የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 6,000 የተማሪ ቪዛዎችን ሰረዘ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ6,000 በላይ የዓለም አቀፍ ተማሪዎችን ቪዛ የአሜሪካ ሕግን በመጣስ እና ከተገቢው ጊዜ በላይ በመቆየት በሚል መሰረዙን ለቢቢሲ ገለፀ።

ቢሮው "አብዛኞቹ" ጥሰቶች የተፈጸሙት ጥቃት በመፈጸም ሲሆን፣ በተፅዕኖ ስር [ዕጽ እና መጠጥ] ሆኖ ማሽከርከር፣ ስርቆት እና "ሽብርተኝነትን መደገፍ" ይገኙበታል ብሏል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እርምጃ የተሰማው የትራምፕ አስተዳደር በሰነድ አልባ ስደተኞች እና በዓለም አቀፍ ተማሪዎች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በቀጠለበት ወቅት ነው።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ "ሽብርተኝነትን መደገፍ" ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ባያብራራም፣ የትራምፕ አስተዳደር ፍልስጤምን በመደገፍ ተቃውሞ ባሰሙ አንዳንድ ተማሪዎች ላይ ፀረ ሴማዊ ባህሪ አሳይተዋል በሚል ወንጅሏቸዋል።

ከተሰረዙት 6,000 የተማሪ ቪዛዎች ውስጥ 4,000 ያህሉ የአገሪቱን ሕግ በመጣሳቸው መሰረዛቸውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።

ሌሎች ከ200 እስከ 300 ቪዛዎች ደግሞ "በ አይኤንኤ 3ቢ (INA 3B) ስር በተፈጸመ ሽብርተኝነት" ተሰርዘዋል ሲል የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ገልጾ "የሽብር ተግባር" የሰውን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ወይም የአሜሪካን ሕግ የሚጥስ ድርጊት መሆኑን በሰፊው የሚገልፀውን ኮድ ጠቅሷል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የትራምፕ አስተዳደር ለዓለም አቀፍ ተማሪዎች የሚሰጡ የቪዛ ቀጠሮዎችን አቁሟል።

በሰኔ ወር ቀጠሮ መያዝ ዳግም ሲጀመር ሁሉም አመልካቾች የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶቻቸውን ለተጠናከረ ምርመራ ክፍት እንዲያደርጉ እንደሚጠይቁ አስታውቋል።

"በዜጎች፣በባህል፣በመንግሥት፣በተቋማት ወይም ዩናይትድ ስቴትስ በተመሰረተችባቸው መርሆች ላይ የጥላቻ መልዕክቶች ካሉ እንደሚመለከቱ" ተናግሯል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሠራተኞችም "የውጭ አገር አሸባሪዎችን እና ሌሎች የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋቶችን የሚደግፉ፣ ወይም ሕገወጥ ፀረ ሴማዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃትን የሚፈጽሙ" ላይ ማጣሪያ እንዲያደርጉ ታዝዘዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በግንቦት ወር ለሕግ አውጭዎች እንደተናገሩት ከጥር ወር ጀምሮ "በሺዎች የሚቆጠሩ" የተማሪ ቪዛዎች ተሰርዘዋል።

ሩቢዮ ግንቦች 20 ለሕግ አውጪዎች "የቅርብ ጊዜውን ቁጥር አላውቅም፣ ግን ብዙ የምንሰራው ነገር ሊኖረን ይችላል" ብለዋል።

አክለውም "እዚህ በእንግድነት ተገኝተው የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችንን እየረበሹ ያሉትን ሰዎች ቪዛ መሰረዙን እንቀጥላለን" ብለዋል።

ዲሞክራቶች የትራምፕ አስተዳደር የተማሪ ቪዛን ለመሰረዝ የሚያደርገውን ጥረት በመቃወም ድርጊቱ በሂደት ላይ ያለ ጥቃት መሆኑን ገልፀውታል።

እአአ በ2023-24 የትምህርት ዘመን ከ210 በላይ አገራት የመጡ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ዓለም አቀፍ ተማሪዎች በአሜሪካ ኮሌጆች ተመዝግበዋል ሲል ኦፕን ዶርስ የተሰኘው የውጭ አገር ተማሪዎች መረጃን የሚሰበስብ ድርጅት አስታውቋል።