ወታደራዊ ምሥጢር ለቻይና የሰጠው የአሜሪካ ባሕር ኃይል ኃላፊ በእስራት ተቀጣ

ባሕር ኃይል

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

ጥብቅ ወታደራዊ መረጃ ለቻይና እንደሰጠ ያመነው የአሜሪካ ባሕር ኃይል ባለሥልጣን የሁለት ዓመታት እስር ተፈረደበት።

ዌንሄንግ ዣዎ የተባለው የ26 ዓመት ግለሰብ ባለፈው ጥቅምት ለቻይና ስለላ ተቋም መረጃ እንደሰጠና ጉቦም እንደተቀበለ አምኗል።

በካሊፎርንያ የባሕር ኃይል ነበር የሚሠራው።

አሜሪካ በኢንዶ-ፓስፊክ ቀጠና ያላትን የባሕር ላይ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ምሥጢር ነው አሳልፎ የሰጠው።

ስለ ወታደራዊ እንቅስቃሴ፣ የኦፕሬሽን ትዕዛዞችና እአአ ከ2021 እስከ 2023 ያለውን የመሠረተ ልማት መዋቅር ነው መረጃ እንዳስተላለፈ የተገለጸው።

አሜሪካ በቀጠናው ካላት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ባሻገር የኤሌክትሪክ ዲያግራሞችና ረቂቆችም ሰጥቷል ተብሏል። አሜሪካ በጃፓኗ ደሴት ኦኪናዋ ባላት ወታደራዊ መቀመጫ ስላለው መቆጣጠሪያ መሣሪያ ረቂቅ መረጃ አሳልፎ መስጠቱም ተጠቅሷል።

አሜሪካ በጃፓን ደሴት ያላት ወታደራዊ መቀመጫ በእስያ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ቁልፍ ነው።

ቀጠናውን የደኅንነት ጉዳዮች ዋነኛ መዳረሻ ያደረገችው አሜሪካ፣ የቻይናን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለመገዳደር ባለፉት ዓመታት የተለያዩ የጥምረት ሥራዎች በአካባቢው እያከናወነች ነው።

ከአጋር አገሮች ጋር በመሆን በቀጠናው ወታደራዊ ልምምድ አጠናክራለች።

መረጃውን አሳልፎ የሰጠው ግለሰብ ሁኔሜ በተባለ አካባቢ በሚገኝ ወታደራዊ መቀመጫ ነበር የሚሠራው።

የአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስቴር እንዳለው በጥብቅ ወታደራዊ ስፍራዎች በመግባት መረጃ ሰብስቧል።

“ውስብስብ የግንኙነት መስመር በመጠቀም መረጃውን አስተላልፏል” ተብሏል።

መረጃዎቹን ከላከ በኋላ በማጥፋት ከቻይና የስለላ ተቋም ጋር ያለውን ግንኙነት መደበቁም ተገልጿል።

ከነሐሴ 2021 እስከ ግንቦት 2023 ባሉት ጊዜያት ቢያንስ 14 ጊዜ ወደ 14,866 ዶላር ገደማ ተከፍሎታል።

ግለሰቡ የተወለደው ቻይና ሲሆን በዜግነት አሜሪካዊ ነው።

በ2009 አሜሪካ ገብቶ በ2012 ዜግነት አግኝቷል። ከአምስት ዓመት በኋላ በባሕር ኃይል ተቀጥሯል።

ባለፈው ነሐሴ ነው በቁጥጥር ሥር የዋለው። የቀረበበትን ክስም መፈጸሙን አምኗል።

የ20 ዓመታት እስር እንዲፈረድበት ተጠይቆ ለ27 ወራት እንዲታሰር ተወስኗል።

የአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስትር ምክትል ዐቃቤ ሕግ ጀነራል ማቲው ኦንሰል እንዳሉት፣ የቻይና የስለላ ተቋም በአሜሪካ ወታደራዊ መዋቅር ውስጥ ጥብቅ መረጃ የማግኘት ይሁንታ ያገኙ ባልደረቦችን ዒላማ ያደርጋል።

“በገንዘብ ያታልሏቸውና ጥብቅ የመንግሥት መረጃ ይወስዳሉ” ብለዋል።

“ዌንሄንግ ዣዎ አገሩን ለመከላከል የገባውን ቃል አጥፏል። የአሜሪካ ወታደሮችንም አደጋ ላይ ጥሏል” ብለዋል።

አምና ጂንቻኦ ዌይ የተባለ የ22 ዓመት ግለሰብም ለቻይና ብሔራዊ መረጃ በማቀበል መከሰሱ ይታወሳል።

ሁለቱን ግለሰቦች ለስለላ የመለመለው የቻይና ስለላ ክንፍ ተመሳሳይ ስለመሆኑ ግልጽ መረጃ የለም።