እስራኤል በጋዛ ዒላማ አድርጌያቸዋለሁ ያለቻቸው የሐማስ ዋሻዎች

ሐማስ ያልተጠበቀ የተባለውን ጥቃት መሰንዘሩንተከትሎ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ዋሻዎችን ዒላማ ማድረጓን አስታውቃለች።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ "በጋዛ ሰርጥ ሰላማዊ ነዋሪዎች በአንደኛው ክፍል ሲኖሩ ሐማስ ደግሞ በሌላኛው ክፍል [በመሬት ስር ባለው] ውስጥ ይገኛል። እኛም ሐማስ ወደገነባው ሁለተኛው የመሬት ስር ለመድረስ እየሞከርን ነው" ብለዋል።

"እነዚህ ለጋዛ ነዋሪዎች የተሠሩ አይደሉም። ለሃማስ እና ለሌሎች አሸባሪዎች እስራኤል ላይ ሮኬቶችን መተኮሳቸው እንዲቀጥሉ፤ ዘመቻ ለማቀድ፣ አሸባሪዎችን ወደ እስራኤል ለማስረግ ብቻ የተዘጋጁ ናቸው” ብለዋል።

እስራኤል "ጋዛ ምድር ውስጥ የባቡር መስመር" የሚል ስያሜ የሰጠችውን የዋሻ መጠን ለማወቅ በጣም ከባድ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ከ 41 ኪ.ሜ ርዝመትና 10 ኪ.ሜ ስፋት ባለው ጋዛ ሰርጥ በመዘርጋቱ እንደሆነ ይታመናል።

እአአ በ2021 የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ እስራኤል ጦር በፈጸመው የአየር ድብደባ ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝም ዋሻዎችን ማውደሙን አስታውቋል።

ሐማስ ዋሻዎቹ 500 ኪ.ሜ እንደሚረዝሙና 5 በመቶው ብቻ መመታቱን አስታውቋል። የተጎዳው ብሏል። ለማነጻጸር ያህል ለንደን የውስጥ ለውስጥ ባቡር 400 ኪሎ ሜትር ብቻ ይረዝማል።

የጋዛ ዋሻዎች ግንባታ የተጀመረው እስራኤል ጦሯን እና ያሰፈረቻቸውን ዜጎች ከአካባቢው እአአ በ2021 ከማስወጣቷ በፊት ነው።

ሐማስ ሰርጡን ከሁለት ዓመት በኋላ ሲቆጣጠር ግንባታው ተጠናክሮ ቀጠለ። ይህም በደህንነት ስጋት እስራኤል እና ግብጽ ለደህንነት የሸቀጦች እና የሰዎችን እንቅስቃሴ እንዲገድቡ ምክንያት ሆነ።

በአንድ ወቅት 2500 በሚደርሱት ዋሻዎች ሐማስ እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች እቃዎችን፣ ነዳጅ እና የጦር መሳሪያዎችን ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር ተጠቅመውበታል።

እስራኤል እቃዎች በምትቆጣጠረው ክልል በኩል እንዲገባ በመፍቀዷ የዋሻዎቹ ሚና ቀነሰ። ግብጽ ደግሞ በማውደም እና በውሃ በማጥለቅለቅ በዋሻዎቹ ያለውን ህገወጥ የኮንትሮባንድ ንግዱን ዘጋች።

ሐማስ እና አንጃዎቹ የእስራኤል ጦርን ለማጥቃት በድጋሚ ዋሻዎችን መቆፈር ያዙ።

እአአ በ2006 ታጣቂዎች አንዱን ዋሻ ተጠቅመው ሁለት የእስራኤል ወታደሮችን ገደሉ። ጊላድ ሻሊት የተባለውን ወታደር ደግሞ ለአምስት ዓመታት አግተው ቆይተዋል።

የእስራኤል ጦር እአአ በ2013 1.6 ኪሜ የሚረዝም እና 18 ጥልቀት ያለው ዋሻ አግኝቶ ነበር። ኮንክሪት ጣሪያና ግድግዳ ያለው ዋሻ ከጋዛ ሰርጥ እስከ እስራኤሏ ኪቡትዝ የተዘረጋ ነው። አካባቢው ነዋሪዎች ያልተለመደ ድምጽ በመስማታቸው ዋሻው መታወቁ ተገልጿል።

በቀጣዩ ዓመት እነዚህን “የሽብር ዋሻዎች” በመጠቀም የሚሰነዘርን ጥቃት መከላከል አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ የእስራኤል ጦር ከፍተኛ የአየር እና የምድር ጥቃት ድንበር አካካቢ ፈጸሟል።

በጦርነቱ ወቅት ከ30 በላይ ዋሻዎችን ወድሟል ሲል ጦሩ አስታውቋል። ታጣቂዎች ግን አራት የእስራኤል ወታደሮች የተገደሉበትን ጥቃት ለመፈፀም አንዱን ዋሻ ለመጠቀም ችለዋል።

እስራኤል በሚገኘው ሪችማን ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት ዶ/ር ዳፍን ሪችመንድ-ባራክ የምድር ውስጥ ጦርነት ባለሙያ ናቸው።

"የድንበር ተሻጋሪ ዋሻዎች ቀላል ናቸው። ምንም ዓይነት ምሽግም የላቸውም ። የተቆፈሩት የእስራኤልን ግዛት ለመውረር በሚል አንድ ዓላማ ብቻ ነው" ብለዋል።

"የጋዛ ዋሻዎች የተለዩ ናቸው። ምክንያቱም ሐማስ በመደበኛነት እየተጠቀመባቸው ነው ። ረዘም ላለ ጊዜ በውስጣቸው ለመቆየትም የበለጠ ምቹ ናቸው። በእርግጠኝነት ለረዥም እና ዘላቂ ጊዜ በሚሆን መልኩ የተደራጁ ናቸው።"

"አመራሮቹ እዚያ ይደበቃሉ። የዕዝ እና የቁጥጥር ማዕከላትም አሏቸው። እንደ ትራንስፖርትና መገናኛ መስመሮችም ይጠቀሙባቸዋል። ኃይል፣ መብራትና የባቡር ሀዲድ የተገጠመላቸው ናቸው። ለመንቀሳቀሰም ሆነ በቀላሉ ለመቆም ያስችላሉ" ብለዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሐማስ የዋሻ ግንባታ እና የጦርነት ጥበብ "የተሟላ" ይመስላል። በአሌፖ የሶሪያ አማፂ ተዋጊዎችን እና በሞሱል የሚገኘውን የእስላማዊ መንግስት (አይ ኤስ) ጂሃዲስት ቡድንን በመመልከት ብዙ የተማረ ይመስላል።

የጋዛ ዋሻዎች ከመሬት በታች እስከ 30 ሜትር ድረስ እንደሚገነቡ ይገመታል። በቤቶች፣ መስጊዶች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች የህዝብ ህንጻዎች አካበቢ መግቢያ በሮች አሏቸው። ይህም ታጣቂዎች እንዳይታወቁ ያስችላቸዋል ተብሎ ይታመናል።

ግንባታዎቹ የአካባቢውን ህዝብ ዋጋ አስከፍለዋል። ሐማስ በእርዳታ ስም ለጋዛ የተሠጠውን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እና በጦርነት ለወደሙ ግንባታዎች የታቀደ በአስር ሺህ ቶን የሚቆጠር ሲሚንቶ በመውሰድ ለዋሻዎቹ ግንባታ አውሏል ሲል የእስራኤል ጦር ይከሳል።

ሐማስ ባለፈው ቅዳሜ በእስራኤል በፈጸመው ጥቃት ድንበር ተሻጋሪ ዋሻዎችን ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል። በጥቃቱ ቢያንስ 1300 ሰዎች ተገድለዋል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ሲቪሎች ናቸው። 150 የሚሆኑትን ደግሞ አፍኖ ወስዷል። በኪቡትዝ በምትገኘው ክፋር አዛ አካባቢ በደርዘን የሚቆጠሩ ሠላማዊ ሰዎች የተጨፍጭፈዋል። በአካባቢው ዋሻ መውጫ መገኘቱን ዘገባዎች ጠቁመዋል።

ዘገባዎቹ ከተረጋገጡ ዋሻው የተገነባው እስራኤል በኮንክሪት አጥር ስር ነው ማለት ነው። አጥሩ ዘመን ያፈራውን ውስብስብ የጸረ-ዋሻ ቴክኖሎጂ ያቀፈም ነበር። እስራኤል በ2021 ነበር ተከላውን ያጠናቀቀችው።

ዶ/ር ሪችመንድ-ባራክ ይህ አስደንጋጭ እንደሚሆን ተናግረዋል። የትኛውም የዋሻ ማወቂያ ዘዴ ግን ሙሉ ለሙሉ አስተማማኝ አይደለም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። "በጦርነት ውስጥ ዋሻዎች ጥቅም ላይ የሚውሉት ለመከላከል የሚያስችል መንገድ ስለሌላቸው ነው" ብለዋል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የምድር ጦሯን ለማንቀሳቀስ በመዘጋጀት ላይ የምትገኘው እስራኤልም ሆነች ህብረተሰቡ ጦሩ በጋዛ ያለውን የሐማስ ዋሻዎች ሊያጠፋ ይችላል ብሎ ማመን ከእውነታው የራቀ ሊሆን ይችላል ብለው ያስጠነቅቃሉ።

"ሲቪሎች በማንኛውም ምክንያት የማይለቁባቸው የዋሻው ክፍሎች ይኖራሉ... አንዳንዶቹ ዋሻዎች የማይታወቁ ናቸው። ለአንዳንዶቹ ደግሞ ቁሳዊ ጉዳቱ በጣም ከፍተኛ ይሆናል" ብለዋል።

ዋሻዎቹን ማውደም ከፍተኛ የህይወት መጥፋት ያስከትላል። ይህ ደግሞ የእስራኤልን የምድር ጦር፣ ፍልስጤምማዊያን ሲቪሎች እና ታጋቾች ሊያካትት ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ከቅዳሜ ጀምሮ እስራኤላውያን በጋዛ በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ ከ1,500 በላይ ፍልስጤማውያን (ብዙዎቹ ሲቪሎች ናቸው) ተገድለዋል።

"ሐማስ የሲቪሎችን እንደጋሻ መጠቀምን ተክኖበታል። ጥቃት እንደሚፈጸም ካወቁ ንጹሃን ዜጎችን በየህንፃዎቹ ላይ ያስቀምጣሉ። ይህ ደግሞ እስራኤል ጥቃቷን ደጋግማ እንድትሰርዝ ያስገድዳታል" ብለዋል ዶ/ር ሪችመንድ-ባራክ።

“ሐማስ በዚህ በመካኑ በዋሻዎቹ ውስጥ በቀላሉ እስራኤላዊያን፣ አሜሪካዊያን እና ሌሎች ታጋቾችን ማስገባት ይችላል።“

እአአ በ 2021 በነበረው ግጭት በጋዛ ከተማ ላይ በተሰነዘረ ተከታታይ የአየር ድብደባ ሦስት የመኖሪያ ሕንፃዎችን መሬት ፈርሰው 42 ሰዎች ተገድለዋል ።

የእስራኤል ጦር ዒላማ ያደረገው ከመሬት በታች ያሉትን ዋሻዎች መሆኑን ጠቅሷል። ዋሻዎቹን ለማፍረስ ግን ሕንፃውንም ማፍረስ ግድ ብሏል።

ዋሻዎቸው እስራኤል ጦር ያለውን የቴክኖሎጂ እና የስለላ የበላይነትም መና የሚያስቀር ነው። የከተማ ጦርነትን አስቸጋሪነት ከማሳየት ባለፈ ለእስራኤል ወታደሮች ሞት ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲሉ ዶ/ር ሪችመንድ ባራክ ተናግረዋል።

"ሐማስ መላውን መረብ ለማጥመድ በቂ ጊዜ ነበረው። ወታደሮቹ ወደ ዋሻው እንዲገቡ ከፈቀዱ በኋላ በመጨረሻም ሁሉንም ነገር ማፈንዳት ይችላሉ።"

"[ወታደሮቹን] ድንገተኛ ጥቃት ሊያፍኑም ይችላሉ። አደጋ ሊሆኑ የሚችሉ እንደኦክሲጅን ማጣት፣ ጠላትን በአንድ-ለአንድ መዋጋት እና የተጎዱ ወታደሮችን ማዳን ፈጽሞ የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል” ብለዋል።

“ዋሻዎች ሊኖሩ ይችላሉ ተብለው የሚጠረጥሩበትን ቦታዎች ዋሻዎቹ ውስጥ ሳይገቡ መጠበቅ ደግሞ አንድ አካባቢን ተቆጣጥሮ ከመጠበቅ የተለየ ነው። የማይታየውን ነገር መጠበቅ የግድ ይሆናል” ሲሉ አክለዋል።

የእስራኤል ጦር ስጋቶቹን የሚቀንስባቸው አንዳንድ መንገዶችም ይኖራሉ።

በሱፋን ግሩፕ የጸጥታ አማካሪ ድርጅት የምርምር ዳይሬክተር ሆኑት ኮሊን ክላርክ ድሮኖችን (ሰው አልባበራሪዎችን) እና ሰው አልባ ተሽከርካሪዎችን በመላክ ዋሻዎቹ ማጥናት እና ወጥመዶችን መለየትን ይጨምራል ይላሉ።

የጦር አውሮፕላኖች ከመፈንዳታቸው በፊት ወደ መሬት ውስጥ ዘልቀው የሚገቡትን ቦምቦችንም ሊጥሉ ይችላሉ። ከተማው ጥቅጥቅ ያለ በመሆኑ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ።