ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ለኢትዮጵያውያን የምትሰጠውን ቪዛ ቆይታ ወደ ሦስት ወር አሳጠረች
በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠው ቪዛ የቆይታ ጊዜ ወደ ሦስት ወር ማጠሩን አስታወቀ።
ኤምባሲው ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 3/2017 ዓ.ም. በኤክስ ገፁ ባሰፈረው መረጃ፤ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስደተኛ ባልሆኑ የቪዛ አመልካቾች ላይ ባደረገው የፖሊሲ ለውጥ ምክንያት ውሳኔው መተላለፉን ገልጿል።
በአዲሱ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፖሊሲ መሠረት፤ "ከሐምሌ 1/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ለኢትዮጵውያን የሚሰጠው ቪዛ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል እና የሦስት ወር ቆይታ" እንደሚኖረው አስታውቋል።
ኤምባሲው በዚሁ የኤክስ ገጽ ልጥፉ ላይ ከሐምሌ 1/2017 ዓ.ም. በፊት የተሰጡ ቪዛዎች ባሉበት እንደሚቀጥሉ ገልጿል።
ለንግድ እና ለጉብኝት ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን የሚያገኙት ቪዛ "B1" እና "B2" በሚለው ምድብ ውስጥ ይካተታል።
እስካሁን በነበረው አሰራር በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገቡ ተጓዦች የሚያገኙት ቪዛ ለሁለት ዓመት የሚቆይ ነበር። በተጨማሪም የቪዛው የቆይታ ጊዜ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በተደጋጋሚ ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ያስችል ነበር።
አሁን ይፋ የተደረገው ፖሊሲ የቪዛውን የቆይታ ጊዜ ወደ ሦስት ወር ከማሳጠር በተጨማሪ በአንድ ቪዛ ተደጋጋሚ ወደ አገሪቱ መግባትን ከልክሏል።
በአዲሱ ፖሊሲ ቪዛ የሚያገኙ ተጓዦች የቆይታ ጊዜ ባይጠናቀቅም እንኳ ከአሜሪካ ከወጡ በኋላ በዚያው ቪዛ ተመልሰው መግባት አይችሉም።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተለያዩ አፍሪካ አገራትን ቪዛ የቆይታ ጊዜን ወደ ሦስት ወራት ማሳጠሩን ይፋ ያደረገው በትናንትናው ዕለት ነበር። ይህ ውሳኔ ከተላለፈባቸው ሀገራት መካከል ናይጄርያ እና ጋና ይገኙበታል።
ስደተኛ ያልሆኑ እና ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ግዛቷ የሚገቡ ናይጄርያውያን እና ጋናውያን የሚሰጣቸው ቪዛ የሦስት ወር ቆይታ ብቻ እንደሚኖረው እና አንድ ግዜ ብቻ ለመግባት የሚያገለግል እንደሚሆን ገልጿል።
በዚሁ መሰረትም የሁለቱ አገራት ተጓዦች ወደ አሜሪካ የሚገቡበትን የቪዛ የቆይታ ጊዜ እና ቅድመ ሁኔታ ላይ ለውጥ አድርጋለች።
አሜሪካ የቪዛ አሰጣጥ ፖሊሲዋን በመከለሷ ምክንያት ለጉብኝት፣ ለትምህርት እንዲሁም ለሥራ ወደ አሜሪካ የሚያቀኑ መንገደኞች የሚያገኙት የሦስት ወር ቪዛ ብቻ ይሆናል ማለት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የያዙት ቪዛ አንድ ግዜ ብቻ መግባት የሚያስችላቸው ይሆናል።
አሜሪካ የቪዛ ፖሊሲዋን ዳግም የከለሰችው የትራምፕ አስተዳደር እአአ ሰኔ 5/2025 የደህንነት ስጋት ናቸው ባሏቸው 12 አገራት ዜጎች ላይ የጉዞ ክልከላ ማድረጓን ካስታወቀች በኋላ ነው።
ከእነዚህ 12 አገራት መካከል ቻድ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኤርትራ፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን ይገኙበታል።
ከሳምንት በኋላም ኢትዮጵያን ጨምሮ የ36 አገራት ዜጎች አሜሪካ እንዳይገቡ ለማገድ ሃሳብ እንዳለው የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጣዊ ሰነድን ጠቅሰው መገናኛ ብዙኃን ዘግበው ነበር።
ጋና፣ ናይጄሪያ እና ኢትዮጵያ እገዳው ሊጣልባቸው ይችላል ከተባሉ አገራት መካከል ተጠቅሰውም ነበር።
በግንቦት መጨረሻ፤ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በውጭ አገሮች የሚገኙ ኤምባሲዎቹ የተማሪዎች የቪዛ ቀጠሮ እንዳይሰጡ አዝዞ ነበር።
የአመልካቾችን የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የማጣራት ሂደት ለማስፋት በዝግጅት ላይ እንዳለ ያስታወቀው አስተዳደሩ፤ ለተማሪዎች የቪዛ ቀጠሮ እንዳይሰጥ በጊዜያዊነት አግዶ ቆይቷል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ መልዕክት በሰፈረበት ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በተላከ ማስታወሻ ላይ እገዳው "ተጨማሪ መመሪያ እስኪወጣ ድረስ" ይቆያል ተብሏል።
አስተዳደሩ የተማሪዎች አመልካቾች የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን የማጣራት ስራ አጠናክሮ የሚሠራ ሲሆን ይህም በኤምባሲዎች እና በቆንስላ ጽ/ቤቶች ላይ ትልቅ አንድምታ እንደሚኖረው ተገልጿል።