ሐማስ ከእስራኤል አፍንጫ ስር ወታደራዊ ልምምድ በማድረግ እንዴት ኃይሉን መገንባት ቻለ?

አምስት ፍልስጤማውያን ቡድኖች ሐማስ መስከረም 26 በእስራኤል ላይ ጥቃት ሲፈጽም ተሳታፊ ነበሩ። ለዚህም ላለፉት ሦስት ዓመታት በጋራ ወታደራዊ ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የቢቢሲ ኒውስ ትንተና ያመለክታል።

ቡድኖቹ ከፈጸሙት ድንገተኛ ጥቃት ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ጋዛ ውስጥ የጋራ ልምምድ ሲያደርጉ ነበር። ልምምዱ እስራኤልን ከጋዛ ጋር ከሚለየው አካባቢ ከአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ባነሰ ቦታ ጨምር ልምምዱን ማካሄዳቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ይፋ አድርገዋል።

ታጣቂዎቹ ሰዎችን ማገት፣ አንድ አካባቢን ወሮ ማጥቃት እና የእስራኤልን የመከላከያ አጥር እንዴት ጥሰው ማለፍ እንደሚችሉ በልምምዳቸው ውስጥ ተካቷል። የመጨረሻው ልምምድም ከጥቃቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የተካሄደ ነበር።

የቢቢሲ አረብኛ አገልግሎት እና ቢቢሲ ቬሪፋይ የሰበሰቧቸው ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ሐማስ በጋዛ ያሉትን ፍልስጤማውያን አንጃዎችን በአንድ ላይ በማምጣት ጥቃት በሚፈጽሙባቸው ዘዴዎች እንዲካኑ አድርጓል።

በመጨረሻም መስከረም 26/2016 ዓ.ም. አካባቢውን ጦርነት ውስጥ የዘፈቀውን ወረራ እና ጥቃት ወደ እስራኤል ዘልቀው በመግባት ፈጽመዋል።

‘የአንድነት ምልክት’

በምሥጢር ስሙ ‘ጠንካራ መሰሶ’ ተብሎ የሚጠራው ለአራት ዙሮች የተደረገው ወታደራዊ ልምምድ ከሦስት ዓመት በፊት በታኅሣሥ ወር ሲጀምር፣ የሐማስ ዋነኛ መሪ የሆኑት ኢስማኤል ሃኒያ በጋዛ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ታጣቂዎች “የአንድነት ምልክት ነው” ብለው ነበር።

በጋዛ ውስጥ ዋነኛው ኃያል ቡድን የሆነው ሐማስ ሌሎች አስር ፍልስጤማውያን ቡድኖች የተሳተፉበትን የጦር ልምምድ የሚመስለውን ወታደራዊ ልምምድ “በጋራ የዘመቻ ክፍል” የበላይ በመሆን መርቶታል።

ይህ “የጋራ ዘመቻ ክፍል” የሚባለው በአውሮፓውያኑ 2018 በጋዛ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖችን በአንድ ለማስተባበር የተመሠረተ የጋራ ማዕከላዊ ዕዝ ነው።

ከዚያ በፊት ግን ሐማስ በጋዛ ውስጥ ሁለተኛው ትልቁ የታጠቀ ቡድን ከሆነው የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ ጋር በይፋ ትብብር መስርቶ ቆይቷል። ቡድኑ እንደ ሐማስ ሁሉ በዩናይትድ ኪንግደም እና በሌሎች ምዕራባውያን በሽብርተኝነት የተፈረጀ ነው።

ቀደም ባሉት ግጭቶች ሐማስ ከሌሎች ቡድኖች ጎን ተሰልፎ የተዋጋ ሲሆን፣ ለፕሮፓጋንዳ ተብሎ ይፋ የሆኑ መረጃዎች እንደሚያመለክተቱት በአውሮፓውያኑ 2020 በተካሄደው ልምምድ ላይ ግን ከዚህ በፊት ከነበሩት በርካታ ቡድኖች በአንድነት መሳተፋቸው ታይቷል።

የሐማሱ መሪ እንደተናገሩት የመጀመሪያው ልምምድ በታጣቂ ቡድኖቹ መካከል “ቋሚ ዝግጁነት” እንዳለ ያንጸባረቀ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2020 የተካሄደው ልምምድ በጋራ ከተካሄዱት አራት ተመሳሳይ ልምምዶች የመጀመሪያው ነው። ቡድኖቹ ያደረጓቸው አራቱንም ልምምዶች የሚያሳዩ በአግባቡ የተሰናዱ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል በይፋ ቀርበዋል።

በመልዕክት መለዋወጫው መተግበሪያ ቴሌግራም ላይ ከተሰራጨ ቪዲዮ ላይ የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ ቡድንን ጨምሮ 10 ቡድኖች ‘ጠንካራ ምሰሶ’ በተባለው ወታደራዊ ልምምድ ላይ ከሐማሰ ጎን መሳተፋቸውን ቢቢሲ የቡድኖቹ አባላት በጭንቅላታቸው ላይ በሚያስሩት ጨርቅ እና በአርማቸው ለመለየት ችሏል።

ከመስከረም 26ቱ ጥቃት በኋላ በልምምዱ ከተሳተፉት ቡድኖች መካከል አምስቱ በጥቃቱ ውስጥ መሳተፋቸውን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አጋርተዋል። ሌሎቹ ሦስት ቡድኖች ደግሞ በጥቃቱ ውስጥ መሳተፋቸውን የሚያሳውቁ መግለጫዎችን በቴሌግራም ላይ አሰራጭተዋል።

ከጥቃቱ በኋላ ከእስራኤል ታግተው የተወስደተዋል ተብሎ የሚታመኑት በርካታ ሴቶች እና ሕጻናትን በተመለከተ በሐማስ ላይ ጫናዎች እየበረቱ ሲመጡ ትኩረቱ በበለጠ በጥቃቱ ተሳታፊ ወደ ነበሩት ቡድኖች ላይ ዞሯል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት ሦስቱ ቡድኖች ማለትም የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ፣ የሙጃሂዲን ብርጌድ እና አል-ናሲር ሳላህ አል-ዲን ብርጌድ እስራኤላውያን ታጋቾችን መያዛቸውን አሳውቀው ነበር።

እስራኤል ከሐማስ ጋር የደረሰችው ጊዜያዊ ተኩስ አቁም እንዲራዘም ጥረት በሚደረግበት ጊዜ በሌሎች ቡድኖች ተይዘው የሚገኙትን ታጋቾች ሐማስ ያሉበትን እንዲያሳውቅ ተጠይቆ ነበር።

በጥቃቱ ውስጥ እንደተሳተፉ የሚነገርላቸው እነዚህ ቡድኖች ከአክራሪ እስላማዊ ርዕዮተ ዓለም አስከ ዓለማዊ አቋምን በሚያንጸባረቁ የተለያየ አመለካከት ቢኖራቸውም፣ በእስራኤል ላይ ኃይል ለመጠቀም ያላቸው ቁርጠኝነት ግን ያመሳስላቸዋል።

ሐማስ በተደጋጋሚ የሚያወጣቸው መግለጫዎች በጋዛ ውስጥ ያሉ የተለያዩ አመለካከት ያላቸው ታጣቂ ቡድኖች አንድነት እንዲፈጥሩ አጥብቀው የሚጠይቁ ናቸው።

በጋራ ባካሄዱት ወታደራዊ ልምምድ ላይ ቡድኖቹ በአቻነት ይቅረቡ እንጂ፣ በእስራኤል ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በማቀድ ሐማስ የመሪነቱን ሚና ይዞ ቀጥሏል።

ልምምዱን በሚያሳዩ ቪዲዮዎች ላይ ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑ አዛዦች ከምሽግ ውስጥ ሆነው ልምምዱን ሲመሩ እና ሮኬት ሲተኮስ ይታያል።

በተጨማሪም በከባድ ሁኔታ የታጠቁ ተዋጊዎች የእስራኤል ሰንደቅ ዓላማ ያለበት የታንክ አምሳያን በመውረር፣ የታንኩ አሽከርካሪዎች የሚመስሉ ሰዎችን በማስወጣት እየጎተቱ ሲወስዱ እና በአንድ ሕንጻ ላይ ወረራ ሲያካሂዱ ይታያሉ።

በመስከረም ወር መጨረሻ ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመው ጥቃትን በተመለከተ የወጡ ቪዲዮዎች እና የዐይን እማኞች ምስክርነት በልምምዱ ወቅት የተፈጸሙ ድርጊቶች ተግባራዊ መደረጋቸውን ያመለክታሉ።

‘ጠንካራ ምሰሶ’ ማቆም

ፍልስጤማውያኑ ቡድኖች የመጀመሪያውን የጋራ ልምምድ ካደረጉ በኋላ ልክ በዓመቱ ሁለተኛውን ደግመው አካሂደዋል።

የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ኢዘዲን አል-ቃሳም አዛዥ የሆነው አይማን ኖፋል እንዳለው፣ ሁለተኛው ዙር ልምምድ ዋነኛ ዓላማው ያደረገው “የፍልስጤም ትግል ቡድኖችን አንድነት ማጠናከር ነው።”

ጨምሮም ልምምዶቹ “ጠላት በጋዛ ድንበሮች ላይ የገነባው አጥር እና ምህንድስና ከምንም እንደማያስጥለው እንዲያውቅ ለመንገር ነው” ብሏል።

ሌላ የሐማስ መግለጫ ደግሞ በቡድኖቹ መካከል የተካሄዱት “የጋራ ወታደራዊ ልምምዶች ከጋዛ አቅራቢያ ያሉትን ሰፈራዎችን [ቡድኑ እስራኤላውያን ማኅበረሰቦችን የሚገልጽበት ቃል ነው] ነጻ ለማውጣት” የተዘጋጀ መሆኑን አመልክቷል።

ለሦስተኛ ጊዜ ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ልምምድ በተመለከተ በተሰራጨ የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮ ላይ ተዋጊዎቹ ሕንጻዎች ውስጥ ያሉ ክፍሎችን ሲያስሱ እና ታንኮችን ሲቆጣጠሩ ያሳያል። ይህም በጥቃቱ ጊዜ ከተፈጸመው እና በቪዲዮ ከታየው ክስተት ጋር የሚመሳሰል ነው።

ፍልስጤማውያኑ ቡድኖች እያካሄዷቸው ስላሉት ልምምዶቹ እስራኤል ውስጥ ሪፖርት የተደረገ ሲሆን፣ ይህም በአገሪቱ መጠነ ሰፊ የደኅንንት ተቋማት በቅርብ ክትትል አልተደረገባቸውም ብሎ መገመት አይቻልም።

ቀደም ሲል ሐማስ የሚያካሂዳቸውን ሥልጠናዎች ለማስቆም የእስራኤል የመከላከያ ኃይል የአየር ጥቃቶችን ፈጽሞ ነበር። ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ ደግሞ የፍልስጤማውያኑ ቡድን ‘ጠንካራ ምሰሶ’ ብለው የሰየሙት የመጀመሪያው ልምምድ የተካሄደበት ስፍራ በቦምብ ተደብድቧል።

የመስከረም 26 ጥቃት ከመፈጸሙ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ደግሞ፣ በጋዛ ድንበር አቅራቢያ ቅኝት የሚያደረጉ ሴት ወታደሮች ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ደሮኖች) እንቅስቃሴ እንዳለ አስጠንቀቀው ነበረ። ሐማስ የቅኝት የቦታዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ልምምድ እያደረገ መሆኑም ሪፖርት ተደርጓል።

ነገር ግን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት በድንበር አካባቢ የነበሩትን እንቅስቃሴዎች በተመለከተ የተሰጡ መረጃዎች ችላ ተብለው ነበር።

በጋዛ ውስጥ የእስራኤል ሠራዊት የቀድሞ አዛዥ የነበሩት ጄኔራል አሚር አቪቪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ “ልምምድ እያካሄዱ መሆናቸውን የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች ነበሩ። እንዲሁም ቪዲዮዎችም ለሕዝብ ተሰራጭተዋል። ይህ ሁሉ ሲካሄድ የነበረው ከእስራኤል ድንበር በመቶዎች ሜትር ርቀት ላይ ነው” ብለዋል።

ጄኔራሉ ጨምረውም ምንም አንኳን የእስራኤል ጦር ሠራዊት እየተካሄደ ስለነበረው ልምምድ ቢያውቅም “ሥልጠናውን ለምን እያካሄዱ አንደሆነ አልተመለከተውም” ሲሉ ክስተቱ ችላ መባሉን ገልጸዋል።

የእስራኤል ጦር ኃይል ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ በጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ባካሄደው ዘመቻ የሐማስ ተቀዳሚ ከፍተኛ ወታደራዊ መሪ የሆነውን ኖፈልን “ማስወገዱን” አስታውቋል።

በግልጽ ቦታ ላይ መደበቅ

ሐማስ የተካሄዱት ልምምዶች ሁሉ ተጨባጭ ውጤትን እንዲያስገኙ አስፈላጊውን ሁሉ አድርጓል።

ፍልስጤማውያኑ ተዋጊዎች ባለፈው ዓመት ባካሄዱት ልምምድ ላይ የእስራኤል ወታደራዊ ሰፈርን እንዴት መውረር እንደሚችሉ አስመስለው በመሥራት ተለማምደዋል።

ይህ ልምምድ ደግሞ የተደረገው በእስራኤል ቁጥጥር ስር ከሚገኘው በእስራኤል እና በጋዛ መካከል ካለው የኤሬዝ መተላላፊያ ከሦስት ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ ነበር።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ልምምዱን የሚያሳይ ቪዲዮን እና ከአየር ላይ የተነሱ ምስሎችን በማመሳከር ስፍራው ከሰሜናዊ የጋዛ ጫፍ ላይ ከእስራኤል የመከላከያ አጥር 800 ሜትር በራቀ ቦታ ላይ መሆኑን ተረድቷል። ይህ ስፍራ አሁንም በካርታ ላይ ተለይቶ የሚታይ ነው።

የልምምድ ካምፑ እስራኤል በመቶዎች ሚሊዮኖች ዶላር በማውጣት ለደኅንነት ስትል ከገነባችው አጥር ጋር በተያያዘ ለቅኝት ካዘጋጀችው የመመልከቻ ማማ በ1.6 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ የሚገኝ ነው።

ለልምምድ ተብሎ የተዘጋጀው ተመሳሳይ የጦር ሰፈር ከአካባቢው አቀማመጥ በተለየ ዝቅ ተብሎ ወደታች ተቆፍሮ ተሠራ በመሆኑ በአቅራቢያ ቅኝት በሚያደርጉ የአስራኤል ወታደሮች በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ነገር ግን በልምምዱ ወቅተ በሚኖር ፍንዳታ የሚከሰት ጭስ የሚታይ ሲሆን፣ የእስራኤል ሠራዊትም በአካባቢው የአየር ላይ ቅኝት እንደሚያደርግ ይታወቃል።

ይህንን ቦታ ሐማስ ሕንጻዎችን ወሮ ለመቆጣጠር፣ መሳሪያ ደግኖ ታጋቾችን ለመውሰድ እና የደኅንነት አጥሮችን ለማውደም የሚደረጉ ልምምዶችን ለማካሄደ ተጠቀሞበታል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ በመላዋ ጋዛ ውስጥ በዘጠኝ የተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ 14 የሥልጠና ስፍራዎችን ለመለየት የሳተላይት ምስሎችን ጨምሮ ሌሎች ለሕዝብ ክፍት የሆኑ መረጃዎችን ተጠቅሟል።

የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ማከፋፈያ ማዕከል ከሚገኝበት ቦታ ከ1.6 ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ ባለው ቦታ ላይ ሁለት ጊዜ ልምምድ ተካሂዷል። ቦታውም የእርዳታ ድርጅቱ ባለፈው ዓመት በይፋ ካሰራጨው ቪዲዮ ላይ ከጀርባ በግልጽ ይታያል።

ዝግጅት ለምድር፣ ለባሕር እና ለአየር ጥቃቶች

ከጥቃቱ ጥቂት ሳምንት በፊት ልምምዱን የሚመራው የፍልስጤማውያኑ የጋራ ኮሚቴ በቴሌግራም ቻናሉ ላይ ባሰራጨው ምሥል ላይ ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱ ተዋጊዎች በጋዛ ድንበር አካባቢ ባሉ ወታደራዊ ተቋማት ላይ ቅኝት ሲያደርጉ አሳይቷል።

ይህንንም ተከትሎ የቡድኖቹ አራተኛው ወታደራዊ ልምምድ የተደረገባቸው የጥቃት ስልቶች እና ዘዴዎች እስራኤል ከዚህ ቀደም አጋጥሟት በማያውቀው የመስከረም 26/2016 ዓ.ም. ድንገተኛ ጥቃት ላይ ተግባራዊ ሆነዋል።

ተዋጊዎቹ በልምምድ ወቅት እንዳደረጉት ሁሉ በተመሳሳይ በክፍት ነጭ ቶዮታ መኪና ላይ ሆነው በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ ሲዘዋወሩ በቪዲዮ ተቀርጸዋል።

የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮዎች ላይ ታጣቂዎች ለልምምድ የተዘጋጀ ሕንጻን ሲወሩ እና ከውስጥም ባዘጋጇቸው ኢላማዎች ላይ ሲተኩሱ፣ እንዲሁም ጀልባዎችን እና ከውሃ በታች የሚጓዙ ጠላቂዎችን በመጠቀም የባሕር ዳርቻ አካባቢን ለማጥቃት ልምምድ ሲያደርጉ ታይተዋል።

ከዚህ አኳያ እስራኤል በመስከረም 26ቱ ጥቃት ወቅት በጀልባ የመጡ የሐማስ ተዋጊዎችን ዕቅድ እንዳከሸፈች አስታውቃለች።

ከዚህ ሁሉ ግን በጥቃቱ ወቅት በሰፋት ስለተነገረላቸው የሐማሰ ተዋጊዎቸ ጥቅም ላይ ስላዋሏቸው ሞተር ሳይክሎችን አና የአየር ላይ መንሳፈፊያዎችን በተመለከተ ሰለተካሄደ ልምምድ በፕሮፓጋንዳ ቪዲዮዎቹ ላይ ምንም የተባለ ነገር አልነበረም።

ከጥቃቱ ሦስት ቀናት በኋላ ሐማስ ይፋ ባደረገው ቪዲዮ ላይ ሞተር ሳይክሎች ወደ ደቡባዊ እስራኤል ዘልቀው ለመግባት እንዲችሉ አጥሮች እና ማገጃዎች ሲፈራርሱ አሳይቷል። ከዚህ ውጪ ቀደም ብሎ የወጣ ተመሳሳይ ቪዲዮዎችን ቢቢሲ አላገኘም።

በተጨማሪም የአየር ላይ መንሳፈፊያ የሚጠቀሙ ተዋጊዎችን የሚያሳይ ቪዲዮ ከጥቃቱ በኋላ እንጂ ከዚያ በፊት ሐማስ ለሕዝብ ይፋ አላደረገም።

ወታደራዊ ልምምድን በሚያሳየው እና በጥቃቱ ዕለት በተለቀቀው ቪዲዮ ላይ ታጣቂዎች የእስራኤላውያን መንደርን መስሎ በተዘጋጀ ስፍራ ላይ ከአየር ላይ ሲያርፉ ይታያሉ። ይህ ቦታም በሰሜናዊ ጋዛ ውስጥ ከራፋህ በስተሰሜን የሚገኝ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ማረጋገጥ እንደቻለው ይህ ቪዲዮ ከአንደ ዓመት በፊት የተቀረጸ ሲሆን፣ የቪዲዮው የተቀመጠበት የኮምፒውተር ፋይል ስምም የሐማስ የአየር ኃይል ክፍል በመሆነው ‘ኤግል ስከኳድሮን’ በሚል ነው። ይህም በተንሳፋፊ መሳሪያ በእስራኤል ላይ ጥቃት የመፈጸሙ ዕቅድ ከአንድ ዓመት በላይ ሲሠራበት እንደነበረ አመልክቷል።

ለማመን ያዳገተው ድንገተኛ ጥቃት

ከመስከረም 26ቱ ጥቃት በፊት የእስራኤል ጦር ሠራዊት አዛዦችን በመጥቀስ የወጡ ዘገባዎች ሐማስ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ 30,000 የሚደርሱ ተዋጊዎች እንዳሉት ገልጸዋል። በተጨማሪም ቡድኑ ከሌሎች ትናንሽ ታጣቂ ቡድኖች በርካታ ሺህ ተዋጊዎችን ሊያሰባስብ እንደሚችል ይታሰብ ነበር።

ከፍልስጤማውያን ታጣቂ ቡድኖች መካከል ሐማስ በከፍተኛ ደረጃ ልዩነት ያለው ኃያል ቡድን ነው። ሐማስ በጋዛ ያሉ ታጣቂ አንጃዎችን በማሰባሰብ በጋዛ ውስጥ ሰፊ ድጋፍን ማግኘት እና የተዋጊዎቹን ቁጥር የበለጠ ከፍ የማድረግ ፍላጎትንም የያዘ ነው።

የእስራኤል ጦር ሠራዊት ቀደም ሲል በጥቃቱ ላይ 1,500 ተዋጊዎች መሳተፋቸውን የገመተ ሲሆን፣ ታይምስ ኦፍ እስራኤል በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ እንደዘገበው ሠራዊቱ በጥቃቱ የተሳተፉት አሃዘ ወደ 3,000 ይጠጋል ብሏል።

በወታደራዊ ልምምዱ እና በመስከረም ወር መጨረሻው ጥቃት የተሳተፉ የፍልስጤም ተዋጊዎችን ትክክለኛ ቁጥርን ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ቁጥሩ ምንም ይሁን ምን በጥቃቱ ውስጥ የተሳተፉት በጋዛ ካሉ አጠቃላይ ታጣቂዎች መካከል በአንጻራዊነት ትንሽ ቁጥር ያላቸው ተዋጊዎች ብቻ ናቸው።

ምንም እንኳን ሐማስ ከጥቃቱ በፊት በፍልስጤም ታጣቂ አንጃዎች መካከል መተባበረ እንዲጎለብት ሲሠራ የቆየ ቢሆንም፣ ስለጥቃቱ ዕቅድ አና ዝርዝር መረጃን ተቆጣጠሮ ቆይቷል።

የቀድሞው የሊባኖስ ሠራዊት ብርጋዴር ጄኔራል የነበሩት እና በመካከለኛው ምሥራቅ ጥናት እና ምርምር ማዕከል የደኅንነት ተንታኝ የሆኑት ሂሻም ጃቤር እንደሚያምኑት የጦር ልምምዱን የመጨረሻ ግብ የሚያውቀው ሐማስ ብቻ ነው። “ምናልባትም ሐማስ ሌሎቹን ቡድኖች በጥቃቱ እንዲሳተፉ ያደረጋቸው በዕለቱ ሊሆን ይችላል” ይላሉ።

በለንደኑ ኪንግስ ኮሌጅ የደኅንነት ጥናት ከፍተኛ መምህር የሆኑት አንድሪያስ ክሬግ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “የጥቃቱ ዕቅድ በማዕከላዊነት ተሠራ ሲሆን፣ ሁሉም ቡድን ዕቅዱን ተግባራዊ ሲያደረግ ይሆናል በሚለው መንገድ እንዲያሳካ በሚል አፈጻጸሙ ማዕከላዊነትን የተከተለ አይደለም” ብለዋል።

ጨምረውም በሐማስ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ባደረጉት ንግግር በእስራኤል በኩል ያለው የመከላከል አቅም ይህን ያህል ደካማ መሆኑ አስደንቋቸዋል፤ እንዲሁም ታጣቂዎቹ ከእስራኤልን የመከታተያ ቴክኖሎጂ ውጪ ለመሆን ግንኙነታቸውን በቀጥታ ማድረጋቸውን ገምግመዋል።

በአውሮፓው ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ውስጥ የመካከለኛው ምሥራቅ ተንታኝ የሆኑት ሁግ ሎቫት እንደሚሉት እስራኤል የፍልስጤማውያኑን የጋራ የጦር ልምምድ በተመለከተ ሳታውቀው አትቀርም፣ ነገር ግን በፍልስጤም ግዛቶች ውስጥ ያሉትን ታጣቂ ቡድኖች “መደበኛ” እንቅስቃሴን በመገምገም “ከፍተኛ ጥቃት እያንዣበበ መሆኑን የሚያመለክት አይደለም በሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል” ብለው ያምናሉ።

የተጠቀሱት ጉዳዮችን በተመለከተ የተጠየቀው የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሰጠው ምላሽ “በአሁኑ ወቅት ትኩረታችን በሽብርተኛው ድርጅት ሐማስ አማካይነት የተደቀነውን አደጋ ማስወገድ ነው” በማለት ተፈጥረዋል ስለተባሉት የደኅንነት ችግሮች “በኋላ ላይ የሚታዩ ይሆናል” ብሏል።

እስራኤል በመስከረም 26 በተፈጸመባት ጥቃት የደረሰባትን እልቂት ለመከላከል የሚያስችሏት ዕድሎች እንዴት ሊያመልጧት እንደቻሉ በይፋ እስክትመረምር እና እስክትደርስበት ድረስ በርካታ ዓመታት ሊወስድ ይችላል።

ነገር ግን በፍልስጤማውያን ቡድኖች የተፈጸመው ከባዱ እና ድንገተኛው ጥቃት በአስራኤል የመከላከያ ኃይል፣ በአገሪቱ የስለላ ተቋማት እና በመንግሥት ላይ የሚያስከትለው ውጤት ከፍተኛ መናጋት ሊፈጥር ይችላል።