ዴንማርክ ቁርዓን እና ሌሎች ኃይማኖታዊ ጽሁፎችን የሚያቃጥሉ ተቃዋሚዎችን ለማገድ መንገድ እየፈለገች ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዴንማርክ ቅዱስ ቁርዓንን እና ሌሎች ኃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ጽሑፎችን የሚያቃጥሉ ተቃዋሚዎችን ከጸጥታ እና ዲፕሎማሲ ስጋት አንጻር ለማገድ እያሰበች ነው።
ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ወሳኝ ቢሆንም እንደዚህ አይነቱ ተቃውሞ ግን የሚጠቅመው ጽንፈኞችን ከመሆኑም በላይ የጸጥታ ስጋትም ይፈጥራል ብሏል የዴንማርክ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ።
ከኤምባሲዎች ፊት ለፊት የሚደረጉ ተቃውሞዎችን ጨምሮ ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም ዴንማርክ ሕጋዊ አማራጮችን የምትወስድበትን መንገድ እያፈላለገች ነው።
የስዊድን ጠቅላይ ሚንስትርም ተመሳሳይ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሁለቱ የስካንዲኒቪያን አገራት ባለስልጣናት አወዛጋቢ ለሆነው የተቃውሞ ሰልፍ ፈቃድ ከሰጡ በኋላ ጫና በርትቶባቸው ሰንብቷል።
በተቃውሞ ሰልፉ የእስልምና ቅዱስ ቁርዓን እንዲቃጠል ተደርጓል። ይህ ደግሞ ከበርካታ የሙስሊም ወዳጅ አገራት ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል።
የሌሎች አገሮችን ባሕል እና እምነት የሚያጥላላ ቅስቀሳ የሚጎዳው ዴንማርክን በመሆኑ በአንዳንድ የቃውሞ ቦታዎች ላይ ርምጃ መውሰድ እና መሰል ድርጊቶችን ማስቆሙ ተገቢ መሆኑን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በመግለጫው አስታውቋል።
ይሁንና የዴንማርክ መንግሥት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ድርድር ውስጥ የማይገባ መሆኑን በመግለጽ ሁሉም ነገር ከሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ጋር የሚታይ ነው ብሏል።
መግለጫው አክሎም እንደዚህ አይነት አወዛጋቢ ተቃውሞዎች የዴንማርክን ዓለም አቀፋዊ ዲፕሎማሲ የሚያጠለሹ ናቸው ብሏል። በዚህም ምክንያት የቁርዓን መቃጠል ወዲያውኑ ማውገዙን ገልጿል።
ይህ ተቃውሞ “ዴንማርክ ለሌች አገራት ባሕል፣ ኃይማኖት እና ልምድ ማጥላላትን እና ማዋረድን የምትመርጥ አገር ሆና በብዙዎች ዘንድ እንድትሳል አድርጓታል” ብሏል መግለጫው።
በሌላ መግለጫ የስዊድኑ ጠቅላይ ሚንስትር ኡልፍ ክሪስተርሰን ከዴንማርክ ጋር ተመሳሳይ ሥራ ለመስራት እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። በትግበራው ዙሪያም ከዴንማርክ አቻቸው ጋር በቅርበት እየተወያዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በኢንስታግራም ገጻቸው “ሕጋዊ አማራጮችን ለመጠቀም ግምገማ እያደረግን ነው...የብሔራዊ ጸጥታችንን ለማጠናከር እና በስዊድን ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም የሚኖሩ ስዊድናዉያንን ደኅንነት ለመጠበቅ” በማለት ጽፈዋል።
የሁለቱ ጠቅላይ ሚንስትሮች መግለጫ የወጣው ባለፉት ሳምንታት በተደረጉ ተቃውሞዎች ቅዱስ ቁርዓን መቃጠሉን ተከትሎ በርካታ ታዋቂ ሰዎች በግልጽ ከተቹት በኋላ ነው።
ባለፈው ሰኔ አንድ ኢራቃዊ ክርስቲያን ስደተኛ በስቶክሆልም ማዕከላዊ መስጂድ ፊት ለፊት አንድ ኃይማኖታዊ ይዘት ያለው መጽሐፍን አቃጠለ።
ሰውየው ባለፈው ሳምንትም ቁርዓንን ለማቃጠል ፈቃድ አግኝቷል። ይህንን ተከትሎ በኢራቅ ባግዳድ ውስጥ የሚገኘው የስዊድን ኢምባሲ በተቃዋሚዎች ጥቃት ተፈጽሞበት በእሳት ተቃጥሏል። በዚህም ምክንያት ስዊድን ሰራተኞቿን ከኤምባሲ ለማስወጣት ተገዳለች።
ከዚያም በኋላ ሁለት የዴንማርክ ወግ አጥባቂ አክቲቪስቶች ኮፐንሃገን በሚገኘው የኢራቅ ኢምባሲ ፊት ለፊት ቅዱስ ቁርዓንን አቃጥለዋል።












