ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሐማስ ተወካዮች ለተኩስ አቁም ድርድር ካይሮ ገቡ፣ ከስምምነት ይደረሳል ተብሎ ይጠበቃል
አምስት ወራት ያስቆጠረውን የእስራኤል ጋዛ ጦርነትን ጋብ ለማድረግ በሚያስችል ንግግር ላይ ለመሳተፍ የሐማስ ልዑካን ግብፅ ካይሮ መግባታቸውን ተከትሎ አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረሳል የሚል ተስፋ ተፈጥሯል።
ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን እስራኤል “ከሞላ ጎደል” የተኩስ አቁም ስምምነቱን መቀበሏን ገልጸዋል።
አሁን ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው የስድስት ሳምንታት የተኩስ አቁም ስምምነት ተጨማሪ እስራኤላውያን ታጋቾች እና ፍልስጤማውያን አስረኞች ይለቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱ ወገኖች ተኩስ እንዲያቆሙ የሚደረገው ግፊት የተጠናከረው ባለፈው ሐሙስ ጋዛ ውስጥ እርዳታ በጫኑ ተሽከርካሪዎች ዙሪያ ከተሰበሰቡ ሰዎች መካከል ቢያንስ 112 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ነው።
የምግብ እርዳታ ለመቀበል በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ የእስራኤል ወታደሮች ተኩስ ከፍተዋል ሲል ሐማስ ከሷል። እስራኤል ግን ይህንን ክስ በማስተባበል ወታደሮቿ ሊወሯቸው በመጡ “በርካታ ሰግለሰቦች ላይ” መተኮሳቸውን በመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ መረዳቷን እና አብዛኞቹ ሰዎች የሞቱት በግርግር ምክንያት በተፈጠረ መረጋገጥ ነው ብላለች።
ከኳታር ጋር በመሆን በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚካሄደውን ንግግር የሚመሩት የግብፅ ባለሥልጣናት የሐማስ እና የአስራኤል ተወካዮች በድርድሩ ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
በሚቀጥሉት ከ24 አስከ 48 ሰዓታት ባለው ጊዜ ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ሐማስ መናገሩ ተዘግቧል። አንድ የቡድኑ ምንጭ ለግብፅ መገናኛ ብዙኃን ስምምነቱ የሚሰምረው እስራኤል የሐማስን ጥያቄዎች ከተቀበለች እንደሆነ ገልጿል።
አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለስድስት ሳምንታት በሚቆየው የተኩስ አቁም ማዕቀፍ ላይ እስራኤል “ስምምነት” ማሳየቷን ማረጋገጣቸውን ተከትሎ የተኩስ አቁሙ ዕውን እንደሚሆን ተስፋ ተጥሏል።
ባለፈው መስከረም 26 ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሞ 1,200 ሰዎችን በመግደል 253 የሚሆኑትን ደግሞ አግቶ ወደ ጋዛ ከወሰደ በኋላ እስራኤል ሐማስን ለማጥፋት መጠነ ሰፊ የምድር እና የአየር ጥቃቶችን እያካሄደች ነው።
ሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንደሚለው በእስራኤል ጥቃት አስካሁን 21,000 ህጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 30,410 ሰዎች መገደላቸውን፣ 71,700 መቁሰላቸውን እንዲሁም 7,000 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም።
የተኩስ አቁም እንዲደረግ ግፊቱ የበረታው የእርዳታ ድርጅቶች በሰሜናዊ ጋዛ የረሃብ አደጋ ስጋት እንዳንዣበበ ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ ነው።
የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል ኃላፊ ያን ኤግላንድ በጋዛ ለሦስት ቀናት ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ ለቢቢሲ ዛሬ እሁድ እንደተናገሩት፣ የከፋ ነገር ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
“ነዋሪዎች እየተራብን ነው፤ ልናልቅ ነው” በማለት እርዳታ ሲለምኑ እንዳዩ እና በሰሜን ጋዛ ረሃብ መኖሩን አመልክተዋል። አስራኤል እርዳታ እንዲገባ ስላለፍቀደች በስፍራው 300 ሺህ ሰዎች በፍርስራሾች ውስጥ በችግር ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ባለፈው ሐሙስ ከአንድ መቶ በላይ እርዳታ የሚጠብቁ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ፣ አሜሪካ ቅዳሜ ዕለት የመጀመሪያውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ከሦስት የጭነት አውሮፕላኖች ላይ በፓራሹት ወደ ጋዛ አውርዳለች።
እስራኤል በበኩሏ ዛሬ እሁድ ጠንካራ የአየር ድብደባዎችን በደቡባዊቷ የጋዛ ከተማ ኻን ዩኒስ ላይ መፈጸሟን ገልጸላች። ስለደረሰው ጉዳት ግን አስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
ትናንት ቅዳሜ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን በተጠለሉበት በደቡባዊ ጋዛ የራፋህ ካምፕ ላይ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 11 ሰዎች መገደላቸውን ሐማስ አስታውቋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ጥቃቱን “አስደንጋጭ” ያሉት ሲሆን፣ የእስራኤል ሠራዊት ደግሞ ጥቃቱ በእስላማዊ ጂሃድ ታጣቂዎች ላይ “ያነጣጠረ ነው” ብሏል።