በምርጫ 2013 ላይ ማኅበራዊ ሚዲያው ምን አይነት ሚና ነበረው?

በኢትዮጵያ የተካሄደውን ምርጫ በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ በርካታ ይዘቶች ተንሸራሽረዋል።

የምርጫ አስፈጻሚው ተቋም ሊታወቁ ይገባቸዋል ያላቸውን ጉዳዮች በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ሲያሰራጭ ቆይቷል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም እንዲሁ 'ምረጡን'ን ጨምሮ ከምርጫው ጋር የተገናኙ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ ተስተውሏል።

ማኅበራዊ ሚዲያ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አገራት የሚደረጉ ምርጫዎች አንዱ ገጽ እየሆነ መጥቷል። በዚህ ዓመት በተከናወነው የአሜሪካ ምርጫ ማኅበራዊ ሚዲያዎች አዎንታዊም አሉታዊም ሚና ነበራቸው።

ምርጫውን ተከትሎ በነበሩ ተግባራት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እስከመታገድ ደርሰዋል።

በሌላ በኩል በተያዘው ዓመት በኡጋንዳ በተካሄደው ምርጫ ሰበብ የማኅበራዊ ሚዲያና የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች እንዲታገዱ ተደርጓል። ምናልባት እነዚህ ክስተቶች ማኅበራዊ ሚዲያ ምርጫ ላይ ያላቸው ተጽእኖን ሊያመላክቱ ይችላሉ።

በኢትዮጵይ በተካሄደው ምርጫ ማኅበራዊ ሚዲያ 'እንደተፈራው' አልነበረም ይላሉ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ የነበራቸው የኮሚምዩኒኬሽን ባለሙያዎች። እንዴት?

'እንደተፈራው አልነበረም'

የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ባለሙያው አቶ ነጻነት ተስፋዬ ኢትዮጵያ ባካሄደችው ምርጫ ማኅበራዊ ሚዲያው አዎንታዊ አስተዋጾ እንደነበረው ያምናሉ። "እንደተፈራሁ አይደለም። ይሄንን ምርጫ በሚመለከት ሕዝብን ወደ አመጽ ወደ መሳሰሉት ነገር ሊገፋፉ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ ብዬ አስቤ ነበር። ነገር ግን ብዙ አላጋጠመም" ሲሉ ይገልጻሉ።

በምርጫው ላይ ማኅበራዊ ሚዲያ አሉታዊ አስተዋጾ ሊኖረው ይችላል የሚለውን ስጋት የመብቶች ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ዳይሬክተር በፍቃዱ ኃይሉም ይጋሩታል። "ከፍተኛ ሐሰተኛ መረጃና ምናልባት ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ነገሮችን ሊያስከስት ይችላል በሚል ብዙ ተሰግቷል" በማለት ያስረዳሉ።

"ቢያንስ ከዚህ ምርጫ ጋር በቀጥታ የሚገናኙ የግጭትና የሐሰተኛ መረጃ ስጋት ከተጠበቀው በታች በሆነ መጠን አልፏል ብዬ ነው የማም ነው"ም ሲል አክሏል።

ሆኖም ማኅበራዊ ሚዲያው በምርጫው ሂደት ላይ ከተጠበቀው በተቃራኒ ጉልህ ተጽእኖ ሳያሳርፍ ያለፈበት ምክንያት ላይ የባለሙያዎቹ ምልከታ የተለያየ ነው።

አቶ ነጻነት ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ማኅበራዊ ሚዲያውን "በኃላፊነት" እና "በአገራዊ ስሜት" መጠቀማቸውን ምክንያት ያደርጋሉ። ይህንንም ሲያስረዱ "እንዳውም ባልተለመደ ሁኔታ የአንዳንድ ፓርቲ መሪዎችና ዕጩዎች 'ተሸንፌያለሁ የሚቀጥለው ጊዜ ላይ እሞክራለሁ' ብለው እስከሚናገሩ ድረስ - በማኅበራዊ ገጻቸው አስተላልፈዋል። ማኅበራዊ ሚዲያው ሁኔታዎችን በማረጋጋት.... መሰልጠን ነው እስከሚባል ድረስ አስተዎጾ አድርጓል ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።

በፍቃዱ ደግሞ 'እንደተፈራው' ማኅበራዊ ሚዲያ ምርጫው ላይ አሉታዊ ጫና እንዳያደርስ ያደረጉ ሁለት ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ። የመጀመሪያው እሳቸው የሚመሩትን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ምርጫንና ማኅበራዊ ሚዲያን የተመለከቱ የግንዛቤ ማሳደጊያዎችን መሰራታቸው ነው።

ሌላኛው ደግሞ የምርጫው 'ቀዝቃዛ' መሆን ነው ይላሉ። "ምርጫው አገሪቱ ውስጥ ባሉ የተለያዩ የፖለቲካ ሁኔታዎች ምክንያት ሙሉ ትኩረት አላገኘም። ለምሳሌ የትግራዩ ጦርነት፣ ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ ዋና ዋና የፖለቲካ ድርጅቶች ከምርጫው መውጣታቸው" ምርጫው እንዳያጓጓ እና ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ያለውን ተሳትፎ እንዲቀንስ ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በዚህም ምክንያት 'የተፈራው' አልደረሰም። ፌስቡክም የድምጽ መሰጠት ሂደቱ ላይ ተጽእኖ ሊኖራቸው ይችላሉ ያላቸውን የሐሰተኛ አካውንቶችን ማስወገዱ የሚታወስ ነው።

የሐሰተኛ መረጃዎችና ምርጫው

ቢቢሲ ከድምጽ መስጫው ቀን ቀደም ብሎ ባሉት ቀናት ከምርጫው ጋር የተያያዙና እውነትነታቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገቡ መረጃዎችን አጣርቶ ባወጣው ዘገባ የተለያዩ ሐሰተኛ መረጃዎችን አጋልጧል።

ከተሰራጩ የሐሰት መረጃዎች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን የተመለከተውና ከብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ወጣ ከተባለው የሐሰት ድምጽ ውጪ የተፈጠሩ ሐሰተኛ መረጃዎች ጎልተው አልታዩም።

በፍቃዱ የሚመሩት የመብቶች ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ምርጫውና የማኅበራዊ ሚዲያን የተመለከቱ ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል።

ከምርጫው ጋር የተገናኙ ሐሰተኛ መረጃን የሚከታተል ቡድንም እንደነበር ያስታወሱት በፍቃዱ በምርጫው ቀን "ፌስቡክን ከመሳሰሉ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ሐሰተኛ መረጃዎችን ከስር ከስሩ ለማስወገድ ስንከታተል ነበር። ነገር ግን ብዙ የሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭት አልተፈጠረም" ሲሉም ገልጸዋል።

ከምርጫው ቀን ቀደም ብሎ ባሉት ጥቂት ቀናት "ምርጫ ተጀምሯል የሚሉ በሐሰተኛ ምስል የተደገፉ፤ እስካሁን ድረስ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ነው የሚሉ ማስረጃ የሌላቸው መረጃዎች እንዲሁም ደግሞ በፎቶ ሾፕ በተሰሩ ፎቶዎች አንድ የምርጫ ጣቢያ በአማጺ ቡድን ቁጥጥር ስር ውሏል ወይም ደግሞ ተቃጥሏል የሚሉ" የቅጠፈት ዜናዎች ነበሩ ሲሉ የሚያስረዱት በፍቃዱ ሆኖም "ብዙም ተጽእኖ አልፈጠሩም" በማለት ገልጸዋል።

በድኅረ ምርጫ ወቅትም ማኅበራዊ ሚዲያው የጎላ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳላሳደረ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል። እንደ አቶ ነጻነት ገለጻ ከምርጫው በኋላ ባሉት ጊዜያት የድምጽ መስጠት ሂደቱ በሰላም መጠናቀቅን ለመግለጽ በስፋት ውሏል።

ሆኖም "አንዳንድ ግለሰቦችና አክቲቪስት ነን የሚሉ ግለሰቦችም የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ በመፈለግ ሆን ብለውም ቢሆን፣ ገና ድምጹ እንኳን ተቆጥሮ ሳያልቅ እከሌ አሸነፈ እከሌ ወደ ፓርላማ ሊገባ ነው ሲሉ ነበር። አንድ ሁለት አይደለም በጣም በርካታ ናቸው። ይሄ ደግሞ ሕዝብ ያሳስታል....ይሄ ጥሩ አይደለም" ሲሉ አስረድተዋል።

ይህን ሁኔታ አስመልክቶ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ ውጤት የመግለጽ ኃላፊነት የቦርዱ መሆኑን ጠቅሶ ይህንን የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው። በሌላ በኩል ፓርቲዎች በድኅረ ምርጫ በድምጽ መስጫ ቀን ችግሮች ናቸው ያሉትንና በመልካምነት ያዩትን ለማስረዳት ማኅበራዊ ሚዲያው በስፋት ጥቅም ላይ እንደዋለም ጠቅሰዋል።

በፍቃዱ ደግሞ በድኅረ ምርጫ ወቅት ስላላው ሁኔታ ሲያብራሩ "ይጠበቁ የነበሩት ሐሰተኛ መረጃዎች እከሌ አሸነፈ ተጭበረበረ የሚሉ ነበሩ - ግን እስካሁን ባለው አዝማሚያ በየጣቢያዎቹ ያሉትን ከመግለጽና ከመገረም ባለፈ ተጭበርብሯል የሚልና ወደ ግጭት ሊያመራ የሚችል መንፈስ ያለው ሐሰተኛ መረጃ ወይም የቅስቀሳ እየተላለፈ አይደለም" ብለው ይህንን በአወንታዊነት አስቀምጠውታል።

ማኅበራዊ ሚዲያና የምርጫው ተሳታፊዎች

ማኅበራዊ ሚዲያ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችን ከዜጎች ጋር 'በቅርበት' እንዲገናኙ አግዟል ይላሉ - ባለሙያዎቹ። "ፓርቲዎች... መደበኛ ሚዲያ ላይ የሚገኙት ደቂቃ የተወሰነ ነው። ነገር ግን ማኅበራዊ ሚዲያ ሰፊ ጊዜ ወስደው ሐሳባቸውን ባሰኛቸው ቋንቋ የሚያስተላልፉበትን እድል ፈጥሮላቸዋል። ይሄ ቀላል ነገር አይደልም - በአሁኑ ምርጫ ላይ ያገኘነው ሰፊ ዕድል ነው" ያሉት አቶ ነጻነት ናቸው።

በሌላ በኩል "ሕዝቡ ደግሞ የዜግነት ጋዜጠኝነት [citizen journalism] መብቱን በደንብ ተጠቅሟል ብዬ አስባለሁ። ምርጫ ጣቢያ ላይ የሚታዩ ችግሮችን፤ በድምጽ አሰጣጥ የሚታዩ ችግሮችን፤ ሕገወጥ ተግባራትን በማጋለጥ ጭምር ለሚመከተው አካል በመጠቆም እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ረገድ ማኅበራዊ ሚዲያው አስተዋጾ አድርጓል" ብለዋል።

በተጨማሪም ለቀጣዩ ምርጫ 'ማኅበራዊ ሚዲያን እንዴት በበጎ መጠቀም እንደሚቻል' ትምህርት ሰጥቷል ሲሉ ያስረዱት የኮምዩኒኬሽን ባለሙያው ዜጎች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እንዲሄዱ መነሳሳትን የሚፈጥሩ መልዕክቶች እንዲተላለፉበትና ከምርጫ ቦርድ የሚመነጩ መረጃዎች በፍጥነት እንዲጋሩም አግዟልም ብለዋል። ምርጫ ቦርድም ጠቃሚ መረጃዎችን ወደ ምርጫው ተሳታፊዎች ለማድረስም እንደተጠቀመበትም እንዲሁ!

"ፓርቲዎች ከበፊቱ በተሻለ ለሕዝቡ ቅርብ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ከመራጮቻቸው ጋር ወይም ከደጋፊዎቻቸው ጋር በከፊል የሚገናኙበት መድረክ መፍጠሩ አወንታዊ ነው" ሲሉ የጠቀሱት ደግሞ በፍቃዱ ናቸው።

"አንዳንዶች ግን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባላቸው ድጋፍና በሚስተጋባ ድጋፍ ተታለው ካላቸው ድጋፍ በላይ ማኅበራዊ ድጋፍ ያለቻው [እንደሆነ] እንዲሰማቸው አድርጓል ብዬ አምናለሁ" ብለዋል።

ጳግሜ 1/2013 ዓ.ም የሚካሄደው ምርጫ ከማኅበራዊ ሚዲያ አኳያ የተለየ ትኩረት እንደሚፈልግም የተናገሩት በፍቃዱ ለዚህ መነሻ የሚያደርጉት ደግሞ ምርጫው የሚካሄድባቸው አብዛኞቹ አካባቢዎች በጸጥታ ስጋት ስር ያሉ በመሆናቸው ነው።

"አንዳንቹ ግጭት የማይቋረጥባቸው ናቸው። እነዚህ አከባቢዎች ላይ ውጥረቱ መጀመሪያውኑ መሬት ላይ ስላለ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይም እንቅስቃሴው የተጋጋለ ሊሆን ይችላል" ሲሉ አንስተዋል።

በአቶ ነጻነት የተገለጸውም ይሁን በበፍቃዱ የተብራራው የሰኔ 14/2013 ዓ.ም ምርጫ ማኅበራዊ ሚዲያ በሌሎች አገራት እንደተስተዋለው 'አስጊ ችግርን' ሳያስከትል ማለፍ ግን እርግጥ ይመስላል።