ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሚድሮኩ ሆራይዘን ፕላንቴሽንስ እንዴት "በሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ" እና "በታፈሱ ሰዎች" ቅጥር ተጠያቂ ሳይሆን ቀረ?
- ፀሐፊ, አማኑኤል ይልቃል
- የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ አማርኛ
በ2017 ዓ.ም. መጀመሪያ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መርማሪዎች በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ወደሚገኘው የሚድሮክ ሆራዘን ፕላንቴሽን አንድ የእርሻ ጣቢያ ሲያመሩ ያጋጠማቸው የጠበቁት አልነበረም። በእርሻ ጣቢያው የተሰበሰቡ ሰዎችን የተመለከቱት መርማሪዎቹ፤ ጠጋ ብለው ከየት እና እንዴት እንደመጡ ጠየቁ።
ግለሰቦቹ ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች ታፍሰው ለቀናት ከታሰሩ በኋላ በኩባንያው እርሻዎች ላይ እንዲሠሩ የመጡ ነበሩ። ጉዳዩ ለኢሰመኮ መርማሪዎች ያልታሰበ ነበር። ኢሰመኮ በሆራይዘን የእርሻ ጣቢያዎች ውስጥ አሳሳቢ የሠራተኛ "ቅጥር" ሁኔታን ሲያገኝ የመጀመሪያው አይደለም።
የተቋሙ ባለሙያዎች ቀድሞውንም ወደ ስፍራው ያመሩት ከዚህ ቀደም በኩባንያው እርሻ ጣቢያዎች እየተፈጸመ ያገኙት የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ መቆሙን ለማረጋገጥ ነበር።
ኢሰመኮ እስካሁን ይፋ ያላደረገው ይህ ግኝት ዕድሜያቸው ከስምንት ዓመት ጀምሮ የሆኑ ሕጻናት ተማሪዎች፤ ኩባንያው ለትምህርት ቤት ግንባታ "ያበደረው ገንዘብ በጉልበታቸው እንዲከፈል" ጭምር ቡና እንዲለቅሙ መደረጉን የሚያሳይ ነው።
በድንገት የተደረሰበት የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የቡና እርሻ ጣቢያዎች ውስጥ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ እየተፈጸመ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ደረሰበት በ2016 ዓ.ም. የክትትል ቡድኖችን ባሰማራበት ወቅት ነበር። የኢሰመኮ ባለሙያዎች በቦታው የተገኙት፤ የእርሻ ጣቢያዎች ያለውን የሴቶች እና ወጣቶች መብት አያያዝ በተመለከተ ክትትል ለማድረግ ነው።
የኮሚሽኑ የሕጻናት መብቶች አስተባባሪው ይድነቃቸው ከበደ እንደሚናገሩት፤ አገር አቀፉ ክትትል ከተደረገባቸው ሰባት ክልሎች ውስጥ በሦስቱ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ እየተፈጸመ ስለመሆኑ ተደርሶበታል።
ከእነዚህ ክልሎች አንዱ ኦሮሚያ መሆኑን አረጋግጠዋል። በኦሮሚያ ክልል የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ የተገኘው በየትኛው ኩባንያ የእርሻ ጣቢያዎች እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበዋል።
ቢቢሲ የተመለከተው ይፋ ያልተደረገ የኢሰመኮ ሪፖርት እርሻ ጣቢያዎቹ የሚድሮኩ "ሆራይዘን ፕላንቴሽንስ" ንብረት እንደሆኑ አስፍሯል። ለዚህ ዘገባ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ከ10 በላይ የቀድሞ እና የአሁን ሠራተኞችም የኩባንያው እርሻዎች ተማሪዎችን ቡና ሲያስለቅሙ እንደነበር አረጋግጠዋል።
ኢሰመኮ ሐምሌ ወር ላይ ባወጣው የ2017 ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሪፖርት ላይም የድርጅቱ ስም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ተጠቅሷል። ባለ 152 ገጹ የኢሰመኮ ሪፖርት በሆራይዘን ፕላንቴሽንስ የእርሻ ጣቢያዎች ሲፈጸም የነበረ "ሕፃናትን በቡና ለቀማ ላይ የማሰማራት አሠራር እና የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ መቆሙን"፤ እንደ "ቁልፍ እምርታ" ጠቅሶታል። የደረሰበትን ግኝት ግን በዝርዝር አላቀረበም።
የሕጻናት መብቶች አስተባባሪው ይድነቃቸው በእርሻ ጣቢያዎች ላይ የተደረገው ክትትል ሪፖርት አሁንም "በግምገማ ሂደት ውስጥ እያለፈ" መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል። በዚህ ምክንያት "ጠቅላላ የሆነ መረጃ ከመስጠት ባለፈ ለይተው [የኩባንያ] ስም እየጠቀሱ" ለመናገር እንደሚቸገሩ አስረድተዋል።
ይፋ ያልተደረገው ሪፖርት ዝርዝሮች
በግዙፉ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር የሚገኘው ሆራይዘን ፕላንቴሽንስ ከዚህ ቀደም በመንግሥት ባለቤትነት ስር የነበሩ ስድስት ሰፋፊ እርሻዎችን ያስተዳድራል። በእርሻዎቹ ከሚመረተው ቡና ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብ የሚድሮክ መረጃ ያመለክታል። እንደ ስታርባክስ ያሉ ዓለም አቀፍ የቡና ኩባንያዎች የሆራይዘን ደንበኞች እንደሆኑም በድረ ገጹ ተጠቅሷል።
ኢሰመኮ፤ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ድርጊቶችን ያገኘው ሊሙ ኮሳ፣ ጉመር እና ሡንጡ በተባሉት የሆራይዘን ፕላንቴሽንስ የእርሻ ጣቢያዎች ውስጥ ነው። አምስት በኩባንያው እየሠሩ ያሉ እና የቀድሞ ሠራተኞች፤ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ለቡና ለቀማ ሲያሰማሩ እንደነበር ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ቢቢሲ በተመለከተው የኢሰመኮ ሪፖርት፤ ዕድሜያቸው "ከ8 ዓመት" ጀምሮ የሆኑ ሕጻናት በጅማ ዞን ሊሙ ኮሳ ወረዳ በሚገኙት እርሻ ጣቢያዎች እንዲሠሩ መደረጉን ያመለክታል። የኮሚሽኑ መርማሪዎች "ዕድሜያቸው ከስምንት እስከ 13 የሆኑ እና ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል የሚማሩ ሕፃናት" ቡና ሲለቅሙ እንዳገኙ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
ሕጻናቱ ለለቀማ የተሰማሩት በኩባንያው እና በአካባቢው ትምህርት ቤቶች መካከል በተደረገ ስምምነት አማካኝነት እንደሆነ ሪፖርቱ ያመለክታል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሠራተኞችም ይህንኑ አረጋግጠዋል።
በሆራይዘን ፕላንቴሽንስ እና በትምህርት ቤቶች "መካከል በተደረገው ስምምነት በቡና ለቀማ ወቅት ተማሪዎች በሳምንት ለሁለት ቀናት በትምህርት ሰዓት ቡና እንዲለቅሙ እንደሚደረግ" በሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።
ስምምነቶቹ ሁለት ዓይነት ይዘት አላቸው። የመጀመሪያው የስምምነት ዓይነት ትምህርት ቤቶቹ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ሲባል ተማሪዎች ቡና የሚለቅሙበት ነው።
የድርጅቱ ሠራተኛ እና የወላጆች ኮሚቴ አባል የነበሩ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፤ ከተማሪዎቹ ቡና ለቀማ የሚገኘው ገቢ የሚሰጠው ለትምህርት ቤቶቹ እንደሆነ ተናግረዋል። የኢሰመኮ ሪፖርትም በበኩሉ፤ "ክፍያዉ የሚፈጸመው ለትምህርት ቤቶች መሆኑን በክትትሉ ለማረጋገጥ ተችሏል" በማለት ተመሳሳይ አሠራር ጠቅሷል።
ሌላኛው የስምምነት ዓይነት "የሕፃናቱን ጉልበት ለዕዳ መክፈያነት" መጠቀምን የሚመለከት ነው። የጉመር እርሻ ጣቢያ ሠራተኞች ልጆች የሚማሩባቸው "የጉመር የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች" ሲገነቡ፤ ሆራይዘን ፕላንቴሽንስ "አስር ሺህ ብር በስጦታ ሁለት መቶ ሺህ ብር ደግሞ በብድር" እንዳቀረበ ሪፖርቱ ያስረዳል።
"ትምህርት ቤቱም ከሆራይዘን የወሰደውን የሁለት መቶ ሺህ ብር ብድር ለመመለስ" በሚል በትምህርት ቀናት ጭምር ሕጻናቱ እንዲሰሩ ማድረጉን ይገልጻል። ሪፖርቱ "ተማሪዎችን በትምህርት ቀናት ጭምር ከ10 እስከ 15 ለሚደርሱ ቀናት በቡና ለቀማ ሥራ ላይ በማሰማራት የሕፃናቱን ጉልበት ለዕዳ መክፈያነት እየተጠቀመ እንደሆነ ማረጋገጥ ተችሏል" ይላል።
ግዳጅ እና ቅጣት
ሕጻናት ተማሪዎች በእርሻ ጣቢያዎች የተሰማሩት "በግዳጅ" እንደሆነ በኢሰመኮ ሪፖርት ላይ ሰፍሯል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የሆራይዘን ፕላንቴሽንስ ሠራተኛ "ወላጆች ተማሪ ልጆቻቸውን ወደ እርሻው የሚልኩት በግዴታ" እንደሆነ ገልጿል።
"ቡና ያልለቀሙ ተማሪዎች ቤተሰቦቻቸው ብር እንዲከፍሉ ይገደዳሉ። አለበለዚያ ደግሞ 'ትምህርት ቤት ሄደህ አትማርም፣ ወላጅ አምጣ' ተብለው የሚመለሱበት ሰዓት ነበር" ሲል እማኝነቱን ሰጥቷል። "አንድ ተማሪ አንድ ዙር ሄዶ ቡና ካልለቀመ 250 ብር ይዞ መቅረብ አለበት" ሲልም በኮሳ እርሻ ጣቢያ ላይ ተማሪዎቹን ያሰማራ የአንድ ትምህርት ቤት አሠራርን አስረድቷል።
በሡንጡ የእርሻ ጣቢያ ላይ ተማሪዎቹን ያሰማራውን "ለኩ ጪሜ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት" የጠቀሰው የኢሰመኮ ሪፖርትም በተመሳሳይ፤ "በቡና ለቀማ ሥራ ላይ ባልተሰማራ" ተማሪ ላይ "በቀን 250 ብር ቅጣት" ሲጣል እንደነበር ይገልጻል።
"[ተማሪው] ቅጣቱን ካልከፈለ ደግሞ ከትምህርት ቤቱ ሊባረር እንደሚችል ኢሰመኮ ከተማሪ ሕፃናት እና ከወላጆቻቸው ጋር ባደረገው ውይይት አረጋግጧል" በማለትም አክሏል።
ሕጻናቱ ለአደጋ በሚጋለጡበት ሁኔታ ውስጥ እና ለረጅም ሰዓታት ቡና እንዲለቅሙ መደረጋቸውም በሪፖርቱ ላይ የተጠቀሰ ጉዳይ ነው።
በጉመር እርሻ ጣቢያ ተሰማርተው የነበሩ "ዕድሜያቸው ከ14 በታች የሆኑ ሴት ተማሪዎች" ቡና በሚለቅሙበት ወቅት "በወንድ ተማሪዎች ፆታዊ ትንኮሳ እንደሚፈጸምባቸው እና ይህንንም ለመምህራንም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው ለመናገር እንደሚፈሩ" መናገራቸውን በሪፖርቱ ላይ ተካትቷል።
ተማሪዎቹ ለዚህ ዓይነቱ ጥቃት የተጋለጡት "በቡና ለቀማ ወቅት በጫካ ውስጥ አስተማማኝ የደኀንነት ጥበቃ" ባለመኖሩ እንዲሁም ይዘዋቸው የመጡት መምህራን የሚከታተሏቸው "አልፎ አልፎ ብቻ ብቅ እያሉ" ስለሆነ መሆኑን ያስረዳል።
የሕጻናት መብቶች አስተባባሪው አቶ ይድነቃቸው፤ ቢቢሲ በተመለከተው ሪፖርት ላይ ስለተጠቀሰው የፆታዊ ጥቃት ድርጊት ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ይህ ጉዳይ "የእኛ ግኝት አይደለም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። "ሴት ሠራተኞችን ስንጠይቃቸው 'የደረሰብን ጥቃት አለ' ብለው ይሄ፣ ይሄ ብለው ያስቀመጡልን የለም" የሚሉት አስተባባሪው፤ የእርሻ ሥራ የሚከናወነው "ጫካ ውስጥ" ከመሆኑ አንጻር ግን "ሴት ሠራተኞች የበለጠ ለፆታዊ ጥቃት ተጋላጭ" ሊሆኑ እንደሚችሉ አስታውሰዋል።
በተጨማሪም የኢሰመኮ መርማሪዎች አንዲት ተማሪ በዚሁ የእርሻ ጣቢያ ቡና እየለቀመች በነበረበት ጊዜ "ከጎሬው የወጣ ጅብ ሲያባርራት ወድቃ ጉዳት እንደደረሰባት"፤ "በተማሪዋ ቤት በመገኘት ተጎጂዋን እና የተማሪዋን ቤተሰብ በማነጋገር" አረጋግጠዋል።
ሪፖርቱ "ጉዳት የደረሰባት ተማሪ ክትትሉ እስከተደረገበት ወቅት በእርሻ ጣቢያው የተደረገላት ምንም ዓይነት የሕክምና እርዳታ አለመኖሩንም ገልጻለች" ይላል።
ሕጻናቱ የለቀሙትን "በግምት ከ25-30 ኪሎ ግራም የሚመዝን ቡና" ተሸክመው እንደሚያደርሱ፣ ክትትል በተደረገበት ዕለት "እስከ ምሽቱ 12፡30 ድረስ ሲሠሩ እንደነበር" እንዲሁም ምግብ እና ውሃ ከቤታቸው ይዘው ያልመጡ ተማሪዎች "ለረሃብ እና ውሃ ጥም እንደሚጋለጡ" በሪፖርቱ ላይ ተዘርዝሯል።
"ሕፃናቱ ከትምህርት ቤት ወደ እርሻ ጣቢያው በአይሱዙ ተሸከርካሪዎች ተጭነው እንደሚመጡ እና በርካታ ሕፃናት በአንድ ላይ ተጨናንቀው ስለሚጓዙ አደጋ ይደርስብናል የሚል ሥጋት እንዳለባቸው ለኢሰመኮ ገልጸዋል" ሲልም ያስረዳል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የሆራይዘን ሠራተኛ እና ሌላ የአካባቢው ነዋሪም በወላጆች ዘንድ ይህ ስጋት እንደሚነሳ አረጋግጠዋል።
ሌላኛው አሳሳቢ ጉዳይ፡ የታፈሱ ሰዎች 'ቅጥር'
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ግኝቱን ለፌደራል እና ለክልል መንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም ለሆራይዘን ፕላንቴሽንስ ማሳወቁን አቶ ይድነቃቸው ይናገራሉ። ከስምንት ወራት በኋላ ለድጋሚ ክትትል ባለሙያዎችን ወደ እርሻ ጣቢያዎቹ መላኩን ያስታውሳሉ። ሌላኛው አሳሳቢ ጉዳይ የተደረሰበት በዚህ ጊዜ ነው።
አቶ ይድነቃቸው እንደሚናገሩት፤ ወደ ስፍራው ያመሩት የኢሰመኮ ባለሙያዎች ወደ "እርሻ ጣቢያዎች የሚሄዱ ሠራተኞችን" አግኝተዋል። "ባለሙያዎቹ ሲያጣሩ፤ በአዲስ አበባ የጎዳና ላይ ልጆች እንደነበሩ እና ወደ ማቆያ ገብተው እንደነበረ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ከተወሰኑ ቀናት ወደዚህ ሥራ እንዲሠሩ እንደመጡ እና የመጡትም ያለ ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸውላቸዋል" ሲሉ የባለሙያዎቹን ግኝት አስረድተዋል።
አስተባባሪው፤ ይህ ጉዳይ በየትኛው ኩባንያ የእርሻ ጣቢያ እንደተገኘ ከመናገር ተቆጥበዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት የእርሻ ጣቢያ ሠራተኞች ግን በ2015 እና 2016 ዓ.ም. መጨረሻ ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች የታፈሱ ሰዎች ወደ ሆራይዘን እርሻዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።
ቢቢሲ፤ ነሐሴ 2016 ዓ.ም. ወደ ኩባንያው እርሻዎች የተወሰዱ ሦስት ሰዎችን አነጋግሯል። ግለሰቦቹ እንደሚያስረዱት፤ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በፖሊስ ከተያዙ በኋላ "ቃሊቲ ውሃ ልማት አካባቢ" በሚገኝ መጋዘን እንዲቆዩ ተደርገዋል።
ከእነዚህ ወጣቶች አንዱ በህንጻ ግንባታ ላይ እየሠራ የነበረው ካሳሁን መለሰ (ስሙ የተቀየረ) ነው። ካሳሁን መርካቶ ተክለ ሃይማኖት አካባቢ በአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የተያዘው ራት ለመብላት ከባልደረቦቹ ጋር በወጣበት አጋጣሚ እንደነበር ያስታውሳል።
"ህንጻ ኮንስትራክሽን ውስጥ ኦቨር ታይም እየሠራን ከምሽቱ ስድስት ሰዓት አካባቢ ለእራት ስንሄድ ነው የተያዝነው" የሚለው ካሳሁን፤ የፖሊስ አባላት እርሱን እና ባልደረቦቹን "ምንም ሳይለዩ" እንደያዟቸው ይናገራል።
"እንዲሁ" በፖሊስ የተያዘው ካሳሁን ብቻ አልነበረም። ጓደኞቹን ለማግኘት እየሄደ እንደነበረ የገለጸ ሌላ እማኝ፤ ልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ ከታክሲ ሲወርድ በፖሊስ መያዙን ተናግሯል።
እማኞቹ እንደሚያስረዱት፤ ታስረው ከነበሩት ሰዎች መካከል "የመንግሥት ሠራተኞች" እንዲሁም "በመምህርነት" እና "በአሽከርካሪነት" የሚሠሩ ግለሰቦች ይገኙበታል።
ኢሰመኮ ጥር ላይ ባወጣው መግለጫ ኑሯቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ሰዎች ተይዘው የሚቆዩት ቃሊቲ በሚገኘው "የአሽከርካሪዎች ማሠልጠኛ አካባቢ ባለ ሰፊ መጋዘን" ውስጥ እንደሆነ ገልጾ ነበር።
ካሳሁንም በቃሊቲው ማቆያ ለሁለት ሳምንት መታሰሩን ይናገራል። ታሳሪዎች ቤተሰብ ሆነ ሌላ ጠያቂ እንዲያገኙ እንዳልተፈቀደላቸው፣ ስልካቸውንም ተቀምተው እንደነበር አንስተዋል።
ካሳሁን ወደ ማቆያው ከገባ 15 ቀናት በኋላ ከታሳሪዎቹ መካከል የተወሰኑ ሰዎች እየተመረጡ "ወደ ሥራ" ተብለው መጫናቸውን ያስታውሳል። "ወደ እርሻ ብለው አልነገሩንም። ዝም ብለው እየመረጡ ነው 'ወደ ሥራ' ብለው ያስገቡት" ይላል።
ወደ እርሻው በተወሰደበት ዕለት "ዘጠኝ" ታታ ተብለው የሚታወቁት የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀሳቸውን ያስታውሳል። ተሽከርካሪዎቹ እያንዳንዳቸው "64 ገደማ" ሰዎችን ጭነው እንደነበረም ያስረዳል።
ካሳሁን እንደሚናገረው ከዚህ አስቀድሞ ሁለት ጊዜ "ገላን እና ዘነበ ወርቅ" አካባቢ በሚገኙ ማቆያዎች ውስጥ ታስሮ ነበር። "[ወደ ጅማ ሲወስዱን ግራ መጋባት] ተፈጥሮብኛል፤ ግን ያው [እስሩ] ተደጋጋሚ ስለሆነብኝ 'የደረስኩበት ልድረስ' ብዬ ነው ዝም ብዬ ተነስቼ የመጣሁት" ሲል በወቅቱ የተሰማውን ይናገራል።
ሌሎች ሁለት ምንጮች ግን ከቃሊቲው ማቆያ ከመውጣታቸው በፊት ለምን ዓይነት ሥራ እንደሚሄዱ እንደተገለጸላቸው አስረድተዋል። እርሻ ላይ ለመሥራት ከተስማሙት መካከል አንዳንዶቹ ለመሄድ ፈቃደኛ የሆኑት "ከእስር ለመውጣት" በሚል እንደነበር ገልጸዋል።
በጉዞ ላይ እያሉ "ያመለጡ" እንደነበሩም ይናገራሉ። አንድ እማኝ፤ ተሽከርካሪዎቹ ለምሳ ወልቂጤ ከተማ ላይ በቆሙበት ወቅት ያመለጡ ሰዎችን መመልከቱን ተናግሯል። ካሳሁንም በተመሳሳይ መኪናው ጅማ ከተማ ከደረሰ በኋላ ወደ ኩባንያው ከመተላለፋቸው በፊት በነበረው ጊዜ ያመለጡ እንደነበሩ ጠቅሷል።
ካሳሁን "አንድ መኪና እዚህ ሶኮሩ [በጅማ ዞን ውስጥ የሚገኝ ወረዳ] የሚባለው ቦታ ላይ ወድቆ ነበር። የተወሰኑ ልጆችም ተጎድተው ነበር፤ እየመሸ ስለነበር እኛ ጥለን ሄድን" ሲል በአደጋ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ እንዳሉ አስታውሷል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እማኞች፤ ጅማ ከተማ ከደረሱ በኋላ ወደ የሆራይዘን ፕላንቴሽንስ ተሽከርካሪዎች መዘዋወራቸውን፤ ከዚያም በተለያዩ እርሻ ጣቢያዎች መበተናቸውን ገልጸዋል። እርሻ ጣቢያዎቹ በሆራይዘን ፕላንቴሽንስ ስር የሚገኙት ኮሳ፣ በበቃ፣ ሊሙ፣ ጉመር እና ጨለለቂ መሆናቸውን ስድስት እማኞች እና የኩባንያው ሠራተኞች አረጋግጠዋል።
በዚህ መልኩ የመጡ ሰዎች በብዛት ቡና ለቀማ ላይ የቆዩ ሲሆን፣ ወደ ጨለለቂ ጣቢያ የተወሰዱት ደግሞ በበቆሎ እርሻ ላይ ሲሠሩ ነበር።
አንድ የሆራይዘን ሠራተኛ፤ ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች የመጡ ልጆች በቶሎ ከአካባቢው እና ከሥራው ጋር አለመላመዳቸውን ያስታውሳል።
"እንሄዳለን ብለው በጣም ይረብሻሉ። በብዛት 'ታመናል' ብለው ይተኛሉ። ሕክምና ቢደረግላቸውም እዚህ ከሚቀርብላቸው ምግብ ጋር ያልተዋሃዱ ልጆች አሉ" ይላል። "አንዳንዴ ደግሞ በደቦ የመቀመጥ ነገር ተባይ ይፈጥራል። ያቺን ያቺን ነገር መቋቋም አልቻሉም" ሲልም ያክላል።
ከእነዚህ ሠራተኞች መካከል ጥቂቶቹ አሁንም በሥራ ላይ ናቸው። በ2015 ዓ.ም. በተመሳሳይ መልኩ ከተወሰዱ ሰዎች ውስጥ በዚያው አካባቢ ትዳር መሥርተው እየኖሩ ያሉ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል።
አብዛኞቹ ሰዎች ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ መጡበት መመለሳቸውን የሆራይዘን ሠራተኞች ተናግረዋል። ሁለት የንዑስ እርሻ ኃላፊዎችም ይህንኑ አረጋግጠዋል።
መደበኛ ሥራ እያላቸው የተያዙ ሰዎች "ከቤተሰብ ገንዘብ አስልከው" መመለሳቸውን አንድ ሠራተኛ አስታውሷል። ሌላ እማኝ ደግሞ "ገንዘብ አዋጥተው ዕድሜያቸው ከፍ ያለ ሰዎች" ወደ መጡበት እንዲመለሱ ማድረጋቸውን አንስቷል።
ካሳሁን በበኩሉ፤ "ከሁለት ወር በላይ የሠራ የለም። ሳንቲም እስከሚወስዱ ድረስ ቆዩ፤ ከዚያ በኋላ ነው ተነስተው የሄዱት" ይላል። እርሱ ወደነበረበት ንዑስ እርሻ ከመጡ 68 ሰዎች ውስጥ አሁንም እየሠሩ ያሉት ሁለቱ ብቻ መሆናቸውን ያስረዳል።
የሆራይዘን ምላሽ
ሆራይዘን ፕላንቴሽንስ ከሕጻናት ጉልበት ብዝበዛም ሆነ ከታፈሱ ሰዎች ቅጥር ጋር የተያያዙትን ክሶች አይቀበልም። የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ነፃነት ጋሻዬ፤ "አገራችን የፈረመችውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ተከትለን አውሮፓ እና አሜሪካ አገራት ላይ ኤክስፖርት የምናደርግ ትልቅ ድርጅት ነን" ሲሉ የሚመሩትን ኩባንያ ተከላክለዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ በኢሰመኮ ከቀረበው ሪፖርት ውስጥ "ያልተቀበልናቸው በልዩነት የወጣንባቸው ነገሮች አሉ" ብለዋል።
አቶ ነፃነት "ለትምህርት ቤት ጥገና" የሚውል ገንዘብ መስጠትን ጨምሮ የኩባንያው እርሻ ጣቢያዎች ከትምህርት ቤቶች ጋር ስምምነት ፈጽመዋል መባሉን ይስማሙበታል። ስምምነቶቹ የተፈጸሙት "አካባቢውን ለመጥቀም"፣ "ተማሪዎችን ራሳቸውን እንዲያጎለብቱ" እንዲሁም ትምህርት ቤቶቹ የሚጠቀሙበት "ግብአት እንዲያገኙ" ለማድረግ እንደሆነ ያስረዳሉ።
"ነገር ግን ሕጉን ተከትለን ማለት ነው፤ በግዳጅ አይደለም። በአግባቡ ተግባብተን፣ ዕድሜያቸው የደረሱትን ለይተን፣ ከትምህርት ሰዓት ውጪ በሆነ መልኩ ነው የምንሠራው" ሲሉ ክሱን ውድቅ አድርገዋል።
ተማሪዎች ሲሰማሩ ነበረው "ቅዳሜ እና እሁድ" እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ነፃነት፤ እርሻ ላይ የሚቆዩትም "ከጠዋት 2 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት ገደማ" መሆኑን ይናገራሉ።
ይህም ቢሆን ግን ቡና ለቀማ ላይ የተሳተፉት "ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው" ብቻ እንደነበሩ በአጽንኦት ያነሳሉ። "የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆነው ከ15 እና ከ18 በላይ የሆኑ ልጆች አሉ" ሲሉም መከራከሪያቸውን ያጠናክራሉ።
ተማሪዎች በፈቃደኝነት ወደ እርሻ ጣቢያዎቹ ስለመምጣታቸው ሆራይዘን ማጣራት ያደርግ እንደሆነ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ነፃነት፤ "ተማሪ በራሱ ፈቃድ ነው የሚሠራው ግብአቱንም ሚያገኘው ለራሱ ነው። እንደዚህ በአስገዳጅ ሁኔታ የሚሠራበት ሁኔታ አለ ብዬ አላስብም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች የታፈሱ ሰዎችን በተመለከተ የቀረቡ ክሶችንም በተመሳሳይ ተቃውመዋል። እንደ አቶ ነጻነት ገለጻ፤ ድርጅታቸው በምርት ስብሰባ ወቅት የሚያስፈልጉትን በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ለማግኘት ከክልል እና ከፌደራል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር ይፈራረማል።
ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ካፋ ዞን እንዲሁም ሰሜን ቤንች እና ደቡብ ቤንች ወረዳዎች ጋር የተደረጉ የሠራተኞች ምልመላ ስምምነቶችን በማስረጃነት ለቢቢሲ አቅርበዋል። ስምምነቶቹ የሚመለመሉ ሠራተኞች ዕድሜ ከ18 ዓመት በላይ መሆን እንዳለበት ያሰፈሩ ናቸው።
ለቢቢሲ ያጋሯቸው የሆራይዘን እርሻ ጣቢያዎች የሥራ ቅጥር ማስታወቂያዎችም ተመሳሳይ መስፈርት አካትተዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በተያያዘ ያቀረቡት በከተማዋ የሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተጻፈን የምስጋና ደብዳቤ ነው። ዋና ሥራ አስፈጻሚው ማስረጃዎቹን ያቀረቡበት ዕለት እና ደብዳቤው የተጻፈበት ቀን ተመሳሳይ ነው።
መስከረም 21/2018 ዓ.ም. የተጻፈው የምስጋና ደብዳቤ፤ ሆራይዘን ፕላንቴሽንስ በመዲናዋ "ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተጋላጭ የነበሩ ከ2,000 በላይ ወጣቶች" ፤ "በጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ" ማድረጉን የሚገልጽ ነው።
ይህ የተደረገውም ከመስከረም 2015 እስከ ታኅሣሥ 2017 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት እንደሆነ ደብዳቤው ያስረዳል።
አቶ ነፃነት እንደሚናገሩት ከመንግሥት ጋር በሚደረጉ ስምምነቶች አማካኝነት ሠራተኞች በሚመለመሉበት ወቅት የኩባንያው ተወካዮች በቦታው ይገኛሉ። "ሁሉም ቦታ ላይ የራሳችን ተወካዮች ይኖራሉ፤ እነዚያ ተወካዮች መልምለው፣ በትክክል ዕድሜያቸው የደረሱ መሆኑን አረጋግጠው ተጭነው ብቻ ይመጣሉ" ሲሉ ሂደቱን አብራርተዋል።
ኩባንያው ከመንግሥት የሚቀርቡለት ሠራተኞች በፈቃዳቸው የመጡ ስለመሆናቸው ያጣራ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ "[ሠራተኛ] በሚመጣበት ሰዓት እና ልናደርግ የምንችለው ሕጋዊ መሆናቸውን [ማረጋገጥ] ብቻ ነው። ሌላው ነገር በሙሉ የመንግሥት አካል [ኃላፊነት] ነው" ብለዋል።
በዚህ መልኩ የመጡ ሠራተኞች በኩባንያው አሁንም ሥራ ላይ ያልሆኑት የምርት ስብሰባ የሚከናወነው ለሦስት ወራት በመሆኑ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ነፃነት፤ "'ፈቃደኛ ነኝ' ብሎ መቆየት ከፈለገ እኛ ጋር መቆየት ይችላል። 'አይ' ካለ ግን ምርቱን እንደጨረሰ ደግሞ መሄድ [ይችላል]፤ እኛ የምናስገደድበት አዋጅም ውልም ስለሌለን ማለት ነው" ብለዋል።
ቢቢሲ፤ ከጎዳና ላይ ተይዘው ወደ ሆራይዘን ፕላንቴሽንስ የተወሰዱ ሰዎችን በተመለከተ ከአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ምላሽ ለማግኘት ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች አልተሳኩም።
የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ቆንጂት ደበላ ከከተማ ውጪ በመሆናቸው ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል። የቢሮው ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ በበኩላቸው "ስለጉዳዩ ምንም መረጃ የለኝም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ደግሞ ጉዳዩን አጣርተው ምላሽ ለመስጠት ቃል ቢገቡም፤ ከዚያ በኋላ የስልክ ጥሪዎችን አልመለሱም።
የሕግ ማዕቀፍ፡ 'የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ' እና 'የግዳጅ ሠራተኝነት' የሚያስብለው ምንድነው?
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፤ ከ15 ዓመት በታች የሆናቸው ሕጻናት "ጫካ ውስጥ"፣ "ያለ ደኅንነት" እንዲሁም "ትምህርታቸው ቆሞ" እንዲሠሩ መደረጉን በመጥቀስ ድርጊቱ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ስለመሆኑ ይደመድማል።
ቢቢሲ ስለ ግኝቶቹ ገለጻ ያደረገላቸው ሁለት የሕግ ምሁራን በበኩላቸው ጉዳዩን ከዚህም ከፍ ባለ ደረጃ ላይ ያስቀምጡታል።
ከሠራተኛ ሕግ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ጥናት በማድረግ የሚታወቁት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ ዶ/ር መሃሪ ረዳኢ፤ ተማሪዎቹ ለቀማው ላይ ካልተሰማሩ የገንዘብ ቅጣት የሚጣልባቸው ከሆነ ጉዳዩ "የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ብቻ ሳይሆን የግዳጅ ሠራተኝነትም (forced labour) ባህሪ" ይኖረዋል ይላሉ።
የሰብአዊ መብቶች ጠበቃ እና አውስትራሊያ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኖተርዳም የሕግ መምህር የሆኑት ዶ/ር ህሩይ ውቤም ተማሪዎቹ ላይ የሚጣለውን ቅጣት አጽንኦት ይሰጡበታል። ድርጊቱ አስገዳጅ እና ቅጣት ያለበት መሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ 'አስከፊ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ' (worst forms of child labour) ተብሎ በሚጠራው ምድብ ውስጥ እንደሚያስገባው ይገልጻሉ።
በአውስትራሊያው ዩኒቨርሲቲ ስለ "ዘመናዊ ባርነት" የሚያስተምሩት ዶ/ር ህሩይ፤ ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የታፈሱ ሰዎች ጉዳይም "የግዳጅ ሠራተኝነት" ምድብ ውስጥ የሚገባ መሆኑን ያስረዳሉ። "ለዘፈቀደ እና ሕገ ወጥ እስር" የተዳረጉት እነዚህ ሰዎች፤ የሚፈልጉትን በነጻነት እንዲመርጡ የሚያስችላቸው ሁኔታ ላይ እንዳልነበሩ ያብራራሉ።
"እነዚህ ሰዎች እስረኛ ናቸው። በጣም በግልጽ ቋንቋ ሊመዘበር የሚችል ተጋላጭነት (abuse of vulnerability) አለባቸው። ምክንያቱም የታሰረ ሰው ምንም ቢሉት ያደርጋል" ይላሉ። የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት "የግዳጅ ሠራተኝነት ጠቋሚዎች" በሚል ካስቀመጣቸውን ነጥቦች አንዱ ይኸው 'ተጋላጭነትን መመዝበር' (abuse of vulnerability) መሆኑንም ይገልጻሉ።
ይኖሩበት ከነበረው ስፍራ ወደ ሌላ አካባቢ እንዲጓዙ መደረጉም ድርጅቱ በጠቋሚነት ካስቀመጣቸው ማሳያዎች አንዱ የሆነውን "የእንቅስቃሴ ገደብ" (Restriction of movement) የሚያሟላ እንደሚያደርገው አክለዋል።
ተጠያቂነት መቼ ይመጣል?
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ እየተፈጸመ መሆኑን ሲደርስበት "በአፋጣኝ መቆም አለበት" በሚል ግኝቱን ለተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ለእርሻ ጣቢያዎቹ ማቅረቡን አቶ ይድነቃቸው ይናገራሉ። ይህንን ተከትሎም ሕጻናትን ቡና ለቀማ ላይ የማሰማራት ተግባር "ሙሉ በሙሉ መቆሙ እንደተረጋገጠ" ያስረዳሉ።
"ትምህርት ቤቶቹ እና እርሻ ጣቢያዎቹ የነበራቸው ውል እንዲፈርስ ተደርጓል" የሚሉት አቶ ይድነቃቸው፤ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮም ተማሪዎቻቸውን ባሰማሩ ትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራን ላይ "አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን" እንደገለጸ ጠቅሰዋል።
ይህንን ድርጊት ለማስቆም "በረጅም፣ በአጭር ጊዜ እና በአፋጣኝ" የሚወስዷቸውን እርምጃዎች ለይተው ለኮሚሽኑ እንዲያቀርቡ ከተጠየቁት እርሻ ጣቢያዎች መካከልም "አብዛኛዎቹ" መላካቸውን ገልጸዋል።
አቶ ይድነቃቸው እንደሚያስረዱት፤ ኢሰመኮ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛን በተመለከተ እንዲተገበሩ ካቀረባቸው ምክረ ሀሳቦች አንዱ የሕግ ተጠያቂነት ነው። "የወንጀል ሕጋችን የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛን ወንጀል አድርጎ ያስቀምጠዋል፤ ምንም ጥያቄ የለውም" የሚሉት የሕጻናት መብቶች አስተባባሪው፤ ኮሚሽኑ በቀጣይ በሚያደርገው ክትትል የዚህን ምክረ ሀሳብ አፈጻጸም እንደሚመለከት ተናግረዋል።
ቢቢሲ ከፍትሕ ሚኒስቴር እና ከኦሮሚያ ክልል ፍትሕ ቢሮ መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም። የጅማ ዞን እና የሊሙ ኮሳ ዐቃቤ ሕግ ኃላፊዎች በበኩላቸው፤ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛን ስለተመለከተው የኢሰመኮ ግኝት እንደሚያውቁ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የጅማ ዞን ዐቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዘሀራ መሐመድ፤ የኢሰመኮ ሪፖርት ለሚመሩት መሥሪያ ቤት እንዳልቀረበ ነገር ግን "ስብሰባ ላይ" ስለጉዳዩ እንደሰሙ ተናግረዋል። ቢሯቸው ይህንን መነሻ በማድረግ በወረዳ ለሚገኙ ኃላፊዎች ስለ ሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ሥልጠና መስጠቱን አክለዋል።
የሊሙ ኮሳ ወረዳ ዐቃቤ ሕግ ኃላፊ የሆኑት ደቻስ አብዱልሰላም በበኩላቸው ሪፖርቱ ለመሥሪያ ቤቱ መቅረቡን ገልጸዋል። "ከወረዳው ጋር በመተባባር" የተማሪዎች ቡና ለቀማ እንዲቀር መደረጉን የሚናገሩት ደቻስ፤ በሊሙ ኮሳ ወረዳ ከሚገኙት ሦስት የሆራይዘን እርሻ ጣቢያዎች ጋር ንግግር ተደርጎ "መግባባት ላይ እንደተደረሰ" አስረድተዋል።
የጅማ ዞንም ሆነ የሊሙ ኮሳ ወረዳ ዐቃቤ ሕግ ኃላፊዎች ከዚህ ጋር በተያያዘ በሂደት ላይ ያለ ወይም የተከናወነ የሕግ ተጠያቂነት እንደሌለ ተናግረዋል። በሁለቱም ኃላፊዎች ዘንድ የሚነሳው ምክንያት ስለ ድርጊቱ በቀጥታ "አቤቱታ አልቀረበልንም" የሚል ነው።
የሕግ መምህሩ ዶ/ር ህሩይ፤ ይህ ሁኔታ የአገሪቱ ሕግ ሥርዓት ያለበት "ክፍተት" ነጸብራቅ እንደሆነ ይናገራሉ። በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ውስጥ የግዳጅ ሠራተኝነት "በግልጽ ወንጀል ሆኖ" አለመቀመጡን የሚያስረዱት ባለሙያው፤ ሕጉ ከዚህ ጋር ተቀራራቢነት ያላቸው ድርጊቶችን ለመመልከት "አቤቱታ መቅረብ" እንዳለበት እንደሚደነግግም ጠቅሰዋል።
"የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ከሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር ያልተያያዘ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛን በተመለከተ ካለበት ክፍተት አንጻር የእነዚህን ሰዎች ጉዳይ ከቀላል የግለሰብ የወንጀል ተጠያቂነት ይልቅ በሰብአዊ መብት ጥሰት የሕግ ማዕቀፍ ማየት የተሻለ ነው" ሲሉ ወደ ተጠያቂነት ያደርሳል የሚሉትን መንገድ ጠቁመዋል።
ዶ/ር ህሩይ፤ ለዚህ አቋማቸው የሚጠቅሰት አንዱ ምክንያት በሆራይዘን ፕላንቴሽንስ ተፈጽመዋል በተባሉት ሁለቱ ድርጊቶች ውስጥ ያለውን የመንግሥት መዋቅር ተሳትፎ ነው።
"ዋናው ተዋናይ የመንግሥት አካል ነው። መንግሥትን ደግሞ በአቤቱታ በሚቀርብ ቀላል ወንጀል መጠየቅ ትርጉም ያለው ለውጥ አያመጣም። በሰብአዊ መብት ጥሰት ማዕቀፍ የመንግሥትን ግዴታ አጉልቶ ማሳየት ለመፍትሔ የቀረበ መንገድ ነው" በማለት ሀሳባቸውን አብራርተዋል።