ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዩክሬን የኒውክሌር ጣቢያ ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ተመለሰ
በዩክሬን ግዙፉ ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት መጀመሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ድርጅት አስታወቀ።
በአካባቢው በደረሰው ጥቃት ከማመንጫው ጋር የተገናኙት የኤሌክትሪክ መስመሮች ተጎድተዋል ተብሏል።
ስድስቱም የጣቢያው ማብላያዎች ሊዘጉ ተቃርበው ነበር ተብሏል።
ማብላያዎችንን ለማቀዝቀዝ እና የመጥፋት አደጋን ለመከላከል ኃይል ያስፈልግ ነበር።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ድርጅት በሩሲያ ኃይሎች የተያዘው ጣቢያ ሁኔታ መሻሻል ቢታይበትም አሁንም አሳሳቢ ነው ብሏል።
ከድርጅቱ የተውጣጣ ቡድን በአውሮፓ ትልቁ ወደ ሆነው የዛፖሪዝሂያ ኒውክሌር ጣቢያ ከሳምንታት በፊት ተጉዟል።
ጉዞው የተደረገው በቦታው የነበረውን ጥቃት ተከትሎ ከዩክሬን እና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፍተሻ እንዲደረግ ጥሪ በመቅረቡ ነበር።
በደቡብ-ምስራቅ ዩክሬን በሚገኘው ጣቢያ ላይ ለደረሰው ጥቃት ሩሲያ እና ዩክሬን አንዱ አንዱን ተጠያቂ እያደረጉ ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ድርጅት ከመጀመሪያው ፍተሻ በኋላ ሁኔታውን ለመከታተል በቋሚነት እንደሚቆይ አስታውቋል።
በስፍራው የተገኙት የቡድኑ አባላት ቅዳሜ ዕለት ከተጎዱት አራት ዋና ዋና የኤሌክትሪክ መስመሮች አንዱ ተስተካክሎ ኤሌክትሪክ ከብሔራዊ ቋት ማስገኘት መቻሉን አውቀዋል ሲል ድርጅቱ በትዊተር ገፁ ላይ አስፍሯል።
በሌላ በኩል በምስራቃዊ ዩክሬን በአይዝዩም የጅምላ መቃብሮች በመገኘታቸው የአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንት የጦር ወንጀሎችን ስለመፈጸሙ እንዲያጣራ ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ጥሪ አቅርበዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ አስከሬኖች በከተማይቱ መውጫ ላይ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ተቀብረው ተገኝተዋል። ከቦታው የሩስያ ጦር በማፈግፈጉ በዩክሬን ቁጥጥር ስር በመዋሉ ነው ሊታወቅ የቻለው።
ከሟቾቹ በርካቶቹ ሲቪሎች ሲሆኑ ሴቶች እና ህጻናት እንደሆኑም ተነግሯል።
ዩክሬን የጦር ወንጀሎች ተፈጽመዋል ብዬ አምናለሁ ብላለች።