እስራኤል ስለ ዌስት ባንክ ያስተላለፈችው አዲስ ውሳኔ መሬቱን የመጠቅለል እርምጃ ነው ሲሉ ፍልስጤማውያን ተቃወሙ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የእስራኤል ደኅንነት ካቢኔ ዌስት ባንክን በተመለከተ ያስተላለፈው አዲስ ውሳኔ አካባቢውን በእጅ አዙር የመጠቅለል እርምጃ ነው ሲሉ ፍልስጤማውያን ተቃውሟቸው አሰሙ።

የእስራኤል ውሳኔ በግዳጅ ይዞታ ውስጥ ያለውን ዌስት ባንክን በቁጥጥር ሥር ከማዋል የማይተናነስ ነው ብለው ከተቃወሙ መካከል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አንዱ መሆናቸውን የሮይተርስ ዘገባ ይጠቁማል።

ከፍተኛ የዋይት ሀውስ ባለሥልጣንን ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ ትራምፕ እስራኤል ዌስት ባንክን በቁጥጥሯ ሥር እንድታውል አይፈልጉም።

"ዌስት ባንክ የተረጋጋች ስትሆን እስራኤልም ደኅንነቷ ይጠበቃል። የዚህ አስተዳደር ግብ ደግሞ በቀጣናው ሰላም ማስፈን ነው" ሲሉ ባለሥልጣኑ መናገራቸው ተገልጿል።

የደኅንነት ካቢኔውን ውሳኔ የአረብ አገራት፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና የግዳጅ ይዞታን የሚቃወሙ እስራኤላውያን ቡድኖች ተቃውመዋል።

ቀኝ ዘመሙ የእስራኤል የፋይናንስ ሚኒስትር በዘላል ስሞትሪች ይፋ ያደረጉት ውሳኔ ተስፋፊ አይሁዶች የፍልስጤምን መሬት እንዲነጥቁ ያስችላቸዋል።

"የፍልስጤም አገርነትን መቅጨታችንን እንቀጥላለን" ብለዋል ሚኒስትሩ።

የተባበሩት መንግሥታት እንደገለጸው፤ በዌስት ባንክ ያለው እንቅስቃሴ መመዝገብ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአካባቢው ከተካሄደው ሰፈራ ሁሉ ባለፈው ዓመት የተከናወነው ይበልጣል።

የእስራኤል አዲስ ውሳኔ በዌስት ባንክ ለአይሁዳውያን በቀጥታ መሬት መሸጥን የሚከለክለውን ድንጋጌ ይቀለብሳል።

ባለፉት ዓመታት የዌስት ባንክ ሰፋሪዎች መሬት ይገዙ የነበረው በእስራኤል መንግሥት ቁጥጥር ከሚደረግባቸው ተቋማት ነበር።

የእስራኤል ሚኒስትሮች አዲሱን አሠራር ያስተዋወቁት "ግልጽነትን የሚያበረታታ እና የመሬት ይዞታን ነጻ የሚያወጣ" ብለው ነው።

ከዚህ ቀደም በጁዲያ እና ሳሚራ አካባቢ የነበረውን "አይሁዳውያንን፣ አሜሪካውያንን፣ አውሮፓውያንን እና አረብ ያልሆነን ሕዝብ የሚያገል" የመኖሪያ ቤት ይዞታ "የሚያስተካክል" እንደሆነም ገልጸዋል።

የደኅንነት ካቢኔው ውሳኔ በዌስት ባንክ የሪል ስቴት ባለቤት ለመሆን ተቀምጦ የነበረውን ሕጋዊ አሠራር የሚያጥፍ መሆኑ ፍልስጤማውያንን አስግቷል።

አዲሱ አሠራር የመሬት ሽያጭን ለማጭበርበር ቀላል እንደሚያደርገው ፍልስጤማውያን ገልጸዋል።

ዌስት ባንክን የሚያስተዳድረው የፍልስጤም መንግሥት ፕሬዝዳንት ማሕሙድ አባስ፤ አዲሱ አሠራር "አደገኛ" ነው ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ "አሠራሩ የእስራኤልን መስፋፋት ሕጋዊ ዕውቅና የሚያላብስ፣ በፍልስጤም ይዞታ ሥር ያሉ ፍልስጤማውያንን ንብረት የሚያወድም እና መሬትን ግዳጅ ይዞታ የሚያጋልጥ ነው" ሲሉም ኮንነዋል።

አሜሪካ እና የመንግሥታቱ ድርጅት በአፋጣኝ ጣልቃ እንዲገቡ ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።

'ፒስ ናው' የተባለው የእስራኤል ተራድኦ ድርጅት በበኩሉ ውሳኔው የፍልስጤም አስተዳደርን አደጋ ውስጥ ይከትታል ብሏል። በዌስት ባንክ የመሬት ነጠቃን እንደሚያስፋፋም አስጠንቅቋል።

ውሳኔውን "በጽኑ አወግዛለሁ" ያለችው ዩናይትድ ኪንግደም፤ "የፍልስጤምን አወቃቀር እና ሕዝቡን የሚበርዝ እንዲሁም ዓለም አቀፍ መርሕን የሚጥስ" በመሆኑ እስራኤል እርምጃውን እንድትቀለብስ ጠይቃለች።

የግብፅ፣ የዩርዳኖስ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ኢንዶኔዥያ፣ ፓኪስታን፣ ቱርክ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውሳኔውን "ሕገ ወጥ ይዞታን የሚያስፋፋ እና ፍልስጤማውያንን ከቤት ንብረታቸው የሚያፈናቅል" ሲሉ አውግዘዋል።

እስራኤል በግዳጅ ይዞታ ሥር ባለው ዌስት ባንክ የምታራምዳቸው ፖሊሲዎች እና ሕገ ወጥ እርምጃዎች "ቀጣናቸውን ወደ ግጭት እና ነውጥ" እንደሚከቱ አገራቱ ገልጸዋል።

በዌስት ባንክ መሬት ለሰፋሪዎች መሸጥ በደላሎች አማካኝነት የሚከናወን ሲሆን፤ የፍልስጤም አስተዳደር እንደ አገር መክዳት ስለሚቆጥረው በሞት የሚያስቀጣ ድርጊት ብሎ ፈርጆታል።

አዲሱ ውሳኔ የሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ሥፍራዎች አስተዳደርን በእስራኤል ሥር ያደርጋል።

'ዘ ኬቭ ኦፍ ፓትሪያርክስ' ወይም 'ኢብራሒሚ ሞስክ' በመባል የሚያወቀው ሃይማኖታዊ ሥፍራ ለሙስሊሞች፣ ለክርስቲያኖች እና ለአይሁዳውያንም ትልቅ ትርጉም የሚሰጥ ነው።

አብርሃም፣ ይስሐቅ እና ያዕቆብም የተቀበሩበት ይህ ሥፍራ በሙስሊሞች ዘንድ አራተኛው ቅዱስ ቦታ ሲሆን፤ አይሁዳውያን ሁለተኛው ቅዱስ ቦታ ይሉታል።

አዲሱ ውሳኔ በፍልስጤም አስተዳደር ሥር ያሉ የአርኪዮሎጂ ሥፍራዎች አስተዳደርን ለእስራኤል አሳልፎ የሚሰጥም ነው።