ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዋይት ሐውስ ኢራን እና አሜሪካ የእስረኞች ልውውጥ ሊያደርጉ ነው መባሉ አስተባበለ
ኢራን በሁለቱ አገራት መካከል የአስረኞች ለውውጥ ሊደረገው ማለቷ “ጭካኔ የተሞላበት” ሐሰተኛ መረጃ ነው ስትል አሜሪካ አስተባበለች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁሴን አሚር አብዱላሂ እሁድ ዕለት ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት፣ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር እስረኛ ለመለዋወጥ መስማማቷን እና በቅርቡ ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
ሆኖም የዋይት ሐውስ የደኅንነት ቃል አቀባይ ንግግሩን አስተባብለው የኢራን ባለሥልጣናትን ኮንነው፣ የሚኒስትሩ ንግግር የእስረኞችን ቤተሰብ ልብ የሚሰብር ነው ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢራን ብሔራዊ ቴሌቪዢን ጣቢያ ቀርበው በአገራቸው እና በአሜሪካ መካከል ስምምነት መደረሱን በመጥቀስ “በአሜሪካ በኩል ነገሮች በጥሩ መልኩ ከቀጠሉ የእስረኞች ልውውጥ ሲደረግ በቅርቡ እናያለን” ብለዋል።
ጨምረውም አሜሪካ “ከፋይናነስ ጋር በተያያዘ ያሉ ጉዳዮችን ለመፍታት ስትሞከር” ኢራንም ዝግጁ ናት ብለው ነበር።
ይህንን ንግግር ሐሰት ነው ያለው ዋይት ሐውስ በበኩሉ፣ ኢራን ውስጥ የታሰሩ ሦስት ዜጎቿን ለማስፈታት አሜሪካ ቁርጠኛ ናት ብለዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2016 የነዳጅ ኩባንያ ኃላፊ የሆነው የአሜሪካ እና የኢራን ጥምር ዜግነት ያለው ሲያማክ ናማዚ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በመተባበር ኢራንን ሰልሏል በሚል ተከሶ 10 ዓመታት ተፈርዶበታል።
ሲያማክ ባለፈው ሳምንት በቴህራን እስር ቤት ውስጥ ለሲኤንኤን በሰጠው ቃለ መጠይቅ ፕሬዝዳንት ጆ ባይድን “ከዚህ ስቃይ እንድወጣ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ያድርጉ” ሲል ጠይቋል።
ኤማድ ሻርጊ የተባለው ሌላ የኢራን እና የአሜሪካ ዜግነት ያለው ባለሀብት እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 በቴክኖሎጂ ላይ የሚሰራ ኩባንያ ላይ ኢንቨስት ለማድርግ ወደ አገሪቱ በተጓዘበት ጊዜ ታስሯል።
ሞራድ ታሃህባዝ የተባለው ሌላኛው የኢራን-አሜሪካ ዜግነት ያለው እና የብሪታኒያን ዜግነት ደርቦ የያዘ ግለሰብ፣ የኢራንን ሕግ ችላ በማለት እንዲሁም ለአሜሪካ መሰለል ሚሉ ክሶች ቀርበውበት እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 የ10 ዓመት ፍርድ ተበይኖበታል።
ነገር ግን ባለፈው ሐምሌ ወር የኤሌክትሪኒክስ ቁጥጥር እየተደረገበት በዋስ የተለቀቀ ሲሆን፣ የዩናይትድ ኪንግደም ባለስልጣናት ሙሉ በሙሉ እንዲለቀቅ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ያለውን የኒውክለር ስምምነት ካቋረጡ እና የኢራንን ኢኮኖሚ ክፉኛ ያንኮታኮቱ ማዕቀቦችን ዳግም ከጣሉ በኋላ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረት ነግሷል።
ኢራን በርካታ የአሜሪካ እና የኢራን ዜግነትን በጥምር የያዙ ዜጎችን እና ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ሰዎች በቅርብ ዓመታት ውስጥ በስለላ ላይ ተሰማርተዋል የሚል ክስ አቅርባ አስራለች።
ኢራን በበኩሏ በአሜሪካ የታሰሩ ዜጓቹ እንዲፈቱ ስትጠይቅ ቆይታለች።