አደጋ በደረሰባት ጀልባ ላይ የነበሩ 30 ስደተኞች ሜዲትራኒያን ላይ የደረሱበት ጠፋ

ከሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ የባሕር ዳርቻ ስደተኞችን የጫነች ጀልባ በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ተገልብጣ 30 ሰዎች የደረሱበት ጠፋ።

ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የተነሱ ስደተኞችን ያሳፈረችው ጀልባ አደጋው ከደረሰባት በኋላ 30 የሚደርሱት ሰዎች ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተሰግቷል።

በባሕር ላይ አደጋ የሚገጥማቸውን ስደተኞች የሚታደገው ‘አላርም ፎን’ የተባለው የሰብአዊ እርዳታ ቡድን፣ የአውሮፓ አገራት ለስደተኞቹ የግድየለሽነት አቋም ባይዙ ኖሮ ደብዛቸው የጠፋውን ሰዎች ማዳን ይቻል ነበር ብሏል።

የበጎ አድራጎት ቡድኑ እንዳለው በጀልባዋ ላይ ከነበሩት ስደተኞች የድረሱልን ጥሪ ከደረሰው በኋላ የሊቢያን፣ የጣሊያንን እና የማልታን ባለሥልጣናት ስለአደጋው የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።

የጣሊያን የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች ግን፣ ጀልባዋ በሊቢያ ጥበቃ በሚደረግበት የባሕሩ ክፍል ውስጥ የነበረች በመሆኑ እንዲሁም በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ወደ ቦታው መድረስ አዳጋች እንደበር ገልጿል።

የሊቢያ ባለሥልጣናት በበኩላቸው የነፍስ ማዳን ተግባር ለማከናወን የሚያስችላቸው ጀልባዎች እንዳልነበሯቸው ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ የሚመራው የጣሊያን ቀኝ አክራሪ መንግሥት የስደተኞቹን ሕይወት ለመታደግ አፋጣኝ እርምጃ አልወሰደም በሚል ጠንካራ ትችት እየቀረበበት ነው።

የጣሊያን የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች እሁድ ማታ ላይ 17 ሰዎችን ከባሕር ላይ ማትረፋቸውን ገልጻው፤ 30 ሰዎች ግን አለመገኘታቸውን አመልክተዋል።

ከተረፉት ስደተኞች መካከል ሁለቱ አስቸኳይ የሕክምና ድጋፍ ስለሚያስፍለጋቸው ወደ ማልታ እንደሚወሰዱ፣ ቀሪዎቹ ግን ወደ ጣሊያን መወሰዳቸው ተነግሯል።

ይህ አደጋ ያጋጠመው ባለፈው የካቲት ወር በተመሳሳይ በሕገወጥ መንገድ ወደ ጣሊያን ሊሻገሩ ሲሞክሩ በደቡባዊ ጣሊያን ከምትገኘው ካላብሪያ ግዛት አቅራቢያ በደረሰ አደጋ ቢያንስ 79 ሰዎች ከሞቱ በኋላ ነው።

በተለያዩ ሦስት አጋጣሚዎች ከ1,300 በላይ ስደተኞችን ከደቡባዊ የጣሊያን የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ እንዲሁም ተጨማሪ 200 ከሲሲሊ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ በጣሊያን የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች በሕይወት መትረፋቸው ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ የጣሊያን ገዢ ፓርቲ ፖለቲከኛ በአሁኑ ወቅት 700,000 የሚጠጉ ስደተኞች በባሕር በኩል ወደ ጣሊያን ለመግባት ሊቢያ ውስጥ ሆነው እየተጠባበቁ ናቸው ብለዋል።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ፓርቲ አባል የሆኑት ፖለቲከኛ ቶማስኮ ፎቲ ለአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት፣ የአገራቸው የደኅንነት ተቋም እንደገመተው 685,000 የሚሆኑ አብዛኞቹ በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ሊቢያ ውስጥ ይገኛሉ። እነዚህም በሕገወጥ የሰዎች አሸጋጋሪዎች አማካይነት ወደ ጣሊያን በባሕር በኩል ለመግባት እየጠበቁ ናቸው ብለዋል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 105,000 የሚሆኑ ስደተኞች የሜዲትራኒያን ባሕርን በአደገኛ ሁኔታ በማቋረጥ ወደ ኢጣሊያ መድረሳቸው ይነገራል።