ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እያንዳንዱ የሐማስ አባል በሞት ጥላ ሥር መሆኑን ኔታንያሁ ተናገሩ
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እያንዳንዱ የሐማስ አባል በሞት ጥላ ሥር መሆኑን ተናገሩ።
ኔታንያሁ ይህን ያሉት በአገሪቷ ከተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ መንግሥት የመጀመሪያ ስብሰባ በኋላ ነው።
ከእርሳቸው በተጨማሪም የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ቤኒ ጋንትዝ አሁን የጦርነት ጊዜ ነው ብለዋል።
ሆኖም የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ከኔታንያሁ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸው፣ እስራኤል ዘመቻዋን በጦርነት ሕግ መሠረት ማድረግ እንዳለባት አሳስበዋል።
በእስራኤል የሟቾች ቁጥር 1 ሺህ 200 የደረሰ ሲሆን፣ ከ1 ሺህ 100 በላይ የሚሆኑት ሰዎች የተገደሉት እስራኤል በጋዛ ላይ በፈፀመችው የአየር ጥቃት ነው።
የእስራኤላውያንን ቁጣ እና ፍርሃት እንረዳለን ያሉት ፕሬዚደንት ባይደን፣ እስራኤል የጀኔቫ ስምምነቶችን እንድታከብር አሳስበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ባይደን የሐማስን ጥቃት የደገፈችው ኢራን ጥንቃቄ እንድታደርግ አስጠንቅቀዋል።
ቀደም ብሎ ረቡዕ ዕለት ኔታንያሁ እና ጋንትዝ ሰፊ ተቃውሞ አስነስቶ የነበረውን መራር ፖለቲካዊ ልዩነት ወደ ጎን በማለት በጋራ ለመቆም ተስማምተዋል።
ጋንትዝ አዲስ የተቋቋመው መንግሥት አንድ መሆኑንና ሐማስን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ዝግጁ መሆኑን ለእስራኤል ዜጎች ተናግረዋል።
አዲስ የተቋቋመው የጦር ካቢኔ ከኔታንያሁ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ጋንትዝ እና ከቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር በተጨማሪ የመከላከያ ሚኒስትሩን ዮቭ ጋላትን ያካትታል።
ሆኖም የአገሪቷ ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዬር ላፒድ ይህንን ጥምረት አልተቀላቀሉም።
ኔታንያሁ እና ጋንትዝ በጋራ በሰጡት መግለጫ ለላፒድ በጦር ካቢኔው መቀመጫ እንደሚተውላቸው ተናግረዋል።
በስምምነቱ መሠረት ጦርነቱ በሚካሄድበት ጊዜ “የጦርነቱን ሂደት ከሚመለከቱ ጉዳዮች በስተቀር ማንኛውም ዓይነት ሕግም ሆነ የመንግሥት ሃሳብ ለውሳኔ እንደማይቀርብ" ተገልጿል።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣንን እንዲይዙ የተሾሙ ሰዎች የኃላፊነት ጊዜ በጦርነቱ ወቅት ሁሉ የሚቀጥል ይሆናል።
ከሦስቱ ባለሥልጣናት በተጨማሪ የጦርነቱ መሪ ካቢኔን በታዛቢነት የሚያገለግሉ የጦር ሥልት ባለሙያ የሆኑ ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ይካተቱበታል።
በታዛቢነት ካቢኔውን የተቀላቀሉት ጋንትዝ እና ጋዲ ኤስንኮት የቀድሞ የእስራኤል ጦር አዛዥ ናቸው።
አዲስ የጦር ካቢኔ መቋቋሙ የተገለጸው የሐማስ ታጣቂዎች ከጋዛ ሰርጥ ሆነው የከፈቱትን ጥቃቶች ተከትሎ ግጭቱ ለቀናት በቀጠለበት ወቅት ነው።
ቅዳሜ ዕለት ሐማስ ከከፈተው ድንገተኛ ጥቃት ጀምሮ እስካሁን በእስራኤል ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ሐማስም አረጋውያንና ሕጻናትን ጨምሮ 150 የሚደርሱ ሰዎችን አግቶ መውሰዱንም ገልጿል።
የእስራኤል ጦር ለሚያካሂደው የምድር ወረራ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በጋዛ ድንበር በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኙ ረቡዕ ዕለት አስታውቋል።
እስራኤል ከሐማስ በተጨማሪ በሌባኖስ ካሉ የሔዝቦላህ ታጣቂዎችና በሶሪያ ከሚገኙ ኃይሎች ጋር ተኩስ ተለዋውጣለች።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የመከላከያ ሚኒስትሩ ጋላት፣የፍልስጤም ግዛት ሙሉ በሙሉ በከበባ ውስጥ እንደገባች እና የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ውሃ እና የምግብ አቅርቦት መቆሙን ተናግረው ነበር። እስካሁን በጋዛ ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በአየር ጥቃት ተገድለዋል።
በእስራኤል የጋራ መንግሥት መመስረቱ ብሔራዊ ደኅንነቱን በሚቆጣጠሩት ኢታማር ቤን ግቪር ጨምሮ በሚኒስትሮች ድጋፍ አግኝቷል።
ግቪር “ለተመሰረተው አንድነት እንኳን ደስ አላችሁ። አሁን ማሸነፍ አለብን” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ኔታንያሁ እና ጋንትዝ በጋራ ለመስራት መስማማታቸው የተገለጸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና መንግሥታቸው ያወጣውን አወዛጋቢ የሕግ ማሻሻያ ረቂቅ ተከትሎ ለወራት የዘለቀ ተቃውሞ ከተካሄደ በኋላ ነው።
ተቃዋሚዎቹ በኔታንያሁ የፖለቲካ ተቀናቃኞች እንዲሁም በእስራኤል ጦር፣ ደኅነነት እና የጸጥታ አገልግሎት የቀድሞ ባለሥልጣናት፣ በቀድሞ የፍትሕ ኃላፊ እንዲሁም በታዋቂ የሕግ ባለሙያዎች እና የንግድ መሪዎች ድጋፍ ተደርጎላቸው ነበር።