የኦሮሚያው ግጭት እርዳታ የሚጠብቁ ሰዎችን ቁጥር እንደጨመረው ተመድ ገለጸ

በኦሮሚያ ክልል እየተባባሰ የመጣው ግጭት የሰብአዊ እርዳታ የሚጠባበቁ ነዋሪዎችን ቁጥር እንደጨመረው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) አስታወቀ።

በክልሉ የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ ባሻገር የመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ላይም ጫና እንደተፈጠረ ኦቻ ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።

በተባባሰው ግጭት ምክንያት በቅርቡ ምን ያህል ሰዎች እንደተፈናቀሉ ለማወቅ አዳጋች ቢሆንም፣ የክልሉ ባለሥልጣናት እስካሁን ባወጧቸው አሐዞች መሠረት በምዕራብ ወለጋ ዞን 106,000 ነዋሪዎች እንዲሁም በሆሮ ጉዱሩ 116,000 ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል።

“በክልሉ ተደራራቢ ቀውሶች መፈጠራቸው የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። ግጭቶችን ተከትሎ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉም ነው” ሲል ኦቻ ኅዳር 28 ቀን 2015 ዓ. ም. ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።

ባለፉት ቀናት በምዕራብ ኦሮሚያ ምሥራቅ ወለጋ ዞን ብሔር ተኮር በሆኑ ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ መሆናቸው ሲገለጽ ቆይቷል።

በተለይም በምሥራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ በሚገኙት ጊዳ አያና እና ኪራሙ ወረዳዎች ባለፉት ቀናት በነበሩ ጥቃቶች በርካቶች ሲገደሉ በመቶ ሺዎች መፈናቀላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች እና ጥቃቶች ሳቢያ እየደረሱ ያሉ ግድያዎች፣ የአካል ጉዳቶች እና መፈናቀሎች እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደሆኑ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኅዳር 28/2015 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

የሰሞነኛው ግጭት ዋነኛ ተሳታፊዎች “ሸኔ እና የአማራ ታጣቂዎች” ናቸው ያለው ኢሰመኮ፤ በክልሉ ዞኖች በታጣቂ ቡድኖቹ በተፈጸሙ ጥቃቶች በመቶዎች የሚገመቱ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን እና ቁጥራቸው የማይታወቅ ሰዎች ደግሞ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ገልጿል።

ኦቻ በበኩሉ፣ ከሰሞኑ በተነሳው ግጭት ምን ያህል ሰዎች እንደተፈናቀሉ ገና ባይታወቅም፣ እስካሁን በእነዚህ አካባቢዎች የተፈናቀሉና እርዳታ የሚጠባበቁ ሰዎችን ቁጥር ከፍ እንደሚያደርገው ጠቅሷል።

ክልሉ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች ተጨማሪ መጠለያዎችን እያዘጋጀ እንደሆነ በሪፖርቱ ተገልጿል።

የእርዳታ አቅርቦት እና እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እንደማይመጣጠን የገለጸው ኦቻ፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን እርዳታ ከሚፈልጉ19,000 አባወራዎች መካከል 1,100 ብቻ ድጋፍ እንዳገኙና በምሥራቅ ወለጋ ዞን እርዳታ ከሚፈልጉ 30,000 አባወራዎች 9,337 ብቻ ድጋፍ እንዳገኙ አስታውቋል።

በበጀት እጥረት እና እርዳታ ማሳለጫ መንገዶች በማጣት፤ ኦቻ ኦሮሚያን ጨምሮ ሰብአዊ እርዳታ በሚያደርስባቸው አካባቢዎች ድጋፍ ከሚፈልጉ ሰዎች ግማሽ ያህሉን እንኳን ማዳረስ እንዳልቻለ በሪፖርቱ አካቷል።

በክልሉ በተለይም በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች የሕጻናት መቀንጨር መከሰቱንም የኦቻ ሪፖርት ያመለክታል።እስካሁን 563,000 ሕጻናት ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን፣ 1.96 በመቶው በከፋ ሁኔታ እንዲሁም 18 በመቶው በተወሰነ መጠን መቀንጨር ገጥሟቸዋል።

የኮሌራ እና ኩፍኝ ወረርሽኝ ያለውን ችግር እንዳባባሱት እንዲሁም የተመጣጠ ምግብ እጥረት ላይ የቤተሰቦች አለመኖር ክፉኛ በድርቅ የተጎዱ ወረዳዎች ያሉ ሕጻናትን ለአደጋ ማጋለጡን ኦቻ አክሏል።