ገበሬ ለመሆን ከአየርላንድ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው በረከት ወርቁ

በረከት ወርቁ ወላይታ ውስጥ በ600 ሄክታር መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬ ታመርታለች።

እራሷን ‘ታታሪዋ ገበሬ’ ‘በረከት ገበሬ’ እያለች በመጥራት ትታወቃለች።

ግብርና እጅግ የተከበረ ሙያ እንደሆነ የምትገልጽበት መንገድ ነው።

ኢትዮጵያ መጥታ እርሻ ከመጀመሯ በፊት ነዋሪነቷ አየርላንድ፣ ደብሊን ነበር።

የሦስት ልጆች እናት የሆነችው በረከት፣ ተወልዳ ያደገችው ሐዋሳ ነው።

ከመንግሥት ሠራተኛ ቤተሰብ ነው የተወለደችው።

የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እዚያው ሐዋሳ ነው ያጠናቀቀች።

ከዚያም ለሥራ ወደ ደቡብ ሱዳን አቀናች።

በደቡብ ሱዳን መከላከያ ውስጥ ሠርታለች። በአገሪቱ ምክር ቤት መዝገብ ቤትም አገልግላለች።

ከደቡብ ሱዳን ደግሞ ወደ ኡጋንዳ ሄደች።

በኡጋንዳ ካቬንዲሽ ዩኒቨርስቲ ሕግ እየተማረች በኡጋንዳ እና በደቡብ ሱዳን መካከል ለሰባት ዓመታት እየተመላለሰች መሥራት ቀጠለች።

አየርላንዳዊ ባለቤቷን የተዋወቀችውም እዚያው ነው።

ከዚያም ወደ አየርላንድ ተጓዘች።

ኑሮዋንም በመዲናዋ ደብሊን አደረገች።

“እርሻ የጀመርኩት በአባቴ ምክንያት ነው”

በረከት ወደ ግብርና የገባችው በአባቷ ምክንያት እንደሆነ ትናገራለች።

“. . .አባቴ ታቦር አንደኛ ደረጃ አስተማሪ ነበር። መምህራን ኮሌጅ እና ማንዴላ የርቀት ትምህርትም ያስተምር ነበር። በእረፍት ጊዜውም የእርሻ ሥራን ያሳየን ነበር። ሰፊ እርሻ ሳይሆን 2 ሄክታር፣ 3 ሄክታር የቤተሰብ መሬት ላይ ነበር የሚያሳየን. . .”

አባቷ ክረምት ላይ ከሥራ እረፍት ሲያገኙ ወደ ሱሉልታ ይዘዋቸው ይሄዱ እንደነበር ታስታውሳለች።

ከአባቷ ጋር አብራ እርሻ ውስጥ በመሥራት ነበር ክረምቷን የምታሳልፈው።

በጋ ላይ ደግሞ ቤት ውስጥ የተለያዩ እጽዋቶችን ችግኝ ያፈላሉ።

“. . .የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ምሩቁ አባታችን የነበረው የአስተማሪ ደመወዝ እኛን ለማሳደግ በቂ አልነበረም። ስለዚህ ቤታችን ችግኝ ማፍላት፣ ቅርጻ ቅርጽ መሥራትና ሌሎችም ብዙ ሥራዎች እንሠራ ነበር።”

ሁሉም የቤተሰብ አባል የዚህ ሥራ አካል ነበር።

ከስድስቱ የቤቱ ልጆች፣ ኋላ ላይ ታናሿ የሥነ ጥበቡን ዓለም ስትቀላቀል ታላቋ ደግሞ ወደ ግብርናው ገብቷል።

እሷም የግብርና ፍቅር ያደረባትም በዚህ ወቅት እንደሆነ ታስታውሳለች።

“ከአገር ቤት ከወጣሁ በኋላም ዐይኔ የሚያየው እርሻ ብቻ ነበር” የምትለውም ለዚሁ ነው።

ሌላ ሥራ ላይ ሆና ራሱ አትክልት ትተክላለች።

ደቡብ ሱዳን መከላከያ ውስጥ እና ምክር ቤት በምትሠራበት ወቅት ግቢውን ታስውብ እንደነበር ትናገራለች።

በስተመጨረሻ ደግሞ ጠቅልላ ወደ ግብርናው ገባች።

“ከሙሴቪኒ ወንድም ጋር እርሻ እሠራ ነበር”

በረከት ወደምትወደው ሙያ ከመግባቷ በፊት ከአገር ቤት የወጣችው ቤተሰቧ ችግር ላይ ስለወደቀ ነበር።

ወቅቱንም እንዲህ ታስታውሳለች።

“ሕይወት ከባድ ነበር። አባታችን የጨጓራ ካንሰር ታመመብን። ካንሰር ምን እንደሆነ እንኳን አናውቅም ነበር። በሰዓቱ የነበረንን ንብረት በጠቅላላ ሸጠን ነበር። እኔ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ልጅ ነበረኝ። ያለምንም ረዳት ልጅን እያሳደጉ፣ ኑሮን ተቋቁሞ መግፋት ቀላል አይደለም። ወደ ደቡብ ሱዳን የመሄድ ዕድል ሳገኝ፣ መውጣቱን መረጥኩ። ሥራ ተወዳድሬ ሳገኝ ደቡብ ሱዳን ሄድኩ።”

ደቡብ ሱዳን አንድ ዓመት ከሠራች በኋላ የወታደሮች ትጥቅ ለመግዛት ወደ ኡጋንዳ ስትመላለስ ነበር የዛሬውን ባለቤቷን የተዋወቀችው።

የአየርላንድ ልዩ ኃይል ካፕቴን የሆነው ባለቤቷ ያኔ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጠባቂዎች አሠልጣኝ ነበር።

እርሻ በኡጋንዳ የመጀመር አጋጣሚው የተፈጠረላትም በዚያ ወቅት እንደሆነ ትናገራለች።

“ከኢትዮጵያ በፊት እርሻ የጀመርኩት ኡጋንዳ ውስጥ ነው። ከሙሴቪኒ ታናሽ ወንድም ጄኔራል ሳሊም ሳሌህ ጋር እርሻ እሠራ ነበር። እሳቸው ሰፊ መሬት ስለነበራቸው በእርሳቸው መሬት ላይ ነበር የምሠራው።”

በረከት ቻይና፣ ሞዛምቢክ፣ ጣልያን፣ ታንዛኒያ ከቆየች በኋላ ነው ኑሮዋን በአየርላንድ ያደረገችው።

ወደ ኢትዮጵያ መመለስ

ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው ከአሥር ዓመታት በፊት ነው።

ያኔ የእራሷ መሬት ስላልነበራት መቂ መሬት ተከራይታ ነበር እርሻ የጀመረችው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ትመላለስ ነበር።

2008 ዓ. ም. ላይ የእራሷን 40 ሄክታር የእርሻ መሬት አገኘች።

“. . .አየርላንድ እያለሁ ነው ስለ ኢትዮጵያ ማሰብ የጀመርኩት። እኛ አገር ጥሩ አፈር አለን፤ በዓለም ትልቁ ወንዝ [ከአማዞን ቀጥሎ] እኛ ጋር ነው፤ የአየር ንብረታችን ጥሩ ነው፤ እንደፈለግን ተንቀሳቅሰን መሥራትም እንችላለን። ታዲያ ለምን በደንብ አልተጠቀምንበትም? የሚለውን አሰብኩ።”

ደብሊን ሳለች ከትንንሽ እርሻዎች ላይ ትልልቅ ምርት ሲገኝ ተመልክታለች። ያውም በዓመት ስምንቱ ወራት ቀዝቃዛ በሆኑበት አገር።

በረከትን ይገርማት የነበረው አየርላንዶች በዚያ የአየር ንብረት አምርተው ከእራሳቸው ተርፈው ወደ ውጭ አገራት ምርታቸውን መላካቸው ነበር።

ኢትዮጵያ ባለው አቅም ከዚህ የላቀ ሥራ መሥራትና ልዩነት መፍጠርም እንደሚቻልም አምና ወደ አገር ቤት ተመለሰች።

ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰች በኋላ መጀመሪያ ላይ አርሲ ውስጥ መሬት አግኝታ አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት ጀመረች።

ነገር ግን በ2009 ዓ. ም. በኦሮሚያ ተከስቶ ከነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ እርሻዋ ሙሉ በሙሉ እንደወደመባት ትናገራለች።

ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ሀባብ፣ ዝኩኒ ወዘተ. . . አንድ ዙር ካመረተች በኋላ በሁለተኛ ዙር ቲማቲም እና ቃርያ ተክላ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለመላክ እየተዘጋጀች ሳለ ነበር ውድመቱ የደረሰው።

“ወደ ውጪ የሚላከው ምርት ላይ ምንም ዓይነት የአፈር ማዳበሪያ እና መድኃኒት አልጠቀምም። በወቅቱ ኮሮላ የሚባል የሕንድ የአትክልት ዘር ነበር። ከሕንድ መጥቶ ከተተከለ በኋላ ምርቱን የሚቀበሉትም ሕንዶች ነበሩ። ከላዩ ላይ አንድ ፍሬ ሳልበጥስ ነው እርሻው የወደመው” ስትል ታስታውሳለች።

በወቅቱ መጋዘኗ ወድሟል፣ ማዳበሪያዋ ተዘርፏል፣ ምርቶቿም ተሰርቀዋል።

“በጣም አስደንጋጭ ነበር። ምንም ጉዳት ቢደርስብኝም በአገር ላይ ተስፋ መቁረጥ ቀላል አይደለም። አርሲ ያለውን መሬት እንደነበረው ትቼ ወደ ደቡብ ክልል ቀይሬ መሥራት ጀመርኩ” ትላለች በረከት።

ግብርና በወላይታ

ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ለኢንቨስትመንት አንድ ሚሊዮን ዩሮ ይዛ ነበር።

ያለማችው እርሻ ሲወድም ጠቅላላ ኪሳራ ደረሰባት።

ወደ አየርላንድ ተመልሳ በድጋሚ ገንዘብ ለማግኘት ስትሞክር ረዥም ጊዜ ወስዶባታል።

ከዚያም ሦስት ሚሊዮን ዩሮ ይዛ ወደ አገር ቤት ገባች።

ከአንድ ዓመት በፊት ወላይታ መሬት ለመግዛት ሄዳ ሳለ፣ የኢንቨስትመንት ቢሮ መሬት ከምትገዢ 600 ሄክታር መሬት እንስጥሽ እንዳሏት ትናገራለች።

መሬቱን ተረክባ ዳግመኛ ወደ እርሻ ገባች።

አትክልትና ፍራፍሬ ታመርታለች፣ የእንስሳት እርባታም አላት።

የግብርና ሥራዋ በረከት ወርቁ ኢንተግሬትድ አግሮ ኢንዱስትሪ ይባላል።

የእርሻ መሬቷ ላይ ሙዝ፣ ቲማቲም፣ ሀባብ፣ ዝኩኒ፣ ደበርጃን እና ሌሎችም ምርቶች አሏት።

ቡና ማቀነባበሪያ እና አስጎብኚ ድርጅትም ከፍታለች። ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ግንባታ ላይም ናት።

እስካሁን ባለው “ትርፋማ ነኝ” የምትለው በረከት፣ በእርሻ መሬቷ ለ130 ቋሚ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥራለች።

የአካባቢው ማኅበረሰብ በጎ አቀባበል ቢኖረውም፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግን ተገቢውን ድጋፍ እንዳልሰጡ በረከት ትገልጻለች።

“የሰው አቀባበል ጥሩ ነው። ግን በመንግሥት ባለሥልጣናት በኩል የማይገቡኝ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ የሆነ ባለሀብት ‘ውሃ ሊያጠጣ ስለሆነ ውሃ ዝጊ’ እባላለሁ። የውሃ እጥረት አለ። ራሴ ተፍጨርጭሬ ነገሮችን ለማስተካል እሞክራለሁ እንጂ እዚያ አካባቢ ያሉ የመንግሥት አካላት እምብዛም ድጋፍ አይሰጡም።”

ደቡብ ሱዳን ከነበረችበት ጊዜ አንስቶ የስፖርት ትጥቅ በመሸጥ፣ በግብርና እና በሌሎችም ሥራዎች ጥሩ ገቢ ታገኝ ነበር።

ባለቤቷ ጆናታን ፒን፣ ግሌኔቨን የሚባል ድርጅት ያለው ሲሆን እሷም በድርጅቱ የድርሻ ባለቤት ናት።

ከእነዚህ ሥራዎቿ ያገኘችውን ገቢ ይዛ ነው በኢትዮጵያ የግብርና መስክ ኢንቨስት ያደረገችው።

“በረከት ገበሬ”

በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እና ማኅበራዊ መዋቅር ውስጥ አብላጫውን ድርሻ የሚይዘው ግብርና ቢሆንም፣ ዛሬም እርሻ አልዘመነም።

አርሶ አደሮች ምርታቸውን ሸጠው ቤተሰባቸውን መደገፍ ይቅርና እራሳቸውን ለመቻልም ሲከብዳቸው ይታያል።

በሌላ በኩል ግብርና ‘አሳፋሪ’ ተደርጎ ሲቆጠርም ይስተዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከወንዝ በቅርብ ርቀት እየኖሩ ውሃ መሳቢያ ሞተር (ፓምፕ) በማጣት ምርታቸውን የሚያጡ አርሶ አደሮችን በረከት እንደ ምሳሌ ትጠቅሳለች።

ማዳበሪያ አጥተው ማምረት ያቃታቸው አርሶ አደሮችም ጥቂት አይደሉም።

ከመንግሥት በተጨማሪ ውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮችን እንዲደግፉ በረከት ትመክራለች።

“. . .ኢትዮጵያን የሚስተካከል አየር ንብረትም ይሁን አፈር በደቡብ ሱዳንም፣ በኡጋንዳም፣ በጣልያንም፣ በአየርላንድም አላየሁም። ውሃችንን፣ አየር ንብረታችንን፣ አፈራችንን አልተጠቀምንበትም። ገበሬ ሲባል ራሱ አሳፋሪ፣ ስድብም እየተደረገ ነው። እኔ ገበሬ ነኝ ብዬ ያንን ለመስበር ነው ወደ ግብርና የገባሁት።”

በረከት ስለ ግብርና ያለውን የተዛባ ምልከታ መለወጥ ስለምትፈልግ ነው እራሷን ‘በረከት ገበሬ’ እንዲሁም ‘ታታሪዋ ገበሬ’ እያለች የምታሞካሸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ ወታደሩን፣ መምህሩን ወዘተ. . . የሚመግብ ገበሬ እንዲከበር ነው ፍላጎቷ።

በቀጣይ የግብርና ምርቶቿን እሴት ጨምራ ወደ ውጭ አገራት መላክ አቅዳለች።

ከእሷ ባሻገር ሌሎች አርሶ አደሮችም “መሬታቸውን፣ ውሃቸውን፣ አፈራቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ከድህነት እንድንወጣ እፈልጋለሁ” ትላለች።

ወደ ኢትዮጵያ ባለሀብቶች እንዲመጡ ከመጋበዝ ባለፈ ሂደቶችን ታመቻቻለች።

በዚህም ለውጥ ማምጣት እንምትችል ተስፋ ሰንቃለች።