ኢሞጂዎች ተርጓሚ የማያስፈልጋቸው የዓለም ቋንቋ ይሆኑ ይሆን?

😊 ይህ ኢሞጂ ቢላክልዎት ምን ያስቅሃል/ሻል ሊሉ ይችላሉ። 😫 በዚህኛዋ ኢሞጂ እያንቀላፋሁ መሆኔን ላሳይ እችላለሁ።

ይሁን እንጂ እነዚህን ኢሞጂዎች በአጭር መልዕክትዎ መካከል ከመጠቀም አልፈው ዘለግ ያለ አረፍተ ነገር መመስረት ይችላሉ?

እኤአ በ2018 ላይ የብሪታኒያ ግንባር ቀደም የቴኒስ ተጫዋቹ አንዲ ሞሬ በሠርጉ ዕለት የተሰማውን ስሜት አንድም ቃል ሳይጠቀም በኢሞጂ ብቻ መልዕክቱን ትዊትር ሰሌዳው ላይ በማስፍር ዓለምን አስደንቆ ነበር።

ከሠርግ ዝግጅት ወደ ቤተ ክርስቲያን የተደረገው ጉዞ፣ የቀለበት ሥነ ሥርዓቱ፣ የፎቶ ፕሮግራሙ፣ ደግሱ፣ ፍቅር እና እንቅልፍ የተካተቱበት የሞሬ መልዕክት በኢሞጂ የታዩበት ነው።

ይህም አዲስ የዓለማችን መግባቢያ ቋንቋ እየተወለደ መሆኑን ያሳየ ነበር።

የምትስቀዋን ኢሞጂ የፈጠሩት እነ ቪቪያን ኢቫንስ ኢሞጂ ዓለም ሊግባበት የሚችል ቋንቋ ነው ይላሉ።

ኬቲ ብሮኒ የገበያ ጥናት የሥነልቦና ባለሙያ ናት።

በአውሮፓውያኑ በ2017 ለአንድ የትርጉም ድርጅት ኢሞጂዎችን ለመተርጎም ተቀጠረች።

ኢሞጂዎች ዓለም ሊግባባቸው የሚችል ቋንቋ ከሆኑ ለምን አስተርጓሚ አስፈለገ?

ብሮኒ አንደምትለው አሁን ወረት ሆኖብን በኢሞጂ እንጠቀም እንጂ የዓለም ቋንቋ መሆን አይችሉም። እንደውም እንደማሟያነት ነው ሊጠቅሙን የሚችሉት ስትል ታስረዳለች።

ኢሞጂዎች አጭር መልዕክት ስንልክ፣ በአካል ስናወራ የፊታችን ገጽታ ሊቀየር እንደሚችለው ሁሉ ስሜታችንን ለመግለጽ ይጠቅሙናል።

አንዳንዴ በአጫጭር መልዕክቶቻችን ውስጥ ኢሞጂዎችን ካልቀላቀልን የጻፈው ሰው ጥሩ ባልሆነ ስሜት ወይንም ደግሞ በትዕዛዝ መልክ የተናገረን ሊመስለን ይችላል።

ይሁን እንጂ ይህንን ለማስቀረት የምንጠቀማቸው ኢሞጂዎች አሉታዊ ጎን ሊኖራቸው ይችላል።

ሁላችንም ስልካችን ውስጥ ተመሳሳይ ኢሞጂዎች ቢኖሩንም ስንጠቀም ልንል የምንፈልገው ጉዳይ ግን በባህል፣ በቋንቋ በእድሜ እና በመሳሰሉት ጉዳዩች የተለያየ ሊሆን ይችላል።

ለምሳሌ የአውራ ጣት ምልክትን ማሳየት በምዕራባውያን ባህል አንድ ንግግር ትክክል ወይንም አግባብ መሆኑን ሊያሳይ ይችላል።

ነገር ግን በግሪክና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ይህ ምልክት ስድብ ነው።

የመላዕክ ኢሞጂን ማሳየት አሁንም ለምዕራብውያኑ የዋህነትን ሲያሳይ፣ ቻይና ውስጥ ግን የሞት ፍርሃት ምልክት ሆኖ ነው የሚያገለግለው።

የማጨብጨብ ምልክት የደስታን፣ ማበረታታትን እና ጎሽ የማለት መልዕከትን የሚያስተላልፍ መሆኑን በርካቶቻችን ብንቀበለውም ለቻይናውያን ግን ወሲብ የመፈፀም ምልክት ነው።

በ2017 በተደረገ ጥናት በረመዳን ወቅት ሙስሊሞች ስሜታቸውን ለመግለጽ ምን ዓይነት ኢሞጂ ይጠቀማሉ የሚለውን በማየት ፕሪስሞጂ ኢሞጂ የዓለም ቋንቋ መሆኑን አመላካች ለማግኘት ሞክሯል።

ትዊተር ላይ ከተጻፉ አጫጭር መልዕክቶች ሙስሊሞች በረመዳን ወቅት እንግሊዘኛ፣ ጀርመንኛ፣ ስፓኒሽና የቱርክ ቋንቋ የሚናገሩ ሙስሊሞች ቀይ የልብ ቅርጽ ያለው ኢሞጂ ሲጠቀሙ፤ አረብኛ፣ ኡርዱ እና ፋርስ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ደግሞ የግማሽ ጨረቃን ምልክት ሲጠቀሙ ተስተውለዋል።

'አመሰግናለሁ' ለማለት የምንጠቀመው የእጅ ምልክት ደግሞ ከእነዚህ ኢሞጂዎች በይበልጥ ጥቅም ላይ ውሎ ነበር።

ይሁን እንጂ አረብኛ የሚናገሩ ሰዎች በዘጠነኛ ደረጃ ላይ ነው የተጠቀሙት። በኡርዱ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ደግሞ ጨርሶውኑ አልተጠቀሙትም።

በሙስሊም ባህል ውስጥ እጅን በዚህ መልኩ ለምስጋና ማጋጠም ፀሎትን ለማሳየት ላይጠቅም ይችላል።

በምዕራባውያን ዘንድ ግን ትልቅ የሆነ ሐይማኖታዊ ጠቀሜታ አለው።

ጃፓን ውስጥ ግን ከሐይማኖት ጋር ሳይሆን፣ 'አመሰግናለሁ' 'እባክዎን' የሚለውን ቃል ይተካል።

ስለኢሞጂ ማስተማር አያስፈልገውም

ኢሞጂ ስሜትን የምንገልጽበት ቋንቋ ስለሆነ ለመልመድ በጣም ቀላል ነው።

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከ45 ዓመት ሰው ይልቅ የስድስት ዓመት ልጅ ይህንን የቴክኖሎጂ ቋንቋ መጠቀም ይችላል።

ለወደፊት ሰዎች ቋንቋን ትተው በኢሞጂ መነጋገር ይችሉ ይሆን? እነደ ፕሮፌሰር ቪቪያንስ ኢቫንስ ከሆነ ኢሞጂ መጥቶ የሚሄድ ፋሽኑ የሚያልፍበት ሳይሆን የዲጂታል ተግባቦትን ሙሉ ያደረገ ቋንቋ ነው።

በተግባቦታችን መካከል ኢሞጂዎችን መጠቀም ግንኙነታችንን መልካም ያደርገዋል።

በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ መንደር ሲሊከን ቫሊ እኛን የሚመስል የሮቦት ኢሞጂ እየሰራ ነው።

ይህ ኢሞጂ ወደ ሌሎቹ ሲላክ ስሜታችንን በእንቅስቃሴ ጭምር ለሌሎች ያሳያል።

አሁንም ታድያ የባህል ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ ኢሞጂዎች የዓለምን ሕዝብ ከማራራቅ ይልቅ የማቀራረብ አገልግሎትን ይሰጣሉ ብላ ታምናለች ብሮኒ።

ስለ ኢሞጂዎች በጥቂቱ ማወቅ ይፈልጋሉ?

  • የመጀመሪያው ኢሞጂ በ1999 ጃፓን ውስጥ ሺጌታካ በተባለ ግለሰብ ተፈጠረ። እርሱም የስልክ መልዕክት ተጠቃሚዎች አጭር እና ቀላል የሆነ መልዕክቶች እንዲያስተላልፉ በማሰብ ነው።
  • ብዙ ኢሞጂዎች ደስታን የሚገልፁ ናቸው።
  • በቀን ስድስት ቢሊዮን የሚሆኑ ኢሞጂዎች ይላካሉ። ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ 76 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ስማርት ስልኮችን ይጠቀማል። ከእነዚህ 80 በመቶ ያህል ኢሞጂ ይጠቀማሉ።
  • በቀን ስድስት ቢሊየን ከሚላኩ ኢሞጂዎች መካከል 70 በመቶ ያህሉ ስሜትን የሚገልጹ ናቸው።
  • ጥቅም ላይ ከሚውሉ ኢሞጂዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የምትላከው ኢሞጂ የደስታ እንባ የምታነባዋ ነች።
  • ሁለተኛ ላይ እየሳቀች አይኖቿ ላይ የልብ ቅርጽ ያላት ናት።

የትኞቹ አገራት የትኛውን ኢሞጂ አዘውትረው ይጠቀማሉ?

  • ካናዳ የአብዛኛዎቹ የዓይነምድር ኢሞጂ ይጠቀማሉ
  • አውስትራሊያ የመጠጥ እና የመዝናናት
  • ፈረንሳይ የልብ ቅርጽን ከሁሉም አገራት በተለየ በአራት እጥፍ ይጠቀማሉ
  • አረብኛ ተናጋሪ አገራት የአበባ ኢሞጂ በብዛት ይጠቀማሉ
  • እንግሊዞች ደግሞ የቢራ ኢሞጂን በብዛት ይጠቀማሉ