ከእስራኤል ጋር ለመደራደር ግብፅ የነበሩት የሐማስ ልዑካን ካለውጤት ካይሮን ለቀው ወጡ

ከእስራኤል ተወካዮች ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ የቀጥታ ድርድር ለማድረግ ግብፅ ካይሮ የነበሩት የሐማስ ልዑካን ውጤት ሳያገኙ ወደ መጡበት መመለሳቸው ተዘገበ።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ላለፉት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የቀጥታ ንግግር ከስምምነት ላይ ሳይደረስበት ቢቋረጥም፣ በተዘዋዋሪ የሚደረገው ድርድር ግን እንዳላበቃ ሐማስ አስታውቋል።

በሚቀጥለው ሳምንት ከሚጀመረው የረመዳን ጾም ጋር ተያይዞ ለ40 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ይደረጋል ተብሎ ቢጠበቅም ሳይሳካ ቀርቷል።

ጋዛ ውስጥ በተከሰተ የምግብ እጥረት ምክንያት የረሃብ አደጋ እያንዣበበ መሆኑን ተከትሎ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ዓለም አቀፍ ግፊት እየተደረገ ነው።

የግብፅ እና ኳታር አደራዳሪዎች እስራኤል ከእስር ቤቶቿ በምትለቃቸው ፍልስጤማውያን ምትክ እስራኤላውያን ታጋቾችን ሐማስ እንዲለቅ ስምምነት እንዲደረስ ጥረት ሲያደርጉ ቆይታዋል።

በስምምነቱ የሚለቀቁ በሐማስ እጅ በሕይወት ያሉ ታጋቾች ስም ዝርዝር እንዲሰጣት በመጠየቅ እስራኤል ተደራዳሪዎቿን ወደ ግብፅ አልላከችም ነበር።

ሐማስ ከስምምነት ለመድረስ እስራኤል የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እና ሠራዊቷንም ከጋዛ ከተማ ሙሉ ለሙሉ እንድታስወጣ ቢጠይቅም ተቀባይነት አላገኘም።

የሐማስ ልዑካን “የእስራኤልን ወረራ ለማስቆም እንዲሁም የተፈናቀሉትን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ለማስቻል እና እርዳታ እንዲደርስ” ለማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከአመራሮቻቸው ጋር ለመመካከር ሐመስ ጠዋት ከካይሮ ወጥተው ሄደዋል።

ለግብፅ መንግሥት ቅርብ የሆነው አል-ቃሄራ የተባለው የሳተላይት ቴሌቪዥን አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጠቅሶ ድርድሩ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚጀመር አመልክቷል።

የድርድሩ አለመሳካትን በተመለከተ ከእስራኤል መንግሥት በኩል የተሰጠ አስተያየት የለም።

የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሁለቱ ተደራዳሪዎች መካከል የተፈጠረው መሰናክል “ሊፈታ የሚችል ነው፤ ከስምምነት መደረስ ይችላል” ብሏል።

ለስምምነቱ መሳካት ከሐማስ 40 እስራኤላውያን ታጋቾች ሲለቀቁ፣ በምላሹ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከእስር እንዲወጡ የየስምምነት ሃሳብ ቀርቧል።

በአሁኑ ወቅት ከ130 በላይ ታጋቾች በሐማስ እጅ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ቢያንስ 30 የሚሆኑት ሳይሞቱ እንዳልቀሩ የእስራኤል ባለሥልጣናት ይናገራሉ።

በኅዳር ወር ለሳምንት ያህል ተደርጎ በነበረ ተኩስ አቁም አብዛኞቹ ሴቶች እና ልጆች የሚገኙባቸው 105 ታጋቾች በሐማስ ሲለቀቁ፣ እስራኤል ደግሞ 240 ፍልስጤማውያንን ከእስር ፈትታለች።

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ ወደ እስራኤል ዘልቆ በመግባት በፈጸመው ጥቃት 1,200 ሰዎችን በመግደል 253ቱን ደግሞ አግቶ መውሰዱን እስራኤል አሳውቃለች።

ይህንንም ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደችው ባለው ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ ከ30,800 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አሃዝ ያሳያል።