አቤል አሰፋ በዓለም አቀፍ የሳይንስ ውድድር ለፍጻሜ ከደረሱት አንዱ ሆነ

በዓለም ዙሪያ ያሉ ተማሪዎች በሳይንስ፣ በፊዚክስ እና በሒሳብ ዘርፎች የተለዩ የፈጠራ ሃሳቦችን በማቅረብ በሚሳተፉበት ብሬክስሩ በተባለው ውድድር ኢትዮጵያዊው ለመጨረሻው ዙር ደረሰ።

የ18 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ አቤል አሰፋ በዓለም አቀፍ የሳይንስ ውድድር ወደ መጨረሻው ደረጃ ለመፎካከር ከደረሱት ምርጥ 30 ተወዳዳሪዎች ውስጥ ነው ለፍጻሜ ከደረሱት ከ16ቱ ውስጥ ለመግባት የቻለው።

አቤል ለመጨረሻው ዙር ውድድር የደረሰው ከቀረበበት የሰሜን አሜሪካ አካባቢ በሕዝብ ምርጫ ቀዳሚውን ቦታ ይዞ እንዳለፈ የውድድሩ አዘጋጆች ይፋ አድርገዋል።

‘ብሬክስሩ' [Breakthrough] የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት የሚያዘጋጀው ይህ ውድድር፣ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፣ በዚህ የፈረንጆች ዓመት 2400 ተወዳዳሪዎች ለመሳተፍ አመልክተው ነበር።

ውድድሩ ውስብስብና ጥልቅ የሆኑ የሳይንስ፣ የሒሳብ እና የፊዚክስ ጽንሰ ሐሳቦችን ምንም የሳይንስ እውቀት የሌላቸው ሰዎች በቀላሉ ሊረዱት በሚችሉት መልኩ በ90 ሰከንድ ቪዲዮ ማቅረብ ነው።

‘ብሬክስሩ' ወጣት ተማሪዎች ጥልቅና ውስብስብ የሆኑ ሳይንሳዊ ጽንሰ ሐሳቦችን አሳታፊ እና ተጨባጭ በሆነ መልኩ በቪዲዮ እንዲያቀርቡ ያበረታታል።

አቤል፣ በዚህ ውድድር ላይ የድምጽ ሞገድ ጽንሰ ሃሳብ ላይ ትኩረት ያደረገ ቪዲዮ ነው ለውድድር ያቀረበው።

ሳይንሱ 'ኖይዝ ካንስሌሽን' ይባላል። በከባቢ ያሉ ተደርበው የሚገቡ ድምጾችን እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል የሚያስረዳ ነው።

ይህንን ቪዲዮ ጨምሮ በዙሩ የተመረጡት ቪዲዮዎች በድርጅቱ የፌስቡክ ገጽ እና የዩቲዩብ ቻናል ላይ የተጫኑ ሲሆን ሕዝብ ድምጽ እንዲሰጥባቸው ቀርበዋል።

ቪዲዮው በፌስቡክ እና በዩቲዩብ ከፍተኛ የሕዝብ ድምጽ (ብዙ ላይክ) ያገኘለት ተወዳዳሪም ወደ ምርጥ 15 ተፎካካሪነት ይገባል።

ለዚህ ዙር የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ እስከ ሰኞ መስከረም 09/2014 ዓ.ም. ድረስ የሚቀጥል ሲሆን በቀጣዩ ቀንም ወደ ምርጥ 15ቱ ውስጥ የተካተቱ ሥራዎች ይፋ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እነዚህ ሒደቶችን አልፎ በመጨረሻ አሸናፊ የሚሆነው ተወዳዳሪ፣ የ250 ሺህ ዶላር የትምህርት ዕድል ሽልማት የሚያገኝ ሲሆን፣ አሸናፊ/አሸናፊዋ ተማሪን ለፈጠራ ሥራ ያነሳሳ የሳይንስ መምህር/መምህርት ደግሞ የ50 ሺህ ዶላር ሽልማት እንዲሁም አሸናፊው ትምህርት ቤት የ100 ሺህ ዶላር ሽልማት ይበረከትላቸዋል።

ብርቱ ፉክክር ባለበት በዚህ ውድድር ከምርጥ 30ዎቹ ውስጥ መግባት የቻለው አቤል፣ የውድድሩ አሸናፊ ሊሆን ይችላል በሚል ተስፋ ተጥሎበታል።

በዘንድሮው 'ብሬክስሩ ቻሌንጅ' ምርጥ 30ዎቹ ውስጥ ከተካተቱት ተማሪዎች ውስጥ ከአሜሪካ፣ ከካናዳ፣ ከቺሊ፣ ከቻይና፣ ከክሮሺያ፣ ከሕንድ፣ ከኢራቅ፣ ከኒው ዚላንድ፣ ከፊሊፒንስ፣ ከትሪንዳድ እና ቶቤጎ፣ ከደቡብ አፍሪካ እና ከዩናይትድ ኪንግደም የተሳተፉ ይገኙበታል።

ከሁለት ዓመት በፊት አንዲት ኢትዮጵያዊት ተማሪ አሸንፋ እንደነበር የሚያስታውሰው አቤል፣ በዘንድሮው ዓመት ግን ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ተወዳዳሪ እርሱ ብቻ እንደሆነ ተናግሯል።

ተማሪ አቤል አሰፋ ማን ነው?

አቤል የተወለደው አዲስ አበባ ውስጥ ሲሆን ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ አየርላንድ የተጓዘው የ11 ወር ህጻን ሳለ ነበር።

ቤተሰቡ አየርላንድ ውስጥ ለስምንት ዓመታት ከቆየ በኋላ ወደ አሜሪካ በማምራት ኑሯቸውን እዚያው አድርገዋል።

በሬድመንድ ትምህርት ቤት የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል።

በትምህርቱም የዋዛ አልነበረም። በሁሉም የትምህርት ደረጃዎችም ከፍተኛ ውጤት ነው ያስመዘገበው።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም ያጠናቀቀው ሁሉንም የትምህርት ዓይነት ‘ኤ’ በማምጣት ነበር።

እዚያው በአሜሪካ እና በካናዳ በሚሰጠው ‘አድቫንስድ ፕሌስመንት’ የተባለውን ፈተና በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ‘ኤ’ በማምጣት ስታንፈርድ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ችሏል።

አሁን ላይ በስታንፈርድ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዩተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ነው።

ከልጅነቱ ጀምሮ ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ፍቅር ያለው አቤል፣ ገና የስምንት ዓመት ልጅ ሳለ ነበር በፈጠራ ሥራዎች እጆቹን ማፍታታት የጀመረው።

ከዚያም ወላጆቹ በኮምፒዩተር ሳይንስ ዘርፍ የተማሩ በመሆናቸው እነርሱ የሚሰሩትን እያየ፣ ራሱንም እያስተማረ ፍላጎቱን በእውቀት አዳብሯል።

አባቱ የኮምፒዩተር ስለተ-ቀመር [ኮዲንግ] ሲሰራ ሲመለከት እርሱም ለመስራት ይሞክር እንደነበር የሚናገረው አቤል፣ ይህም የኮምፒዩተር መተግበሪያዎችን፣ ጌሞችን እና ሌሎች ችግር ፈቺ የሆኑ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን የመስራት ከፍተኛ ፍቅር እንዳሳደረበት ያስረዳል።

ገና በልጅነቱ አስገራሚ ሳይንሳዊ የፈጠራ ሃሳቦችን በማመንጨት ቤተሰቦቹን፣ መምህሮቹን እና የሚያውቁትን ሁሉ ያስደንቅም ነበር።

እናቱ ውብአየሁ ዘውዴ “ብዙ ጊዜ የሆነ ሃሳብ አንስቶ እንደ ቀልድ ያለፍናቸው፣ በኋላ ላይ በጥናት መልክ ታትመው አሊያም በተግባር ሲሰሩ ስናይ ይደንቀናል!” ትላለች።

አቤል ኃላፊነት የሚሰማው፣ በትንሽ ማሳያ ብዙ የሚሰራ እና በርካታ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራ ሃሳቦች እንዳሉትም እናቱ ውብአየሁ ትናገራለች።

ቤት ውስጥ የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች ከማሟላትና በሃሳብ ከመደገፍ በዘለለ የተለየ ድጋፍ እንዳላደረጉለት የምትናገረው ውብአየሁ፣ እውቀቱን ይበልጥ ያሳደገው በዘመኑ ያሉትን የቴክኖሎጂ አማራጮች ለትምህርት በማዋል እንደሆነም ታስረዳለች።

ከፈጠራዎቹ መካከል ጥቂቶቹ

ለቤተሰቦቹ ሁለተኛ ልጅ የሆነው አቤል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከማጠናቀቁ በፊት በርካታ የፈጠራ ሥራዎችን ሠርቷል። ከእነዚህ መካከል፦

  • የሰባት ዓመት ታዳጊ ሳለ በፎቶግራፍ አሊያም በቪዲዮ ላይ ያሉ የማይፈለጉ ምስሎችን አውጥቶ በሌላ ምስል መቀየር የሚያስችል መተግበሪያ [አፕሊኬሽን] ሰርቷል።
  • በስምንት ዓመቱ ደግሞ ተንቀሳቃሽ እና ቀላል የሆነ በሞባይል ስልክ መጠቀም የሚያስችል ‘ፕሮጀክተር ሲስተም’ ሰርቷል።
  • በላቲን ፊደል የተጻፈ ጽሑፍ ፎቶ በማንበብ፣ ወደተፈለገው ሌላ ቋንቋ በመለወጥና ተጠቃሚው በመረጠው ቋንቋ በድምጽ የሚያነብ 'ፒክስፒክ' የተሰኘ መተግበሪያን አበልጽጓል።
  • ይማርበት በነበረው ሬድመንድ ትምህርት ቤት፣ ተማሪዎች የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሙከራዎችን እና ሥራዎችን የሚከውኑበት ተቋም ከጓደኞቹ ጋር መስርቶ የቴክኖሎጂ ረዳት ዳይሬክተር ሆኖ እየሰራ ነው።
  • የኮምፒዩተር ካሜራን በመቆጣጠር ፎቶግራፍ ማንሳት የሚያስችል ሶፍትዌርንም ፕሮግራም አድርጓል።
  • የተለያዩ መተግበሪያዎችንና ምናባዊ እውነታ [ቨርቹዋል ሪያሊቲ] ጌሞችን አበልጽጓል።
  • ብዙ ሰው የሚያሳትፍ አቅጣጫ ማመላከቻ [ጂፒኤስ] ላይ የተመሰረቱና በተለያዩ ‘ፕላትፎርሞች’ ላይ መጫዎት የሚያስችሉ፣ ፎቶግራፍ ማንሳት፣ ምስሎችን በፍጥነት ማጋራት፣ በቀጥታ ማውራት እንዲሁም ድምጽ መስጠት የሚያስችሉ የስልክ ጌሞችንም አበርክቷል። ጌሙ 'ስናፕሾት ባትል ሮያል' ይባላል። ይህ መተግበሪያው በአፕስቶር ላይ ተጭኖም ይገኛል። አቤል ይህንን ሲሰራ የ16 ዓመት ታዳጊ ነበር።

አቤል እንደሚለው፣ ይህንን ጌም ለመስራት የፈለገው ወጣቶች በቤት ውስጥ ሆነው ኮምፒዩተር ላይ ብቻ ከሚጫወቱት ቪዲዮ ጌም ይልቅ ከቤት ውጪ ያሉ ጨዋታዎችን በሚያዝናና መልኩ ለማቅረብ በማሰብ ነው።

ይህም በአካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጤናቸው ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ እና በቤት ውስጥ የሚከወኑ ቪዲዮ ጌሞች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ያለመ እንደሆነም አቤል ይናገራል።

ከዚህም በተጨማሪ አቤል ራሱን በተለያዩ ትምህርታዊ ቪዲዮዎች በማስተማር ካገኘው እውቀት የሠራቸውን ሥራዎች፣ ግዙፉ የቴክኖሎጂ ካምፓኒ፣ ማይክሮሶፍት ውስጥ በተዘጋጀ ወርክ ሾፕ ላይ አቅርቧል።

አቤል እንደሚለው ለተለያዩ ድርጅቶችም ድረ ገጽ ሠርቷል።

“ባላሸንፍ እንኳን ስለ ኢትዮጵያ እነግራቸዋለሁ”

አቤል ውድድር ይወዳል። የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያለ በትምህርት ቤታቸው የ‘ናሽናል ሂስትሪ’ ውድድር ነበር። ይህ ውድድር የሚዘጋጀው ብሔራዊ የታሪክ ቀንን አስመልክቶ ሲሆን በአሜሪካ ያሉ ታሪኮች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው።

አቤል ታዲያ ያኔ ወደ ውድድሩ የገባው ስለ የአድዋ ጦርነት የሚተርክ የ10 ደቂቃ ቪዲዮ ይዞ ነበር።

“ይህ የአሜሪካ ታሪክ አይደለም። ‘አይቀበሉህም’ አልኩት” ትላለች እናቱ ውብአየሁ።

አቤል ለእናቱ ስጋት የሰጠው መልስ ግን ብዙዎችን ያስደነቀ ነበር።

“የያዝኩት ታሪክ በውድድሩ ባያሸንፍ እንኳን በዚሁ አጋጣሚ ስለ ኢትዮጵያ እነግራቸዋለሁ” ነበር ያለው።

እናቱ ውብአየሁ እንደምትለው በዚህ ውድድር ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ውስጥ መግባት ችሎ ነበር።

አቤል አገሩን ማስተዋወቅ፣ ለአገሩ መቆርቆር እና አስተዋጽኦ ማድረግ ይፈልጋል።

በእርግጥ ይህ ሃሳብ ያለው አቤል ጋ ብቻ አይደለም። የሕክምና ሳይንስ እያጠናች ያለችው ታላቅ እህቱም አገሯን የማገልገል ህልም አላት።

ኑሯቸው በባሕር ማዶ ይሁን እንጂ ህልማቸው በአገራቸው እንደሆነ እናታቸው ውብአየሁ ትናገራለች።

“ምክንያቱም 'እናንተ ያገኛችሁትን ለማኅበረሰባችሁ መልሳችሁ ስጡ' እያልን ነው ያሳደግናቸው” ትላለች።

ውቅያኖስ ያቋረጠው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት

አቤል ገና በልጅነቱ ያገኘውን እውቀትና የትምህርት ልምድ ራሴ ብቻ ልደግበት አላለም።

ገና በልጅነት ዕድሜው ለሌሎች እኩዮቹ መትረፍን ጉዳዬ ብሎ ይዞታል።

ትምህርት በሚዘጋበት ጊዜ ወደ አገሩ ፊቱን አዙሮ ያገኘውን እውቀትና ልምድ አካፍሏል።

ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከ100 በላይ ለሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሥልጠና ሰጥቷል።

የዕድሜ እኩዮቹ፣ ያለውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ራሳቸውን እንዴት ማስተማር እንዳለባቸው፣ ቴክኖሎጂን ለበጎ ዓላማ እና ችግር መፍቻ መንገድ እንዲጠቀሙበት እንዲሁም ድረ ገጽ እንዴት መስራት እንደሚቻል ያለውን ሳይንሳዊ እውቀት አጋርቷቸዋል።

በእርግጥ በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ ያለው የሰዓት ልዩነት እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ ተግዳሮት ቢሆኑበትም ሳይታክት ያለውን እንካችሁ ብሏል።

ቀደም ብሎም በሚኖርበት አሜሪካ በእረፍት ጊዜው ተማሪዎችን ያስተምር ነበር።

“እውቀቴን ማካፈል ደስታ ይሰጠኛል” ይላል ተማሪው አቤል።

አቤል ወደፊቱ ብሩህ ሆኖ ነው የሚታየው። የሚሄድበትን መንገድም ያውቀዋል። ዓላማውንም፣ ግቡንም።

በትምህርቱ ረገድ ማጥናት የሚፈልገውን የኮምፒዩተር ሳይንስ ለመማር አሉ ከተባሉ የዓለማችን ዩኒቨርሲቲዎችን አንዱን ተቀላቅሏል።

የቴክኖሎጂ እውቀቱን ማካበት፣ ልምድ ማዳበር ይፈልጋል። እየሄደበት ያለው መንገድም ይህንኑ የሚያመላክት ነው።

ከዚያስ? አልነው አቤልን።

“ከዚያ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ያሉ ችግሮችን መፍታት፣ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከት ነው የምፈልገው” ብሏል።