱርክ ሠራሽ የውጊያ አውሮፕላን እንደሆነ ዘግቧል።
በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ ኒጀር ከቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ያላትን ወታደራዊ ግንኙነት ያቋረጠው የአገሪቱ ወታደራዊ መንግሥት፤ በቀጣናው የሚንቀሳቀሱትን ኢስላማዊ ታጣቂዎችን ለመዋጋት ፊቱን ወደ ሩሲያ አዙሯል።
የኒጀር መከላከያ ሚኒስትር ሳሊፉ ሞዲ በሰጡት መግለጫ፤ ቅጥረኞ ወታደሮች በመዲናዋ በሚገኝ የአየር ኃይል ካምፕ ላይ ለ30 ደቂቃ ያህል ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ "በአየር እና በምድር" የአጸፋ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተናግረዋል።