ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የህወሓት የሰላም ጥሪ እና የመንግሥት ዝምታ
የትግራይ ኃይሎች በአፍሪካ ኅብረት የሚመራው የሰላም ድርድር አካል ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ህወሓት የሰላም ድርድር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ያሳወቀው በመንግሥት እና በትግራይ አማፂያን መካከል ድጋሚ ጦርነት ካገረሸ በኋላ ነው።
ከዚህ ቀደም መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ በሁለቱ መካከል ያለው ጦርነት ለአምስት ወራት ያክል ጋብ ብሎ ነበር።
በዚያ ወቅት ሁለቱ ኃይሎች ወደ ሰላም ድርድር ይመጣሉ የሚል ተስፋ ቢፈነጥቅም እንደ አዲስ ባገረሸው ግጭት ምክንያት ድርድሩ የከሸፈ መስሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በተናጠል የተኩስ አቁሙ ወቅት በአፍሪካ ኅብረት መሪነት አሸማጋይነት ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑንና ለዚህም ተደራዳሪዎች መሰየሙ አይዘነጋም።
ህወሓት በበኩሉ በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከሚመራውን የአፍሪካ ኅብረት ድርድር ይልቅ በኬንያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት አሸማጋይነት ለመነጋገር እንደሚችል ገልጾ ነበር።
የት እንደራደር? ማንስ ያደራድረን? በሚል አለመስማማት ውስጥ የነበሩት ሁለቱ ኃይሎች ድጋሚ ወደ ጦርነት ገብተዋል።
ጦርነቱ እንደ አዲስ ከተጋጋለ በኋላ ህወሓት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ የአፍሪካ ኅበረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የተለያዩ መንግሥታት ደግፈውታል።
ነገር ግን ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ግን ይህን የሰላም ጥሪ ተከትሎ በይፋ የተባለ ነገር የለም።
ለመሆኑ የህወሓት የሰላም ጥሪ አንድምታ ምንድነው? መንግሥትስ ለሰላም ጥሪው እስካሁን በይፋ ምላሽ ለመስጠት ያልፈለገው ለምን ይሆን?
የህወሓት መግለጫ አንድምታ
የትግራይ ኃይሎች በ2015 የመጀመሪያው ቀን ባወጡት መግለጫ አዲሱ ዓመት በተለይ በትግራይ ተኩስ የማይሰማበት፤ መሠረታዊ አገልግሎቶችና ሰብዓዊ እርዳታ የሚቀርቡበት እንዲሆን ምኞት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በአደራዳሪነታቸው እንደሚቀጥሉ ከቀናት በፊት ይፋ አድርጓል።
በሌላ በኩል አዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፤ የቀድሞው አለቃቸው ኡሁሩ ኬንያታ የኢትዮጵያ መንግሥትንና ህወሓትን ለማቀራረብ ሲያደርጉ የነበረውን ጥረት እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ምንም እንኳ ለህወሓት “የሰላም ጥሪ” ምላሽ ባይሰጥም ከአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣን ጋር የተገናኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት በሚመራ የሰላም ድርድር ላይ ለመሳተፍ “ቁርጠኛ ነው” መሆኑን መሆኑን ተናግረዋል።
“የህወሓት የሰላም ጥሪ በሁለት ምክንያቶች አከራካሪ ሆኗል” ይላሉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማኅበር ኃላፊ አቶ ያሬድ ኃይለማርያም።
“አንደኛው፤ ይህ የሰላም ጥሪ የታወጀው ‘አክቲቭ’ የሆነ ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ወቅት መሆኑ ነው። የሰላም ጥሪው በወጣ ዕለት አሊያም ማግስት ይመስለኛል በተለያዩ ግንባሮች ህወሓት ጥቃት ሰንዝሯል የሚሉ ዜናዎች ሲሰሙ ነበር። የሰላም ጥሪና ጦርነት አብሮ እንዴት ይሄዳል? የሚለው አንዱ አሳሳቢ ነገር ነው።”
ኃላፊው፤ ሁለተኛው አከራካሪ ጉዳይ “ቡድኑ የሰላም ጥሪ ያወጀው ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበት ነው። የሰላም ጥሪው ልባዊ አይደለም፤ ጊዜ መግዣ እንጂ” የሚለው ግምት ነው ይላሉ።
“እኔ ግን ምክንያታቸው በጦርነት ሜዳ የበለጠ ጉዳት ላለማስተናገድም ይሁን ለሌላ፣ ጥሪውን በአትኩሮት ነው የምመለከተው” ይላሉ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ “ማንኛውም ወገን ለሰላም ዕድል እንስጥ፤ እኔ ተኩስ አቆማሉሁ ካለ ከዚያ በኋላ የሚመጣው ነገር ለሰላም ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ ያሳያል” ይላሉ።
“ስለዚህ ህወሓት በእርግጥም ለሰላም ዝግጁ ነው የሚለውን ከዚህ በኋላ ባሉት ጊዜያት የምናየው ይሆናል። እኔ ግን ይህን ጥሪ ውድቅ አላደርገውም።”
ከ30 ዓመታት በላይ ለተባበሩት መንግሥታት ያገለገሉት የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያና የቀድሞ ዲፕሎማቱ ባይሳ ዋቅወያም በተመሳሳይ “እኔ በበኩሌ እንነጋገር ማለትን እንደ ሽንፈት አላየውም” ይላሉ።
ምሁሩ “ግጭት አሊያም ጦርነት የፖለቲካ ውድቀት ነው። ፖለቲካ ላይ መስነፍ ነው ግጭት የሚያመጣው” ይላሉ።
ሁለቱ ወገኖች መጀመሪያም ቢሆን ወደ ግጭት ማምራታቸው ስህተት ነው የሚሉት አቶ ባይሳ “ኢትዮጵያ ውስጥ በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ ችግርን መፍታት እንደ ድክመት ነው የሚታየው” ባይ ናቸው።
“አሁን የትግራይ ኃይል እንነጋገር ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ‘ደክመዋል፤ ለዚህ ነው ሰላም የሚሉት። እንሰብራቸዋለን’ የሚል ነገር ይሰማል።”
ዲፕሎማቱ ጨምረውም “ይህን የሚለው መንግሥት ብቻ ሳይሆን ተምረዋል የምትላቸው ትላልቅ ሰዎችም ናቸው” ይላሉ።
“ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የሰውን ሕይወት ያድናል፤ ኢኮኖሚው እንዳይጎዳ ያደርጋል፤ መሠረተ ልማትን ከጥፋት ይታደጋል፤ ስለዚህ ሊበረታታ ይገባዋል” በማለት መንግሥት ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።
የመንግሥት ዝምታና ቅደም ሁኔታ
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ “የመንግሥት ዝምታ አንድምታው ምንድነው? የሚለውን መገመት በጣም ከባድ ነው” ይላሉ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መንግሥት የሰላም ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የሚካሄድ ከሆነ ለመሳተፍ ቁርጠኛ ነው ከማለታቸው ውጪ መንግሥት ለህወሓት ጥሪ ይፋዊ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።
ምንም እንኳ የመንግሥት ዝምታ ግራ አጋቢ ቢሆንም “ከህወሓት በኩል የቀረበውን ጥሪ መጠራጠር አሊያም እምነት አለማሳደር ሊሆን ይችላል” በማለት አቶ ያሬድ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
“ምናልባት መንግሥት ከህወሓት የሚጠብቀው ተጨማሪ ነገር ያለ ይመስለኛል። አሁን ጦርነት ካለበት ቦታ ህወሓት እንዲወጣ ፈልጎ አሊያም ተኩስ እንዲቆም ፈልጎም ሊሆን ይችላል።”
አቶ ያሬድ አክለው “አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቻቸው ህወሓት ትጥቅ መፍታት አለበት የሚል አስተያየት ሲሰጡ አይተናል” ይላሉ።
“እስካሁን መንግሥት ምንም አለማለቱ ከህወሓት ጋር ያለው አለመተማመን ጉዳይ ይመስለኛል። ነገር ግን መንግሥት ምንም ሐሳብ ሳይሰጥ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ማለቱ ከባድ ነው።”
ህወሓት “የሰላም ጥሪ” ካወጀ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ “በምዕራብ ትግራይ ጉዳይ አንደራደርም” ሲሉ ተደምጠዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንደ አዲስ ከማገርሸቱ በፊት ሁለቱ ኃይሎች ወደ ሰላም ድርድር ሊመጡ ይችላሉ በተባለበት ወቅት በአንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች እንዳልተስማሙ ሲነገር ነበር።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማኅበር ኃላፊው፣ የቅደመ ሁኔታ ጉዳይ የእርቅ ሂደቱን ያበላሸዋል ብለው ያምናሉ።
“አደራዳሪው የአፍሪካ ኅብረት ይሁን የሚሉት ስምምነቶች እንዳሉ ሆነው የቀድሞው የትግራይ ክልል ግዛቶች ይመለሱ የሚሉ ነጥቦች ሰንቅረዋል። መሰል ቅደመ ሁኔታዎች የእርቅ ሂደቱን ከወዲሁ ያበላሸዋል ብዬ አምናለሁ።”
አቶ ያሬድ ምክንያታቸውን ሲያስረዱ፤ “በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው በንግግር፣ በውይይት መፈታት ያለባቸው ጉዳዮች ወደ ውይይቱ ለመግባት እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጥ የለባቸውም” ይላሉ።
ቅደመ ሁኔታ መሆን ያለበት ማን ያደራድረን? የት እንደራደር? መቼ? ማን ታዛቢ ይሁን? የሚሉት ነጥቦች እና ተኩስ አቁም ናቸው የሚሉት አቶ ያሬድ፣ በአንዳንድ ግጭቶች ተኩስ ቆሞ ድርድር እንደሚደረግ፣ በሌሎች ቦታዎች ደግሞ ተኩስ አቁሙ ወረቀት ላይ ሰፍሮ የጣሰ እንዲቀጣ እንደሚደረግ ያነሳሉ።
ስለዚህ “ሁለቱ ወገኖች እርቅ የሚፈልጉ ከሆነ ይህንን ቢያስቡበት፣ ካልሆነ ግን ወደ ድርድር የሚደረገው ጉዞ ይደናቀፋል።”
ኦባሳንጆ ወይስ ኡሁሩ?
ተሰናባቹ የኬንያ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ደማቅ ሥነ-ሥርዓት መንበራቸውን ለዊሊያም ሩቶ አስረክበዋል።
ሩቶ በበአለ ሲመታቸው ዕለት ባደረጉት ንግግር የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ እና በታላላቅ ሐይቆች ቀጠና ሰላም ለማምጣት ሲያደርጉት የነበረውን ጥረት እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋል።
የአህጉራዊው ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሰላም ለማምጣት ያደረጉት ጥረት ፍሬያማ አልሆነላቸውም።
የትግራይ ኃይሎች፤ ኦባሳንጆ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አላቸው ባሉት የቀረበ ግንኙነት ሲተቿቸው መቆየታቸው አይዘነጋም።
በአሜሪካ የህወሓት ተወካይ የሆኑት አቶ ዮሐንስ አብርሃ፤ “ከመንግሥት ጋር የሚደረገው ድርድር በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት መሆኑ ቅር ባያሰኘንም፣ ኅብረቱ ተወካይ አድርጎ የሾማቸው ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን ግን እንቀበላቸዋለን አላልንም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ስለዚህ አሁንም በህወሓት በኩል ሽምግልናውን በሚመሩት ኦባሳንጆ ላይ የተነሳው ጥያቄ እንዳለ በመሆኑ፣ ምናልባትም ኅብረቱ ከዚህ አኳያ ሌላ አማራጭ እንዲፈልግ ሊያደርገው ይችላል።
ለዚህ ደግሞ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጉዳዩን በቅርበት በመከታተልና በሁለቱም ወገኖች አመኔታን በማግኘት በኩል ብቸኛው ተመራጭ ሊሆኑ ይችላሉ።
የአፍሪካ የሰላም ጉዳዮች ተንታኝ አብዱላሂ ቦሩ ሃለኬ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት ከዚህ ቀደም ጀምረውት የነበረውን እንዲቀጥሉ አዲሱ ፕሬዝዳንት መወሰናቸው “መልካም ብቻ ሳይሆን ስትራቴጂያዊ ነው” ይላሉ።
በሰላም ድርድሩ ጉዳይ ከህወሓት በኩል የሚነሳው ዋነኛው ጉዳይ የአደራዳሪ ወገኖች ተዓማኒነት በመሆኑ “ኡሁሩ የኅብረቱን ወክለው አደራዳሪ ሆነው የሚመጡበት ዕድል ካለ፤ ሁለቱም ወገኖች በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ጥረት ላይ እምነታቸውን ለማሳደር ይችላሉ፤ ሂደቱንም ያቀለዋል” ይላሉ አቶ ያሬድ ኃይለማሪያም።
ኬንያታ ወደ ሽምግልናው መድረክ የሚመጡ ከሆነ ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች እንደሚኖሩ የሚጠቅሱት አብዱላሂ ኢትዮጵያ እና ኬንያ እንደ ወንድማማች አገራት ቢተያዩም በአካባቢው የበላይነት ለመያዝም የሚፎካከሩ በመሆናቸው ሊንጸባረቁ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ ይላሉ።
ስለዚህም “የፌዴራሉ መንግሥት የሰላም ሂደቱን መቆጣጠር ይፈልጋል። ኦባሳንጆ የሚመሩት ሂደትም ከዚህ ፍላጎታቸው ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። ነገር ግን በኬንያታ በኩል የሚኖረውን በቁጥጥራቸው ሥር ማድረግ አይችሉም” ይላሉ።
አዲሱ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን በኢትዮጵያና በታላላቅ ሐይቆች አካባቢ ሰላም ለማውረድ የጀመሩትን ጥረት እንዲቀጥሉ ማድረጋቸውን፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ እና የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ጆሴፍ ቦሬል አድንቀው ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ገልጸዋል።
የኬንያታን አሸማጋይነት ህወሓት ብቻ ሳይሆን የባሕረ ሰላጤው አገራት እና አሜሪካ እንደሚደግፉት የሚያነሱት አብዱላሂ፣ ስለዚህ ሃሳቡ የአዲሱ ፕሬዝዳንት ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ድጋፍ እንዳለው ይጠቅሳሉ።
ነገር ግን የአፍሪካ ኅብረት ለአንድ ዓመት ያህል ልዩ ተወካዩ አድርጎ የሰየማቸውን የኦባሳንጆን የውክልና ጊዜን ባለፈው ሳምንት ማራዘሙን የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ስለዚህም ኡሁሩ ኬንያታ የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በድርድር ለመቋጨት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚኖራቸው ሚና ከየትኛው ወገን አኳያ እንደሆነ አስካሁን አልታወቀም።
በተጨማሪም መንግሥት እና ህወሓት መቼ እና የት ለድርድር እንደሚቀመጡ በእርግጠኝነት የሚታወቅ ነገር የለም።