በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኢትዮጵያዊውን የደበደበ የውጭ አገር ሠራተኛ እና ኃላፊው ከአገር ተባረሩ

በሐዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ "በተደጋጋሚ በሥራ ገበታው ላይ በሰዓቱ አልተገኘም" በሚል አንድ ኢትዮጵያዊ ሠራተኛ ላይ ድብደባ የፈጸመ የውጭ አገር ዜጋ እና ጉዳዩ ይመለከተዋል የተባለ የኩባንያው ኃላፊ ከአገር ተባረሩ።

የሐዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቲዎስ አሸናፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሥራ ሁኔታ ጋረ በተገናኘ በተከሰተ አለመግባባት የውጭ ዜጋ የሆነ ሠራተኛ አንድ ኢትዮጵያዊ ላይ በፈጸመው አካላዊ ጥቃት እርምጃው ተወስዷል።

ክስተቱን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መጋራቱን ተከትሎ ጥያቄ እና ቁጣ የተፈጠረ ሲሆን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ድርጊቱ ተቀባይነት የሌለው እና አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ እንደሚያደርግ ገልጾ ነበር።

በተለያዩ ጊዜያት በአንዳንድ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ የኃላፊ እና የሥራ መሪ የሆኑ የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ላይ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫና እንዲሁም ጥቃቶችን እንደሚፈጸሙ ሲሰማ ቆይቷል።

የሐዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቲዎስ ለቢቢሲ እንደገለጹት ድብደባው መፈጸሙ እንደታወቀ ተጎጂው ሠራተኛ የሕክምና ድጋፍ እንዲያገኝ መደረጉን እንዲሁም አስፈላጊው መረጃ ተሰብስቦ በጥፋተኞቹ ላይ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ተደርጓል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሚያስተዳድረው ኮርፖሬሽን እርምጃውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ጥቃት ከፈጸመው የውጭ አገር ዜጋ እና ኃላፊው በተጨማሪ ችግሩ ከደረሰበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት አስፈላጊውን እርምጃ አልወሰዱም የተባሉ የኩባንያው አምስት ኃላፊዎች ላይም እርምጃ መወሰዱን አስታውቋል።

ኢትዮጵያዊ ሠራተኛን የደበደበው የውጭ አገር ሠራተኛ "የድርጅቱ የሥነ ምግባር መመሪያ ባለማክበር" እንዲሁም ጉዳዩ ይመለከተዋል የተባለ የኩባንያው የሥራ ኃላፊ በተቆጣጣሪው እና በሠራተኛው መካከል አለመግባባት ሲፈጠር "ተገቢውን አስተዳደራዊ ክትትልና እርምጃ ባለመውሰዱ" ከሥራ መሰናበታቸውን አስታውቋል።

የዞኑ ሥራ አስኪያጅም በሁለቱ የውጭ ዜጎች ላይ ከተወሰደው ከሥራ የማባረር እርምጃ በተጨማሪ ከአገር እንደተባረሩ ገልጸዋል።

ለሁለቱ የውጭ ዜጎቹ ከአገር መባረር እና ለሌሎች ኃላፊዎች መቀጣት ምክንያት የሆነው በግጭት የተፈጠረው በሐዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ በሚገኘው 'ቶዮ ሶላር ኩባንያ' ውስጥ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ያለመግባባቱ እና የግጭቱ መንስዔ ኢትዮጵያዊው ሠራተኛ "በተደጋጋሚ በሥራ ገበታው ላይ በሰዓቱ አልተገኘህም" በሚል እንደሆነ እና ይህንንም ተከትሎ ዜግነቱ ባልተጠቀሰ የኩባንያው ተቆጣጣሪ እና በሠራተኛው መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ወደ አካላዊ ጥቃት መድረሱ ተገልጿል።

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በሚገኘው ኩባንያ ውስጥ በኢትዮጵያዊው ሠራተኛ ላይ የተፈጸመውን ድብደባ የሚያሳየው ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተሠራጨ ሲሆን፣ በቪዲዮ ላይ የሥራ ልብሳቸውን የለበሱ ሰዎች በተሰበሰቡበት ዜግነቱ ያልተገለጸው የውጭ ዜጋ በአንድ ግለሰብ ላይ ድብደባ ሲፈጽም ይታያል።

ግጭቱ የተፈጠረው በሥራ ቦታው ውስጥ እንደሆነ ከቪዲዮው መረዳት የሚቻል ሲሆን ተደብዳቢው ራሱን ስቶ ሲወድቅ እና ሌሎች ከብበው ሲመለከቱት ይታያል።

የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎችም እንዲህ ያለው ክስተት ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ላይ እየተለመደ መምጣቱን እና ያልታዩ በርካታ ሊኖሩ እንደሚችሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

ክስተቱ ያጋጠመበት የሐዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቲዎስ አሸናፊ ግን በዞኑ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች መብት እና ክብር እንዲጠበቅ በሕግ እና በሥርዓት ክትትል እንደሚደረግ፣ ችግሮች ሲያጋጥሙም ተገቢው ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተፈጸመውን ድብደባ ተከትሎ በደረሳቸው ሪፖርት መሠረትም በሁለቱ ላይ ከአገር የማባረር እንዲሁም በሚመለከታቸው ሌሎች ላይ ደግሞተገቢ የሆነ አርምጃ መወሰዱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን በበኩሉ የተፈጠረው አለመግባባት መፈታት የነበረበት "የሠራተኞችን ሰብዓዊ መብት በጠበቀ መልኩ በሕግ እና በድርጅቱ ፖሊሲ መሠረት" መሆን ነበረበት በማለት ከዚሁ ክስተት ጋር በተያያዘ በአምስት የኩባንያው ኃላፊዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም አስታውቋል።

ተጨማሪ ሦስት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም የተባሉ ሥራ አስኪያጆችም "ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ" እንደተሰጣቸው ኮርፖሬሽኑ ተጠቅሷል።

የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ ላይ የተፈጠረውን ድርጊት አውግዞ ድብደባ የደረሰበት ኢትዮጵያዊ ሠራተኛ እንደታከመ እና በመልካም ጤንነትም እንደሚገኝ ገልጾ ነበር።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም እንዲሁ በተመሳሳይ በሐዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ በሚገኝ ኩባንያ ውስጥ የተፈጸመው ድርጊት ተቀባይነት የሌለዉ መሆኑን ገልፆ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ሕግ ተላልፈዉ በተገኙ የድርጅቱ ሠራተኞች ላይ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጾ ነበር።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስር ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች፣ አንድ ነፃ የንግድ ቀጠና እና ሦስት ፓርኮችን ያስተዳድራል።

ሠራተኛወ የተደበደበበተ፣ ሁለት የውጭ አገር ዜጎች ሠራተኞቹ ከአገር የተባረሩበት እንዲሁም ሌሎች ባልደረቦቹ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደበት ቶዮ ሶላር ኩባንያ ሁለት ሺህ ያህል ሠራተኞች አሉት።

በተጨማሪም በየወሩ ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ምርት ወደ ውጪ አገራት ኤክስፖርት እያደረገ ያለ ኩባንያ መሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጠቅሷል።