ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን ከጸረ- መንግሥት ተቃውሞዎች ጋር በተያያዘ የመጀመሪያውን የሞት ቅጣት ፈጸመች
ኢራን በአገሪቱ ከተቀሰቀሰው ጸረ-መንግሥት ተቃውሞዎች ጋር ጥፋተኛ ሆኖ አግኘቸዋለሁ ያለችውን ግለሰብ በሞት መቅጣቷን አስታወቀች።
ሞህሴን ሸካሪ ዛሬ ሐሙስ ኅዳር 29/2015 ዓ.ም. ማለዳ በስቅላት መቅጣቱን የመንግሥት ሚዲያ ዘግቧል።
ሞህሴን የሞት ቅጣቱ ተፈጻሚ የሆነበት አብዮታዊ ፍርድ ቤት “በአምላክ ላይ ጠላትነት” በማሳየት የጥፋተኛነት ውሳኔ ካስተላለፈበት በኋላ ነው።
ሞህሴን መስከረም አጋማሽ ላይ የቴህራንን ዋና ጎዳና በመዝጋት እንዲሁም የልዩ ኃይል አባል የሆነውን ግለሰብ በገጀራ በማቁሰል “ሁከት ፈጣሪ” የሚልም ክስ ቀርቦበታል።
ሞህሴን ይግባኝ ብሎ የነበረ ቢሆንም የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሞት ቅጣቱን ማጽናቱን የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
አንድ የሰብዓዊ ተሟጋች እንዳለው የፍርድ ሂደቱ ቀልድ እንደነበር ወቅሷል።
መቀመጫውን በኖርዌይ ያደረገው የኢራን የሰብአዊ መብቶች ዳይሬክተር ማህሙድ አሚሪ ሞጋዳም በትዊተር ገፃቸው እንዳስታወቁት የኢራን ባለስልጣናት ለዚህ ተግባራቸው አለም አቀፍ እርምጃ እስካልተወሰደባቸው በስተቀር የተቃዋሚዎች ግድያ በየቀኑ እንደሚፈጸምም ያላቸውን ስጋት አጋርተዋል።
የኢራን የፍትህ አካላት በመስከረም አጋማሽ ላይ ከተጀመረው ተቃውሞ ጋር ተያይዞ 11 ግለሰቦች የሞት ቅጣት እንደተፈረደባቸው አስታውቀዋል።
ለዚህ ተቃውሞ መነሻ የሆነው የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ የራስ መሸፈኛዋን በትክክል ባለመልበስ የሂጃብን ጥብቅ ደንብ ጥሳለች በሚል በስነ ምግባር ፖሊሶች ቁጥጥር ስር ውላ ህይወቷ ማለፉን ተከትሎ ነው።
በሴቶች መሪነት እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ በሃገሪቱ 31 ግዛቶች ወደ 160 ከተሞች የተዛመተ ሲሆን ከ1979 አብዮት በኋላም መንግሥትን እየናጠ ያለ ከፍተኛ ተቃውሞም ነው ተብሏል።
የኢራን መሪዎች በሀገሪቷ የውጭ ጠላቶች ያነሷሷቸው ሁከቶች ናቸው በማለት የጸጥታ ሃይሎች "ቆራጥ እርምጃ እንዲወስዱ" ትእዛዝ አስተላልፈዋል።
ከተቃውሞውም ጋር ተያይዞ ቢያን 475 ተቃዋሚዎች ተገድለዋል፣ 18 ሺህ 240 ግለሰቦች ደግሞ መታሰራቸውን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የዜና አገልግሎት ህራና ዘግቧል። በተጨማማሪም 61 የጸጥታ ኃይሎች መሞታቸውንም አስታውቋል።