የአምባገነኑ ፕሬዝዳንት ልጅ የ240 ሚሊዮን ዶላር ንብረት ማፍራቷን ሪፖርት ይፋ አደረገ

የቀድሞ የኡዝቤኪስታን አምባገነን ፕሬዝዳንት የመጀመሪያ ልጅ በሕገ-ወጥ በተገኘ ገንዘብ የ240 ሚሊዮን ዶላር ንብረት ማፍራቷን አንድ ሪፖርት ጠቆመ።

ጉለናራ ካሪሞቫ ከለንደን እስከ ሆንግ ኮንግ የንብረት ባለቤት መሆኗን ፈሪደም ፎር ዩሮኢሲያ የተባለ ጥናት አድራጊ ተቋም ገልጿል።

ጉለናራ ካሪሞቫ በጉቦ እና ሙስና የተገኘ ገንዘብን ዩናይትድ ኪንግደም በሚገኙ ኩባንያዎች አማካይነት መኖሪያ ቤቶች እና ጄት ገዝታለች ብሏል ሪፖርቱ።

ሪፖርቱ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ሕጋዊ አድርገው ለሚጠቀሙ ወንጀለኞች የዩኬ ኩባንያዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን አጋልጧል። ሪፖርቶ ካሪሞቫ በዩኬ ንብረት በቀላሉ ንብረት ማፍራቷ ‘አሳሳቢ’ ነው ብሏል።

ካሪሞቫ ከእአአ 1989 እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው 2016 ድረስ ኡዝቤክስታንን የመሩት ወላጅ አባቷን እስላም ካሪሞቫ ልትተካ ትችላለቸ የሚል ሰፊ ግምት ነበር።

በፖለቲካ ተሳትፎዋ የስፔን አምባሳደር ሆና አገልግላለች። ከፖለቲካ ውጪ ደግሞ ‘ጎጎሻ’ በሚል የመድረክ ስም የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ነበረች። እንዲሁን የውድ ጌጣ ጌጥ ኩባንያን ትመራ ነበር።

እአአ 2014 ላይ ግን ከሕዝብ ዓይን ጠፋች። ዘግይቶ ወላጅ አባቷ ስልጣን ላይ ሳሉ በሙስና ወንጀሎች ተከሳ የቁም እስር እያሳለፈች መሆኑ ታወቀ። እአአ 2019 ላይ ደግሞ የቁም እስር ሕግጋትን ተላልፋለች ተብላ ዘብጥያ ወረደች።

ዐቃቤ ሕግ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ልጅ 1 ቢሊዮን ዶላር በዩኬ፣ ሩሲያ እና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ጨምሮ በ12 አገራት ንብረት የሚያስተዳድር ወንጀለኛ ቡድን አባል ነች ይላል።

“የካሪሞቫ ጉዳይ የሁል ጊዜም ትልቅ ከሚባሉ የጉቦ እና የሙስና ምርመራዎች መካከል አንዱ ነው” ይላሉ የጥናት አድራጊ ቡድኑ አባል የሆኑት ቶም ሜይን።

ፍሪደም ፎር ዩሮኢሲያ በሪፖርቱ ካሪሞቫ አጠራጣሪ በሆን ምንጭ በተገኘ ገንዘብ በዩናይትድ ኪንግደም፣ ስዊትዘርላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ እና ሆንግ ኮንግ 14 ንብረት መግዛቷን ገልጿል።

ሪፖርቱ ትኩረት ካደረገባቸው ንብረቶች መካከል በለንደን ከተማ የተገዙ አምስት ቤቶች የሚገኙበት ሲሆን ቤቶቹ አሁን ላይ 50 ሚሊዮን ፓዎንድ የሚያወጡ ሲሆን ገሚሱ ቤቶች ከዓመታት በፊት ተሽጠዋል።

የፍሪደም ፎር ዩሮኢሲያ ሪፖርት ካሪሞቫ እና አጋሮቿ ንብረት ለማንቀሳቀስ ሲጠቀሟቸው የነበሩ ግለሰቦች እና ኩባንያዎችን ጠቅሷል።

ከግለሰቦቹ መካከል የካሪሞቫ ፍቅረኛ ሩስታም ማዱማሮቭ በአንዳንድ ይፋዊ ሰነዶች ላይ ወራሽ ወይም አስተዳዳሪ ተብሎ የተመዘገ ቢሆንም ሪፖርቱ ግን የንብረቶቹ ባለቤትም ሆነ ትክክለኛ አስተዳዳሪ ካሪሞቫ ነች ይላል።