ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሞት ጥላ ስር ሆነው እስራኤልን እንቅልፍ የነሷት የሐማስ መሪዎች እነማን ናቸው?
ሐማስ በተለይ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጦር ሠራዊቷ እና በስለላ ተቋሞቿ አማካይነት የሐማስን መሪዎች እንደምታጠፋ በመዛት በተለያዩ ደረጃ ያሉ የቡድኑን መሪዎች ዒላማ አድርጋለች።
እስካሁን ግን የቡድኑን ከፍተኛ አመራሮች ለመያዝም ሆነ ለመግደል ሳትችል ቆይታለች። አሁን ከጋዛ ውጪ ኢራን ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት የሐማስ ዋነኛ ሰው የሆኑትን ኢስማኤል ሃኒያን መግደሏን ቡድኑ እና ኢራን አረጋግጠዋል።
ከእስራኤል ጋር በሚደረገው ድርድር ቁልፍ ሰው የሆኑት መቀመጫቸውን ኳታር ዶሃ አድርገው የሐማስን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሲመሩ የነበሩት ሃኒያ በምን እና እንዴት እንደተገደሉ ባይገለጽም በነበሩበት ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሕይወታቸው አልፏል።
ኢስማኤል ሃኒያ ፍልስጤማዊው ታጣቂ ቡድን ካሉት አራት ወሳኝ ሰዎች መካከል አንዱ የነበሩ ሲሆን፣ ከጋዛ ወጥተው ዶሃ ውስጥ መኖር ከጀመሩ በኋላ በጥብቅ የደኅንነት ጥበቃ ስር ዓመታትን አሳልፈዋል።
አሁን ግን ከዋናው መቀመጫቸው ውጪ በዋነኛ ወዳጃቸው ኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተገድለዋል። ኢስማኤል ሃንያ ማን ነበሩ?
ሐማስ “የአል-አቅሳ ጎርፍ” ብሎ በሰየመው ዘመቻ ድንገተኛውን እና ታይቶ የማይታወቀውን የተቀናጀ ጥቃት ቅዳሜ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ከፈጸመ ለኋላ በርካቶች የቡድኑ መሪዎች እነማን ናቸው? የሚል ጥያቄን እያነሱ ነው።
ጋዛን የሚያስተዳድረው የሐማስ አብዛኞቹ መሪዎች በመገናኛ ብዙኃን ሲቀርቡ ፊታቸውን በጭንብል ሸፍነው ሲሆን፣ ኑሯቸውንም ከእስራኤል ሊፈጸምብን ይችላል ከሚሉት ግድያ ለማምለጥ ተደብቀው ነው የሚመሩት።
ታጣቂው ቡድን የፈጸመውን ጥቃት በማቀድ እና በማደራጀት በአሁኑ ወቅት ጉልህ ሚና አላቸው ተብለው የሚታመኑት የሐማስ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ክንፍ ቁልፍ ሰዎችን ማንነት እነሆ።
ኢስማኤል ሃኒያህ
ቅጽል ስሙ አቡ አል-አቢድ የሆነው ኢስማኤል አብደል ሳላም ሃኒያ የተወለዱት በፍልስጤማውያን የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ነው። የሐማስ ፖሊት ቢሮ ኃላፊ ሲሆኑ፣ ከ2006 (እአአ) ጀምሮ አስረኛው የፍልስጤም መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን በቅተው ነበረ።
ቀደም ሲል በእስራኤል ለሦስት ዓመታት በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ ከሌሎች የሐማስ መሪዎች ጋር አስቸጋሪ ሁኔታን ባሳለፉበት በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል ወደ ሚገኝ ሰው ወደ ማይኖርበት አካባቢ በግዞት ቆይተዋል።
ከግዞት በኋላም ወደ ጋዛ ተመልሰው የሐማስ መንፈሳዊ መሪ የሼክ አህመድ ያሲን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ በቡድኑ ውስጥ ያላቸውን ሥልጣን አጠናከሩ፣ በሐማስ የፍልስጥኤም ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ታጭተው ለመሾም በቅቷተዋል።
ነገር ግን የሐማስ ቃሳም ብርጌድ በርካታ ሰዎች ከሞቱበት የአንድ ሳምንት ግጭት በኋላ የፍልስጥኤሙ ፕሬዝዳንት የማህሙድ አባስ ፓርቲ የሆነው ፋታህ ተወካዮችን ከጋዛ ሰርጥ በማባረሩ ፕሬዝዳንቱ በአጸፋው ለአንድ ዓመት ከቆዩበት የጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበር ሃኒያን አባረሩ።
ሃኒያ ከሥልጣን መወገዳቸውን ተቃውመውታል። ከዚያም በኋላ ከፋታህ ጋር እርቅ እንዲወርድ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2017 ደግሞ የሐማስ ፖሊት ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተመረጡ ሲሆን፣ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ የአሜሪካ መንግሥት ሃኒያን ሽብርተኛ ብሎ ፈርጆታል።
ሞሐመድ ዳይፍ
ጋዛ ውስጥ በ1965 (እአአ) የተወለደው ሞሐመድ ዳይፍ አል-ማስሪ በቅጽል ስሙ “አቡ-ኻሊድ” ወይም “አል-ዳይፍ” የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የሆነው የኢዝ አል-ቃሳም ብርጌድ መሪ ነው።
በፍልስጥኤማውያን ዘንድ “ዋነኛው አንቀሳቃሽ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ እስራኤላውያን ደግሞ “የሞት መልዕክተኛ” ወይም “ባለዘጠኝ ነፍሱ ተዋጊ” በሚል ይጠራል።
ሞሐመድ ዳይፍ ጋዛ ውስጥ ከሚገኘው እስላማዊ ዩኒቨርስቲ ባዮሎጂ አጥንቶ በዲግሪ የተመረቀ ሲሆን፣ በዩኒቨርስቲ ቆይታው ለትወና እና ለቲያትር ባለው ፍቅር እንዲሁም የኪነ ጥበብ ቡድን በማቋቋሙ ይታወቃል።
ዳይፍ ሐማስ መመሥረቱ ሲገለጽ ቡድኑን የተቀላቀለው በሙሉ ልብ አልነበረም። በ1989 (እአአ) ለሐማስ ወታደራዊ ቡድን ይሠራል ተብሎ በእስራኤል ባለሥልጣናት ከተያዘ በኋላ ያለፍርድ ቤት ውሳኔ ለ16 ወራት ታስሮ ነበር።
በእስር ላይ በቆየበት ጊዜም ዳይፍ ከዛካሪያ አል-ሾርባጊ እና ከሳላህ ሺሃዲህ ጋር በመሆን ከሐማስ የተለየ የእስራኤል ወታደሮችን የሚማርክ ቡድን ለመመሥረት ተስማማ። ይህ እንስቃሴ ነው እንግዲህ ጎልብቶ አል-ቃሳም ብርጌድ ለመሆን የቻለው።
ዳይፍ ከእስር ከተፈታ በኋላ የኢዝ አል-ቃሳም ብርጌድ ወታደራዊ ቅርጽ በመያዝ መንቀሳቀስ ጀመረ፣ ዳይፍም ከሌሎች የቃሳም መሪዎች ጋር በመሆን የቡድኑ ቀዳሚ መሥራች ለመሆን ቻለ።
ዳይፍ የሐማስ ተዋጊዎች ከጋዛ ተነስተው ወደ እስራኤል እንዲገቡ የሚያስችላቸውን የመሬት ውስጥ መተላለፊያ ዋሻን የቀየሰው እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሮኬቶችን በአንድ ጊዜ የመተኮስ ሃሳብን ካራመዱት መካከል አንዱ ነው።
ከሁሉም በላይ በእስራኤል ከሚቀርቡበት ከባባድ ክሶች መካከል የሐማስ ቦምቦችን ይሰራ የነበረውን የያህያ አያሽ ግድያን ለመበቀል እንደ አውሮፓውያኑ 1996 መጀመሪያ ላይ 50 እስራኤላውያን የተገደሉባቸውን የአውቶብስ የቦምብ ጥቃቶች፣ እንዲሁም በ1990ዎቹ አጋማሽ ተማርከው የተገደሉ ሦስት እስራኤላውያን ጉዳይ ይጠቀሳሉ።
እስራኤል ዳይፍን በ2000 ላይ ይዛ አስራው የነበረ ቢሆንም፣ ሁለተኛው የፍልስጥኤማውያን አመጽ ሲቀሰቀስ ለማምለጥ ችሏል። ከዚያ በኋላም የት እንዳለ አይታወቅም።
አስካሁን የሚታወቁ የዳይፍ ሦስት ፎቶዎች አሉ። አንደኛው በጣም ያረጀ፣ ሁለተኛው ጭምብል አድርጎ እና ሦስተኛው ጥላውን የሚያሳዩ ናቸው።
ዳይፍ በጣም አደገኛ የሚባል የመግደል ሙከራ የተደረገበት በ2002 (እአአ) ነበር። በጥቃቱ ዳይፍ ተዓምር በሚባል ሁኔታ ቢተርፍም አንድ ዐይኑን አጥቷል። አስራኤል ግን በጥቃቱ በተጨማሪ አንድ እጁን እና እግሩን ማታቱን እንዲሁም በተደጋጋሚ በተፈጸሙበት የግድያ ሙከራዎች ምክንያት የመናገር ችግር ገጥሞታል ትላለች።
በአውሮፓውያኑ 2014 የእስራኤል ሠራዊት ለ50 ቀናት የቆየ ጥቃትን በጋዛ ሰርጥ ላይ ባካሄደበት ጊዜ ዳይፍን ለመግደል ሳይችል ቢቀርም፣ ሚስቱን እና ሁለት ልጆቹን ገድሏል።
የሐማሱ ወታደራዊ ክንፍ መሪ ዳይፍ የሚለውን ስም የወሰደው “እንግዳ” ከሚለው የአረብኛ ቃል ነው። ምክንያቱም የእስራኤልን ግድያ ለማምለጥ አንድ ቦታ ላይ ለረጅም ጊዜ ስለማይቆይ እና በየምሽቱ ለማደሪያነት የሚጠቀምብትን ስፍራ ስለሚቀያይር ነው።
መርዋን ኢሳ
በልጅንት ዕድሜው ሐማስን የተቀላቀለው መርዋን ኢሳ ወይም “የማይታየው ሰው” የሞሐመድ ዳይፍ ቀኝ እጅ ነው። የኢዝ አል-ዲን አል-ቃሳም ብርጌድ ምክትል አዛዥ ሲሆን፣ የሐማስ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ቢሮ አባልም ነው።
በሐማስ ውስጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ምክንያት በመጀመሪያው የፍልስጥኤማውያን አመጽ “ኢንቲፋዳ” ወቅት በእስራኤል ተይዞ ለአምስት ዓመታት በእስር ላይ ቆይቷል።
“የቃል ሳይሆን ተግባር ሰው ነው” የምትለው እስራኤል ኢሳ በሕይወት እስካለ ድረስ ከሐማስ ጋር የምታደርገው “የዕውቀት ፍልሚያ” ይቀጥላል ብላለች። ብልህ መሆኑን ስትመሰክርም “ፕላስቲክን ወደ ብረት መቀየር የሚችል” ስትል ትገልጸዋለች።
ድንቅ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች የነበረው ኢሳ፣ ከእስራኤል እስር ቤት ከወጣ በኋላ የፍልሥጥኤም ባለሥልጣናት ከ1997 (እአአ) አንስቶ ለሦስት ዓመታት አስረው ሲለቁት የአል-ቃሳም ብርጌድን ወታደራዊ ሥርዓት በማዘጋጀት በኩል ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
በሐማስ ውስጥ በነበረው ወሳኝ ሚና የተነሳም በእስራኤል የተፈላጊዎች ዝርዝር ውስጥ ገብቶ በ2006 (እአአ) ከዳይፍ እና ከሌሎች የብርጌዱ መሪዎች ጋር ስብሰባ ላይ ሳለ የግድያ ሙከራ ተደርጎበታል። በዚህም የመቁሰል ጉዳት ቢደርስበትም የእስራኤል እሱን የማጥፋት ግብ ሳይሳካ ቀርቷል።
በ2014 እና በ2021 ሁለት ጊዜ የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ጋዛ ውስጥ የሚገኘውን ቤቱን ያወደሙት ሲሆን፣ በዚህም ወንድሙ ተገድሏል።
ኢሳ እስራኤላዊውን ታጋች ወታደር ጊላድ ሻሊትን ለማስለቀቅ የእስረኞች ለውውጥ በተደረገበት ጊዜ ከተነሳው የቡድን ፎቶ ውጪ የፊቱ ገጽታ ከዚያ በፊት ምን ይመስል እንደነበር አይታወቅም።
አቡ አል-ባራ በሚለው የትግል ስሙ የሚታወቀው ኢሳ፣ ያለፈው ሳምንትን ጨምሮ በተለያዩ ወቅቶች ወደ እስራኤል ውስጥ ዘልቆ በመግባት በተፈጸሙ ጥቃቶች፣ እንዲሁም በሌሎች እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሁሉ የእሱ ጥንቃቄ የተሞላባቸው ዕቅዶች እንዳሉ ይታመናል።
ያህያ ሲንዋር
በጋዛ ሰርጥ የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ኃላፊ የሆነው ያህያ ኢብራሂም አል-ሲንዋር የተወለደው 1962 (እአአ) ሲሆን፣ የቡድኑ የደኅነት አገልግሎት መሥራች ነው። ይህ “ማጂድ” የሚባለው የደኅንነት ዘርፍ ተጠርጣሪ የእስራኤል ሰላዮች ላይ ምርመራ ማድረግን እና የእስራኤል የደኅንነት ወኪሎችን መለየትን የመሳሰሉ የሐማስ ውስጣዊ የደኅንነት ሥራዎችን ያከናውናል።
ሲንዋር በተለያየ ጊዜ ለእስር የተዳረገ ሲሆን፣ በመጨረሻም በእስራኤል የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ነበር። ነገር ግን ጊላድ ሻሊት የተባለውን የእስራኤል ወታደር ከሐማስ ለማስለቀቅ በተደረገ የእስረኞች ልውውጥ አማካይነት ተለቆ በሐማስ ውስጥ ወደ ነበረው ከፍተኛ ሥልጣን ተመለሰ።
በመስከረም 2015 (እአአ) አሜሪካ የሲንዋርን ስም “ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች” ከምትላቸው ጥቁር መዝገብ ውስጥ አስገብታዋለች።
ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ኢስማኤል ሃኒያህን በመተካት በጋዛ ውስጥ የሐማስ ፖሊት ቢሮ የበላይ በመሆን ተመረጠ።
አብዱላህ ባርጉቲ
ባርጉቲ በ1972 ኩዌት ውስጥ ተወልዶ ከሁለተኛው የባሕረ ሰላጤው ጦርነት በኋላ ወደ ዮርዳኖስ ለመኖር መጥቷል።
ፈንጂዎችን መሥራት ለመማር ያበቃውን የኤሌክትሪካል ምህንድስና ትምህርትን ለሦስት ዓመት ለመማራር ወደ ደቡብ ኮሪያ ከመሄዱ በፊት የዮርዳኖስ ዜግነት ነበረው። ከዚያም ወደ ፍልስጥኤም የመግባት ፈቃድ በማግኘቱ ትምህርቱን ሳይጨርስ ቀረ።
አንድ ዕለት የአክስቱ ልጅ የሆነውን ቢላልን ዌስት ባንክ ውስጥ ወደሚገኝ ራቅ ያለ ስፍራ ወስዶ ችሎታውን እስኪያሳየው ድረስ ማንም ፈንጂዎችን እንደሚሠራ አያውቅም ነበር። ቢላልም ያየውን በመንገር ባርጉቲን ከአለቃው ጋር አስተዋውቆት ቃሳም ብርጌድን ተቀላቀለ።
ከዚያም ለቡድኑ ፈንጂዎችን እና መርዛማ ንጥረ ነገሮችን እንዲሁም የፈንጂ ማቀጣጠያዎችን ሠርቷል። ባርጉቲ በሚኖርበት ከተማ ውስጥ በሚገኝ መጋዘን ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ ቁሶችን የሚያመርት ልዩ ፋብሪካም አቋቁሟል።
ከ20 ዓመት በፊት ደግሞ በአጋጣሚ በእስራኤል ልዩ ኃይሎች ተይዞ ለሦስት ወራት በምርመራ ላይ ቆይቷል።
ለበርካታ እስራኤላውያን ሞት ተጠያቂ ነው የተባለው ባርጉቲ ፍርድ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ሲቀርብ የሟች ቤተሰቦች በችሎት ላይ ታድመው ነበር።
በመጨረሻም አስካሁን በአስራኤል ምናልባትም በዓለም ታሪክ በጣም ረጅሙ ነው የተባለው ብይን ተላልፎበታል። በዚህም 67 የዕድሜ ልክ እና 5,200 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።
ባርጉቲ ብቻውን ተነጥሎ በመታሰሩ የረሃብ አድማ በማድረጉ የብቸኝነት እስሩ እንዲያበቃ ተደርጓል። በእስር ቤት ሳለ “የጨለማው ልዑል” በሚል ርዕስ መጻፍ ጽፎ ቅጽል ስሙ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል።
በመጽሐፉ ውስጥም ስለ እራሱ ሕይወት እና ከሌሎች እስረኞች ጋር በመሆን እንዴት ፈንጂዎችን የእስራኤል ወታደራዊ ኬላዎችን እንደሚያሳልፉ፣ እንዴት ከርቀት የቦምብ ጥቃት ተልዕኮዎችን እንደሚፈጽም እና ሌሎችንም ነገሮች በመጻፉ ውስጥ ተርኳል።
ኻሊድ ሜሻል
አቡ አል-ዋሊድ ተብሎ የሚታወቀው ኻሊድ ሜሻል በ1956 (እአአ) ዌስት ባንክ ውስጥ ነው የተወለደው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እዚያው ጀምሮ ወደ ኩዌት በመሄድ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቋል።
ሜሻል ከሐማስ መሥራቾች መካከል እንደ አንዱ የሚታይ ሲሆን፣ ከምሥረታው ጀምሮም የፖሊት ቢሮ አባል ሆኖ ቆይቷል። ለአስር ዓመት ያህልም የፖሊት ቢሮው ፕሬዝዳንት ነበር። ከዚያም በ2004 (እአአ) የሼክ አህመድ ያሲን ሞትን ተከትሎ በመሪነት ተሹሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ የሞሳድ ኃላፊ ሜሻልን ለመግደል የሚያስችል ዕቅድ እንዲያዘጋጁ በቀጥታ ባዘዟቸው መሠረት በ1997 (እአአ) የመግደል ሙከራ ተደርጎበታል።
በሐሰተኛ የካናዳ ፓስፖርት ወደ ዮርዳኖስ የገቡ የሞሳድ ወኪሎች ዋና ከተማዋ አማን ውስጥ ጎዳና ላይ ኻሊድ ሜሻልን ጠብቀው መርዛም ንጥረ ነገር በመርፌ ወግተውታል።
የዮርዳኖስ ባለሥልጣናትም የግድያ ሙከራው ላይ ደርሰውበት በድርጊቱ ከተሳተፉት መካከል ሁለቱን ለመያዝ ችለዋል። ሟቹ የዮርዳኖስ ንጉሥ ሁሴን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሻል የተወጋውን መርዝ የሚያረክሰውን መድኃኒት እንዲሰጡ ቢጠይቁም ኔታኒያሁ መጀመሪያ ላይ ፈቃደኛ አልነበሩም።
ሜሻልን ለመግደል ዮርዳኖስ ውስጥ የተደረገው ሙከራ ፖለቲካዊ ገጽታ በመያዙ፣ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ጣልቃ ገብተው ኔታኒያሁ የመርዙን ማርከሻ እንዲሰጡ በማስገደዳቸው ሕይወቱ ሊተርፍ ችሏል።
ማህሙድ ዛሃር
ማህሙድ ዛሃር ከፍልስጥኤማዊ አባት እና ከግብፃዊት እናት ጋዛ ውስጥ በ1945 ነው የተወለደው። የልጅነት ጊዜውንም ያሳለፈው በግብፅ ኢስማኤሊያ ሲሆን፣ አስከ ሁለተኛ ደረጃ ያለውን ትምህርቱን ግን የተከታተለው ጋዛ ውስጥ ነው።
ከዚያም የመጀመሪያ ዲግሪውን በሕክምና ካይሮ ከሚገኘው አይን ሻምስ ዩኒቨርስቲ፣ ከዚያም ሁለተኛ ዲግሪውን በቀዶ ሕክምና አግኝቷል። በፖለቲካ አቋሙ ምክንያት የእስራኤል ባለሥልጣናት ከሥራው እስኪያባርሩት ድረስም በጋዛ እና ኻን ዩኒስ ውስጥ ባሉ ሆስፒታሎች በዶክተርነት ሰርቷል።
ዛሃር ከሐማስ ቀዳሚ መሪዎች መካከል እንደ አንዱ ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን፣ የቡድኑ የፖለቲካ አመራር አባል ነው።
ማህሙድ ዛሃር ሐማስ ከተመሠረተ ከስድስት ወራት በኋላ በእስራኤል ተይዞ ለስድስት ወራት በአስር ላይ ቆይቷል። በወቅቱም ለአንድ ዓመት በግዞት ወደ አስቸጋሪ ቦታ ከታለኩት የቡድኑ አባላት መካከል አንዱ ነበር።
በ2005 (እአአ) በተካሄደ የምክር ቤት ምርጫ ሐማስ በበላይነት ካሻነፈ በኋላ ፍልስጥኤማውያንን ለሁለት የከፈለው ግጭት ተፈጥሮ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢስማኤል ሃኒያህን ከሥልጣን አስከሚያባርሩ ድረስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ ተሹሞ ነበር።
በ2003 (እአአ) እስራኤል ዛሃርን ለመግደል ጋዛ ውስጥ በሚገኘው ቤቱ ላይ 500 ኪሎ ግራም ይመዝናል ተብሎ የሚታመን ቦምብ ከኤፍ-16 አውሮፕላን ላይ ጥላ ነበር። ነገር ግን ዛሃር ከግድያ ሙከራው ቀላል ጉዳት ደርሶበት ሲተርፍ ታላቅ ወንድሙ ተገድሏል።
በ2008 ደግሞ የቃሳም ብርጌድ አባል የሆነው ሁለተኛ ልጁ እስራኤል ጋዛ ውስጥ ባካሄደችው ጥቃት ከተገደሉት 18 ሰዎች እንዱ ነበር።
ዛሃር ምሁራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሥነ ጽሁፋዊ ሥራዎች ያሉት ፀሐፊ ስለመሆኑም ይነገርለታል። ከእነዚህ ውስጥም ቅዱስ ቁርዓንን ያጣቀሰ ወቅታዊ የማኅበረሰቡን ችግር የሚተነትን ጽሁፍ፣ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ለተጻፈ መጽሐፍ የሰጠው ምላሽ እና ረጅም ልቦለድ የጠቀስለታል።