ሐማስ ጥቃት ከመፈጸሙ ከቀናት በፊት ግብፅ እስራኤልን አስጠንቅቃ ነበር - አሜሪካ

ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከመክፈቱ ሦስት ቀናት ቀደም ብሎ ግብፅ እስራኤልን አስጠንቅቃ እንደነበር የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀመንበር ተናገሩ።

በአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ሚካኤል ማክ ኮውል ይህን ያሉት ለጋዜጠኞች ስለማስጠንቀቂያው በተናገሩበት ወቅት ነው።

ሆኖም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ፍፁም ሐሰት” ሲሉ የሊቀመንበሩን አስተያየት ውድቅ አድርገውታል።

የእሰራኤል የደኅንነት ተቋም በአገሪቱ 75 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም የተባለውን እና የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈውን የሐማስ ጥቃት እንዴት አስቀድሞ መከላከል አልቻለም በሚል በከፍተኛ ሁኔታ እየተብጠለጠለ ይገኛል።

ረቡዕ ዕለት በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ ለጋዜጠኞች በዝግ የደኅንነት ማብራርያ የሰጡት ማክ ኮውል “ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ባሉት ሦስት ቀናት ግብፅ እስራኤልን ማስጠንቀቋን እናውቃለን” ሲሉ መናገራቸውን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል - ኤኤፍፒ ዘግቧል።

“ምሥጢራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በዝርዝር ገብቼ መናገር አልፈልግም፣ ነገር ግን ማስጠንቀቂያው ተሰጥቶ ነበር” ሲሉ አክለዋል።

ኃላፊው ጨምረው “ጥያቄው መሆን ያለበት መረጃው በምን ያህል ደረጃ ተሰጥቷል የሚለው ነው” ብለዋል።

የግብፅ የደኅንነት መሥርያ ቤት ባለሥልጣናት በዚህ ሳምንት ካይሮ ውስጥ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ከሆነ በተደጋጋሚ በእስራኤል ጋዛ ውስጥ “አንዳች ትልቅ ነገር” መታቀዱን በመጥቀስ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ተናግረዋል።

ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የደኅንነት መሥርያ ቤቱ ኃላፊ “በጣም ትልቅ የሆነ ክስተት በቅርቡ እንደሚፈጠር ነግረናቸዋል። ትልቅ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ለማስጠንቀቂያችን ተገቢውን ክብደት አልሰጡትም” ብለዋል።

የካይሮ ባለሥልጣናት የእስራኤል አቻዎቻቸው በጋዛ ላለው የደኅንነት ስጋት ተገቢውን ትኩረት ነፍገው በዌስት ባንክ ላይ አተኩረዋል ይላሉ።

ረቡዕ ዕለት ኔታንያሁ እስራኤል አስቀድሞ ስለ ጥቃቱ ማስጠንቀቂያ ደርሷታል የሚለውን መረጃ “ ሙሉ በሙሉ የሐሰት መረጃ” ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

ከጋዛ ጋር ያለውን ድንበር የምትቆጣጠረው ግብፅ በርካታ ጊዜያት በእስራኤል እና በሐማስ መካከል እንደ አሸማጋይ ሆና አገልግላለች።

ቅዳሜ ዕለት ከ1ሺህ 500 በላይ ታጣቂዎች የጋዛን የዸኅንነት አጥር በተቀናጀ መልኩ በምድር፣ በአየር እንዲሁም በባሕር በመጣስ ጥቃት መክፈታቸው ይታወሳል።

በሐማስ ጥቃት በእስራኤል 1ሺህ 200 ሰዎች ሲሞቱ፣ እስራኤል ጋዛ ላይ በፈፀመችው የአጸፋ የአየር ጥቃት ደግሞ 1000 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።

እስራኤል የሐማስ አማፂያን መገኛ ናቸው ያለቻቸውን ሥፍራዎች በአየር እየደበደበች ሲሆን፣ የጋዛ ነዋሪዎች ግን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሙሉ በሙሉ እንደተቋረጠባቸው ተናግረዋል።

ሐማስ በበኩሉ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እስራኤል ለተፈጸመባት ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለባት ሲሉ የሰጡትን አስተያየት ግጭት አቀጣጣይ ሲል አውግዟል።

የሐማስን ጥቃትን ተከትሎ አሜሪካ የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቧን በምሥራቃዊ ሜዲትራንያን ያስጠጋች ሲሆን፣ ለእስራኤል ተጨማሪ የጦር መሣርያ እንደምትሰጥ ተናግራለች።