የኬንያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መንግሥት ቤተሰቤን እያስፈራራ ነው አሉ

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የኬንያ ቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መንግሥት ቤተሰባቸውን ማስፈራራት እንዲያቆም ጠየቁ።

ኡሁሩ ኬንያ መንግሥት በእድሜ የገፉ እናታቸውን እና ልጆቻቸውን እያስፈራራ መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በትናንትናው ዕለት ከወንድ ልጃቸው ቤት ሆነው ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ቃለ ምልልስ የሰጡት ኡሁሩ ኬንያታ በመንግሥት ድርጊት መቆጣታቸው በግልጽ ይታይ ነበር።

ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታም መንግሥት በልጃቸው ቤት ዙሪያ ፖሊስ ማሰማራቱ እንዳስቆጣቸው ተናግረዋል።

ይህ የፖሊስ ስምሪት የተፈጸመው የ90 ዓመት እናታቸውን ይጠብቁ የነበሩ የጸጥታ ሰዎች ከተነሱ ከቀናት በኋላ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።

ኬንያታ እንደሚሉት ሁለቱም እርምጃዎች በዚህ ሳምንት ከተደረገው ጸረ መንግሥት ተቃውሞ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ነው።

“ይህ መንግሥት የሚፈልገው ምንድን ነው ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ። ምክንያቱም እኔን የሚፈልጉኝ ከሆነ ዝም ስላልኩ ፈርቻለሁ ማለት አይደለም። እኔ ጋር ይምጡ። እናቴ ከምን ጋር ትገናኛለች? ልጆቼስ ምን የሚያገናኛቸው ጉዳይ አለ?” ብለዋል።

በዚህ ሳምንት በተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ራይላ ኦዲንጋ የተጠራው እና ለሦስት ቀናት የተካሄደው የተቃውሞ ሠልፍ በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የተካሄደ ሲሆን በአገሪቱ የተከሰተው የኑሮ ውድነት መናርን በመቃወም የተካሄደ ነበር።

ከዚህ በፊት የሚካሄዱ ጸረ መንግሥት ሠልፎችን መንግሥትን ለማስፈራራት በማሰብ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በገንዘብ ይደግፋሉ ሲል ይከስሳቸው ነበር።

በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት ኡሁሩ ኬንያታ

“ምን እንዳያደርጉ ነው የማስፈራራቸው? እኔ የስራ ዘመኔን የጨረስኩ ሰው ነኝ። ለምን አሳሳቢ ከሆኑትና ኬንያውያን ከሚያነሷቸው ጉዳዮች ጋር አይጋፈጡም? ሊጋፈጡ የሚገባቸው ይህንን ጉዳይ ነው። ሌላ ማምለጫ መፈለግ አያዋጣም።” ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ሥልጣናቸውን ያስረከቡት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ለአንድ ዓመት ያክል ምንም አስተያየት አልሰጡም ነበር።

አሁን በቤተሰቦቼ ላይ ተደረገ ያሉትን ማስፈራራት ተከትሎ “መንግሥት እኔ ጋር ጉዳይ ካለው ወደ ቤተሰቦቼ ሳይሆን መምጣት ያለበት ወደ እኔ ነው” ብለዋል።

“ዝም ብየ ቆይቻለሁ። ዝም አልኩ ማለት ግን ቤተሰቦቼን አልከላከልም ማለት አይደለም። ቤተሰቦቼን እጠብቃለሁ፣ እስከመጨረሻውም እከላከልላቸዋለሁ” ብለዋል የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ።

በዚህ ሳምንት በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ፖሊስ ከተለያዩ ሰልፈኞች ጋር ግጭት ውስጥ ገብቷል። በተቃውሞ ሰልፉ በዚህ ሳምንት ብቻ ቢያንስ 10 ሰዎች እንደተገደሉ ተዘግቧል።

ኡሁሩ ኬንያታ የኬንያ አራተኛው ፕሬዝዳንት ሲሆን ኬንያን ለአስር ዓመት ወይም ለሁለት የምርጫ ዘመን መርተዋል።

የነጻነት ታጋይ የነበሩት አባታቸው ጀሞ ኬንያታ፣ ኬንያ ከቅኝ ግዛት ነጻ ሆና በራሷ መሪ መተዳደር ስትጀምር ኬንያታ እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል።