ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቢቢሲ አለቃ በሊኒከር ጉዳይ ይቅርታ ቢጠይቁም 'ሥልጣን ግን አልለቅም' አሉ
የቢቢሲ ዳይሬክተር ጀነራል ቲም ዴቪ ከጋሪ ሊንከር ጋር በተያያዘ ለተፈጠረ የፕሮግራም ክፍተት ተመልካቾችን ይቅርታ ጠይቀው ከሥልጣናቸው ግን እንደማይለቁ ገለጹ።
ቲም ዴቪ ይቅርታውን የጠየቁት በክፍያ የስፖርት ዝግጅቶችን የሚመለከቱ ተመልካቾች ዝግጅቶች ተሟልተው ስላልቀረቡላቸው ነው።
ትናንት ቅዳሜ ማቸ ኦፍ ዘ ደይ የተባለውን ፕሮግራምን ጨምሮ በርካታ የቢቢሲ የእግር ኳስ ፕሮግራሞች እንዲታጠፉ፣ ርዝመታቸው እንዲቀነስ አልያም ደግሞ ያለ ተንታኞች እንዲቀርቡ ተደርጎ ነበር።
ይህ የሆነው ደግሞ የቢቢሲ የስፖርት ፕሮግራም አዘጋጆች እና ተንታኞች ለጋሪ ሊኒከር ድጋፋቸውን ለመግለጽ ከቢቢሲ ሥራዎች እራሳቸውን ካገለሉ በኋላ ነው።
አለመግባባቱ ከየት መጣ?
እውቁ የስፖርት ተንታኝ ጋሪ ሊንከር በማሕበራዊ ሚዲያ በስደተኞች ጉዳይ ላይ ፖለቲካዊ አስተያየት መስጠቱን ተከትሎ እራሱን ከስራው እንዲያገል ቢቢሲ ጠይቆት ነበር።
ለስደተኞች መብት ተቋርቋሪ የሆነው ጋሪ ሊንከር ዩናይትድ ኪንግደም በእንግሊሽ ቻናል በኩል ወደ አገር የሚመጡ ስደተኞችን ወደ ትውልድ አገራቸው አልያም ወደ ሦስተኛ አገር እመልሳለሁ ማለቷን በጥብቅ ተችቷል።
ሊንከር የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚንስቴር ስደተኞችን አልቀበልም በሚል ባወጣው መግለጫ ጥቅም ላይ የዋለውን ቋንቋ እአአ በ1930ዎቹ ከነበረው ናዚ ጀርመን ጋር አያይዞ አስተያየቱን ሰጥቷል።
በዚህም የስፖርት ተንታኙ ከዩናይትድ ኪንግደም ገዢ ፓርቲ ከሆነ የወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች የሰላ ትችት ሲቀርብበት የቆየ ሲሆን ቢቢሲም ከቀናት በፊት ሊኒከር የሰጠው አስተያየት የቢቢሲን የገለልተኛነት ኤዲቶሪያል ፖሊሲ የሚጥስ ነው በማለት ተንታኙ ከቢቢሲ ፕሮግራሞች እራሱን እንዲያገል ጠይቆት ነበር።
የቢቢሲ ውሳኔም ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን ከሊንከር ጋር አብረው የሚሰሩት እንደ አይን ራይት እና አለን ሺረር ያሉ እውቅ የስፖርት ተንታኞች ለባልደረባቸው ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ በቢቢሲ የስፖርት ፕሮግራሞች እንደማይቀርቡ አስታውቀው ነበር።
ይህን ተከትሎም የስፖርት መረሃ ግብሮች ላይ ያልተጠበቁ ለውጦች መጥተዋል። የትናንት ምሽቱ ማች ኦፍ ዘ ደይ ፕሮግራም ላይ ተንታኞች አልቀረቡም። በእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይም አስተያየት የሚሰጥ ባለሙያ ባለመኖሩ ከስታዲየም በሚወጣ ድምጽ ተሸፍኖ ነበር።
የቢቢሲ ዳይሬክተር ጀነራል ቀኑ ለቢቢሲ “አስቸጋሪ ነበር” ያሉ ሲሆን “ሁኔታውን ለማስተካከል በጣም ጠንክረን እየሰራን ነው” ብለዋል።
ቲም ዴቪ ዓላማቸው ጋሪ ሊኒከርን ወደ ቢቢሲ ስቱዲዮ በመመለስ አድማጭ ተመልካቾች ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የስፖርት ፕሮግራሞችን እንዲያገኙ ማስቻል ነው ብለዋል።
ለእግር ኳስ ተንታኙ ድጋፋቸውን እየገለጹ ያሉ አስተያየት ሰጪዎች ግን ቲም ዴቪ ስልጣናቸውን እንዲለቁ እየጠየቁ ነው።
ዳይሬክተር ጀነራሉ ግን ወቅቱ ለቢቢሲ አስቸጋሪ መሆኑን አምነው “ይህን በፍጹም አላደረገውም” ብለዋል።
ከቲም ዴቪ በተጨማሪ የወግ አጥባቂ ፓርቲ አጋር ናቸው የተባሉት የቢቢሲ ቦርድ ሰብሳቢ ሪቻርድ ሻርፕ በተመሳሳይ ስራቸውን እንዲለቁ እየተጠየቁ ነው።
ግለሰቡ ከዚህ ቀደም ለወግ አጥባቂ ፓርቲ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውና ለቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንስ የ800ሺህ ፓዎንድ ብድር አሰጥተዋል መባሉት ተከትሎ በሚዲያ አዘጋጋብ ገለልተኛ ሊሆኑ ስለማይችሉ ከስራቸው ይልቀቁ እየተባለ ነው።