የሱዳን ከፍተኛ ጄኔራል አረብ ኤሜሬቶችን ለፈጥኖ ደራሹ ኃይል ድጋፍ በመስጠት ወቀሱ

አንድ ከፍተኛ የሱዳን ጦር ሠራዊት ጄኔራል የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወታደራዊ ድጋፍ በማድረግ ወቀሱ።

ከዚህ ቀደም የሱዳን መንግሥት ጦር አመራሮች ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በጎረቤት አገር ይደገፋል ከማለት ውጪ በስም የጠሩት መንግሥት ኖሮ አያውቅም።

“ከደኅንነት እና ከዲፕሎማሲያዊ ምንጮች የተገኙ መረጃዎች የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ጃንጃዊድ ሚሊሻን ለመደገፍ አውሮፕላን ትልካለች” ሲሉ ጄኔራል ያሲር አል-አታ በኦምድሩማን ከተማ ለተሰበሰቡ የደኅንነት አባላት ተናግረዋል።

ጃንጃዊድ የሚባሉት የአረብ ሚሊሻዎች በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተደራጁ ሲሆኑ፣ ከቀድሞው የአል-በሽር መንግሥት ትዕዛዝ ተቀብለው በዳርፉር ግዛት ውስጥ እየተቀሰቀሱ አመጸኞችን ሲደመስሱ ነበር።

የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ግን የቀረበባትን ክስ አጣጥላ ከጦርነቱ መጀመር አንስቶ አገሪቱ “ግጭት እንዲቀንስ፣ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ዲፕሎማሲያዊ ንግግሮች እንዲጀመሩ” ጥረት ስታደርግ መቆየቷን አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

እኒህ በስም ያልተጠቀሱት የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ባለሥልጣን አገራቸው በሱዳን ጎረቤት ቻድ በተቋቋመ ጊዜያዊ ሆስፒታል የሰብዓዊ እርዳታ እያደረገች እንደሆነ ጭምር ገልጸዋል።

የሱዳን ጦር መሪ እና የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን ምክትል ሆነው እያገለገሉ ያሉት ጀነራል ያሲር አል-አታ ግን አረብ ኢሜሬቶች ምንነታቸውን ያልገለጿቸው ወታደራዊ ድጋፎችን በመካከለኛው አፍሪካን ሪፐብሊክ፣ በኡጋንዳ እና በቻድ በኩል ለሐምዳን ዳጋሎ ጦር አድርሳለች ሲሉ ይከሳሉ።

ጄኔራሉ ጨምረውም በሩሲያ እንዲበተን ከመደረጉ በፊት ቅጥረኛው ቡድን ቫግነር በመካከለኛ አፍሪካ ሪፐብሊክ በኩል የጦር ድጋፉ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር እንዲደርስ ሲያስተባብር ቆይቷል ብለዋል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ግን ከሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን፤ ቫግነር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለኝም ሲል ቆይቷል።

ድሮን እና ተተኳሾች

ይህ የጦር ጄኔራሉ አስተያየት የተሰማው በጄኔራል መሐመድ ደጋሎ ሔሜቲ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ባለፉት ሳምንታት ውስጥ በአገሪቱ ጦር ሠራዊት ላይ የበላይነትን እየያዘ እንደሆነ ከተነገረ በኋላ ነው።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ኛላ የተባለችውን ሁለተኛዋን የሱዳን ትልቅ ከተማን ጨምሮ በርካታ የምዕራብ ሱዳን አካባቢዎችን እና ሰፊ የካርቱም ሰፈሮችን በቁጥጥሩ ስር አስገብቷል።

የዐይን እማኞች እንደሚሉት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በጦርነቱ ጅማሬ ወቅት ያልነበሩትን ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ዘመናዊ መሳሪያዎችን በቅርብ ጊዜያት ውጊያዎች ላይ ጥቅም ላይ እያዋለ ነው።

ይህን የጦር ጄኔራሉን አስተያየት የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “ፍጹም ሐሰት” ሲሉ ያጣጣሉት ሲሆን፣ ቻድ እና መካከለኛው አፍሪካን ሪፐብሊክ ሮይተርስ ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

ጄኔራል አታ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትቶችን ቢወቅሱም፤ በቅርቡ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎችን ለማሰባሰብ ወደተለያዩ አገራት እየተዘዋወሩ የሚገኙት አል-ቡርሃን ወደ አቡ ዳቢ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት እንደሚሄዱ ይፋ አድርገዋል።

አረብ ኤሜሬትቶች ባለፈው ዓመት በሱዳን የቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ በ6 ቢሊዮን ዶላር ወደብ ለመገንባት ከአገሪቱ መንግሥታት ጋር ስምምነት ፈጽማ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ የሱዳን የወርቅ ምርት መዳረሻው አቡ ዳቢ ነው።

ሰባት ወራት ያስቆጠረው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፣ ሁለቱን ተዋጊ ኃይሎች ለማቀራረብ የተደረጉት ጥረቶች በሙሉ አልተሳኩም።

ባለፉት ወራት ጦርነት በማቆም ከስምምነት እንዲደረስ አሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ድርጅቶች እንዲሁም የአካባቢው አገራት ለማሸማገል ጥረት ቢያደርጉም እስካሁን አልተሳካላቸውም።

ይልቁንም በሱዳን የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ሚሊሻዎች አንዳቸው ከሌላኛው ጋር ወግነው እንደሚዋጉ እየገለጹ ይገኛሉ።

በሱዳን የእርስ በእስር ጦርነት ቢያንስ ከ7 ሺህ በላይ ሰላማዊ ሰዎችን የገደለ ሲሆን፣ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ከመኖሪያቸው ማፈናቀሉን የተባበሩት መንግሥታት አሃዝ ያሳያል።