ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቀሪና ድጋሚ ምርጫው “አስቻይ ሁኔታ የለም” በሚል ራሳቸውን አገለሉ

እናት እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፓርቲዎች ምርጫ ባልተካሄደባቸው እና በድጋሚ ምርጫ በሚካሄድባቸው አራት ክልሎች ሰኔ 9፤ 2016 ዓ.ም. ከሚካሄደው ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ባልተካሄደባቸው የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ 28 የምርጫ ክልሎች ምርጫ ለማካሄድ የካቲት 22፤ 2016 ዓ.ም. የጊዜ ሰሌዳ አውጥቷል።

ሰኔ 9 ይካሄዳል የተባለውን ምርጫ ለማካሄድ “አስቻይ ሁኔታ” የለም ያሉት ፓርቲዎቹ፤ አስቻይ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ ምርጫው እንዲዘገይ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

ፓርቲዎቹ ከሌሎች ሁለት ፓርቲዎች ጋር የካቲት 25 ለምርጫ ቦርድ በጻፉት ደብዳቤ “ትክክለኛ ምርጫ ለማድረግ የማያስችሉ” ያሏቸውን ነጥቦች አንስተው ቦርዱ ውሳኔውን ዳግም እንዲያጤነው ጠይቀዋል።

ሆኖም በቀሪና ድጋሚ ምርጫ በሚደረግባቸው አካባቢዎች እንንቀሳቀሳለን ያሉት ሁለቱ ፓርቲዎች ቦርዱ “ማስተካከያ” ባለማድረጉ በምርጫው አንሳተፍም ሲሉ አስታውቀዋል።

ፓርቲዎቹ ለውሳኔያቸው አገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ መሆኗ እንዲሁም የጸጥታ ችግርን እንደ ምክንያት አንስተዋል።

የእናት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ አያሌው የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመጥቀስ ወደ “ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓት” ስትመለስ ምርጫው መካሄድ አለበት ብለዋል።

ምርጫው ይካሄድባቸዋል በተባሉ ክልሎች ያለው አሁናዊ የሠላምና የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ አይደለም የሚሉት ፕሬዘዳንቱ ለምርጫው “አጃቢ” መሆን አንሻም ሲሉ ራሳቸውን ማግለላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ከቦታ ቦታ በኮንቮይ እየተንቀሳቀስሽ፤ በአጃቢ እየተንቀሳቀስሽ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም። ምርጫ ለማካሄድ የስነ-ልቦና ዝግጅትም ቢሆን ያስፈልጋል። ነጻ የሆነ አዕምሮ ያስፈልጋል። ይሄ በሌለበት ሁኔታ፤ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ እጩዎችን ማስመዝገብ፤ መስራት የሚቻልበት ሁኔታ የለም። የመራጮች ምዝገባ በእንደዚህ አይነት መልኩ ማካሄድ የሚቻልበት ሁኔታ የለም” ብለዋል።

ይህን ስጋታችንን ለምርጫ ቦርድ አቅርበናል ያሉት ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ ቦርዱ ሰጠን ባሉት ምላሽ ስጋታቸውን እንዳልተጋራ ገልጸዋል።

ምርጫውን ለማድረግ ‘ሁኔታዎች ምቹና ምርጫው ሊደረግ እንደሚችል፤ የምርጫው ሂደትም እየተካሄደ እንደሆነ’ የሚገልጽ ደብዳቤ ከቦርዱ ለፓርቲዎቹ እንደተላከላቸው ጠቅሰው፤ በምላሹ ባለመስማማታቸው ከምርጫው ተሳትፎ ራሳቸውን ማግለላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በእንደዚህ አይነት [ሁኔታ] አጃቢ፤ ተባባሪ ሆነን መሄድ አንፈቅድም” ብለዋል።

ከሁለቱ ፓርቲዎች በተቃራኒ ምርጫው “ዘገዬ” የሚሉና በአፋጣኝ እንዲካሄድ ሲወተውቱ የቆዩ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ።

የእናት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ “ሁሉም ፓርቲ የየራሱ ግምገማ አለው” በማለት የእይታ ልዩነት እንደሆነ አንስተው፤ “እኛ ግን ውጤታማ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም” የሚል ግምገማ ነው ያለን ብለዋል።

ቀሪና ድጋሚ ምርጫ ከአንድ ወር በኋላ በሚደረግባቸው አራት ክልሎች ፓርቲዎቹ ምን ያህል የምርጫ እንቅስቃሴ (Constituency) አላችሁ ብሎ ቢቢሲ የጠየቃቸው ፕሬዝዳንቱ፤ በሁለት ክልሎች “ትልቅ እንቅስቃሴ አለን” ሲሉ መልሰዋል።

“ከሶማሌና አፋር ክልሎች ካልሆነ በስተቀር በሌሎቹ ላይ [እንቅስቃሴ] አለን” ያሉት ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ፤ ሆኖም እንቅስቃሴያቸው በአካባቢዎቹ ነባራዊ ሁኔታዎች “አንጻራዊ” መሆኑን አንስተዋል።

ይህም በመሆኑ ለምርጫ ቦርድ ምርጫውን እንዲከልስ ጥያቄውን ማቅረባቸውን በመጥቀስ፤ ለእንቅስቃሴያቸው የአካባቢዎቹ ሁኔታ “ወሳኝ” እንደሆነ ተናግረዋል።

በ2013 ዓ.ም. በተደረገው ጠቅላላ ምርጫ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለሦስት ወንበሮች እጩዎችን አቅርቦ ነበር።

99 መቀመጫዎች ላሉት ክልሉ ምክር ቤት ደግሞ አምስት እጩዎችን ለአሶሳ ምርጫ ክልል አቅርቧል።

በደቡብ ክልል ስር የነበረውና በ2014 በሕዝበ ውሳኔ ክልል በሆነው ደቡብ ምዕራብ ክልል መስቃንና ማረቆ ምርጫ ክልሎች እናት ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት እጭዎችን አቅርቦ ነበር። ለክልል ም/ቤት ደግሞ ሦስት እጩዎችን ማስመዝገቡን የምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባ ዝርዝር ያሳያል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ቀሪና ድጋሚ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ክልሎች የእጩዎችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአፋር አምስት፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ 21፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ደግሞ አምስት እጩዎች ተመዝግበዋል።

ለክልል ምክር ቤት በአፋር 73፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ 198፣ በሶማሌ 22፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ደግሞ 10 እጩዎች ቀርበዋል።