ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጉግል በአውሮፓውያኑ 2022 በብዛት ‘ጉግል’ የተደረጉ ቃላትን ይፋ አደረገ
የቴክኖሎጂ ኩባንያው ጉግል እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያኑ 2022 ዓመት ተጠቃሚዎች በብዛት የፈለጓቸውን ቃላት ይፋ አደረገ።
ኩባንያው በስፋት ‘ጉግል’ ከተደረጉ ቃላት መካከል ቀዳሚው ‘ዎርድል’ ነው ብሏል።
‘ዎርድል’ ጆሽ ዋርድል በተባለ የሶፍትዌር መሃንዲስ ከአንድ ዓመት በፊት የተፈበረከ የቃላት ጨዋታ ሲሆን፣ ሰዎች በስድስት ሙከራዎች የዕለቱን ቃል በማወቅ የጨዋታው አሸናፊ ይሆናሉ።
በርካቶች የዕለቱን የዎርድል ቃል ለማወቅ ‘ዎርድል’ የሚለውን ቃል ‘ጉግል’ ስለሚያደርጉ ቃሉ በብዛት ጉግል ላይ የተፈለገ አድርጎታል።
በዓለም ላይ ያጋጠሙ ትልልቅ ክስተቶችም በብዛት ጉግል ተደርገዋል።
የዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ ሞት በዓመቱ በስፋት በጉግል ተጠቃሚዎች ፍላጎት ከታዩባቸው ቀዳሚ አምስት ክስተቶች መካከል አንዱ ሆኗል።
ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ያለችው አገር የ‘ዩክሬን’ ስም ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ ጉግል የተደረገ ቃል ሆኗል።
ከታዋቂ ግለሰቦች መካከል ደግሞ በጉግል ላይ በቀዳሚነት የተፈለገው ጆኒ ዲፒ ሆኗል። ተዋናይ እና ሙዚቀኛው ጆኒ ዲፕ ከቀድሞ ባለቤቱ ጋር የነበረው የፍርድ ቤት ክርክር የበርካቶች ቀልብ ስቦ ነበር።
ዊል ስሚዝ ደግሞ ጆኒ ዲፕን በመቀጠል ጉግል ላይ በዓመቱ በበይነ መረብ ላይ የተፈለገ (ሰርች) የተደረገ እውቅ ሰው ሆኗል።
ዊል ስሚዝ ከወራት በፊት ኮሜዲያን ክሪስ ሮክን በአካማዲ አዋርድስ ላይ በአደባባይ በጥፊ ከተማታ በኋላ ሚሊዮኖችን አጀብ አሰኝቶ ነበር።
የሜዳ ቴኒስ ተጫዋቿ ሴሬና ዊሊያምስ ደግሞ ከስፖርተኞች ስሟ በብዛት ጉግል ላይ የተፈለገች አትሌት ሆናለች።
ሴሬና ከሜዳ ቴኒስ ተጫዋችነቷ ‘ጡረታ’ እንደምትወጣ ካስታወቀች በኋላ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃሃን ላይ ሰፊ ሽፋን አግኝታ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ በተለይ በአሜሪካ ያሉ የጉግል ተጠቃሚዎች በፍጥነት ሃብት የሚጋበስበትን መንገድ ሲፈልጉ ነበር።
እንደ ‘የሎተሪ ጨዋታዎች’፣ ‘ሜጋ ሚሊዮንስ’ እና ‘ፓወርቦል ነምበርስ’ የሚሉት ቃላት በስፋት ተፈልገዋል ተደርገዋል።