የቀድሞው የሞሳድ ባለሥልጣን የኢራን ጠቅላይ መሪ እንዴት ዒላማ ሊሆኑ እንደቻሉ ይናገራሉ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ በአሜሪካ እና በእስራኤል የጋራ ጥቃት ከተገደሉ ሁለት ሳምንት ሊሞላው በተቃረበበት በአሁኑ ጊዜ፣ መሪው እና የአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ባለሥልጣናት የት እንዳሉ? እንዴት መለየት እንደተቻለ እና እየተካሄደ ያለው ጦርነት መቋጫ ምን ሊሆን እንደሚችል ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች ሆነዋል።

የቀድሞ የእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት ራሚ ኢግራ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሳይበር ቴክኖሎጂዎች እና ዲጂታል መሳሪያዎች በስለላ ሥራ ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

ከአንድ ሳምንት በፊት በአሜሪካ እና በእስራኤል የጋራ ዘመቻ የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን በመግደል የተጀመረው ጦርነት በየቀኑ አዳዲስ ገጽታዎችን እየያዘ መስፋፋቱን ቀጥሏል። ሆኖም ግን የዚህ ዓለምን እያሳሰበ የመጣው ጦርነት መነሻ የሆነው የመጀመሪያው ዕለት ክስተትን በተመለከተ ግልጽ የሆነ መረጃ አልወጣም።

አሜሪካ እና እስራኤል የእስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪ የት እንደሚገኙ እንዴት እንደታወቀ እንዲሁም እስራኤል በዚህ ጦርነት ውስጥ ምን ማሳካት እንደምትፈልግ እና ዕቅዷን ለማሳካት እስከምን ድረስ ልትሄድ እንደምትችል ማወቅ የበርካቶች ፍላጎት ነው።

በእስራኤል ቴል አቪቭ የቢቢሲው ዘጋቢ ካስራ ናጂ እነዚህን ጥያቄዎችን በማንሳት የእስራኤል የመረጃ እና የስለላ ድርጅት በሆነው በሞሳድ የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለነበሩት ራሚ ኢግራን ጠይቋል።

የቴክኖሎጂ ሚና በመረጃ አሰባሰብ ውስጥ

የቀድሞው የሞሳድ ባልደረባ እንደሚሉት፣ ባለንበት ዓለም ውስጥ የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎች የስለላ ድርጅቶች ከፍተኛ መጠን ያለው መረጃ እንዲሰበስቡ አስችሏቸዋል። ከእነዚህም መካከል ግለሰቦች ሙሉ በሙሉ የግላቸው እንደሆኑ የሚቆጥሯቸውን ምሥጢራዊ መረጃዎችን ሳይቀር ማግኘት የሚቻልበት ዕድል መፈጠሩን ይጠቅሳሉ።

"ዛሬ ማንም ሰው መረጃ ለመሰብሰብም የሆኑ ነገሮችን ለመፈጸም ምንም ማድረግ አያስፈልገውም" ይላሉ ራሚ ኢግራ። "የስለላ ተቋማት የሞባይል ስልኮችን መጥለፍ፣ በተለያዩ ቦታዎች ድምጽ ማዳመጥ እና በብዙ አጋጣሚዎችም ምሥሎችን ማንሳት ይችላሉ። የስለላ መረጃ አሰባሰብ አሁን በበይነ መረብ መሳሪያዎች እና በተራቀቁ ቴክኖሎጂዎች ላይ በእጅጉ የተመሠረተ ነው።"

የቀድሞው የስለላ ባለሥልጣን እንደሚሉት የኢራን ዋና ከተማ ቴህራንን በመሰሉ ከተማ ውስጥ የካሜራዎችን እና የዲጂታል መሳሪያዎችን ኔትወርክ ማግኘት የሚያዳግት ነገር አይደለም።

የኻሜኒ አስከሬን ምሥል እንቆቅልሽ

ነገር ግን አንዳንድ ጉዳዮች ለራሚ ኢግራ ጭምር እንቆቅልሽ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳዩት የተናገሩት የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን ምሥል እንዴት እንደተገኘ አሁንም ግልጽ አይደለም።

"ይህ ምሥል የተገኘው በሳይበር ኦፕሬሽን ወይም አንድ በስፍራው ከነበረ የሰው ምንጭ በኩል ሊሆን ይችላል" በማለት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ከሚገኘው መረጃ ባሻገር በሰውም የሚሰበሰብ መረጃም ወሳኝ መሆኑን አክለዋል።

በተጨማሪም የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት ለምን ቤታቸው ውስጥ እንደነበሩ ግልጽ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ምናልባት አያቶላህ ኻሜኒ ደኅንነታቸው አስተማማኝ እንደሆነ እና ያጋጠማቸው ዓይነት ጥቃት ዒላማ እንደማይሆኑ አስበው ሊሆን ይችላል ሲሉ ግምታቸውን ገልጸዋል።

የጦርነቱ ግቦች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

የቀድሞው የሞሳድ ባለሥልጣን ራሚ ኢግራ አሁን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ግቦች ላይ ያላቸውን ግምት ያስቀምጣሉ። አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ውስጥ የአገዛዝ ለውጥ ማምጣት ቀዳሚ ግባቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል። ለዚህ ደግሞ የተወሰኑ ሁኔታዎች ሲሟሉ ብቻ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

በኢራን ውስጥ ሥር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ሦስት ነገሮች አስፈላጊ ናቸው ይላሉ። እነዚህም ሰፊ ሕዝባዊ ንቅናቄ፣ መንግሥትን በጦር መሳሪያ የመጋፈጥ አቅም እና ይህንን የሚመራ ግልጽ አመራር መኖር ናቸው። ነገር ግን ራሚ እንደሚሉት እነዚህ ለለውጥ ወሳኝ የሆኑት ነገሮች በአሁኑ ጊዜ በኢራን ውስጥ እንደሌሉ ይናገራሉ።

የቀድሞው የሞሳድ ባለሥልጣን እንደተናገሩት፣ በኢራን ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ የሚመጣ ከሆነ በረጅም እና ቀስ በቀስ በሚከናወን ሂደት ሊሆን ይችላል።

በተጨማሪም የዚህ ጦርነት ግቦች ውስን ሊሆኑ እንደሚችሉ እና ለዚህ አስፈላጊው ነገር ደግሞ የአሜሪካ መንግሥት ግቦቹን ማሳካት መቻሉን መቼ እንደሚገልጽ ማወቁ ላይ ነው ብለዋል።

ራሚ ኢግራ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በኢራን ውስጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲፋጠኑ ቢፈልጉም፣ እንዲህ ያለው ሁኔታ ዕውን እንዲሆኑ ብዙ ምክንያቶች ያስፈልጋሉ።

በዚህ ጦርነት የአሜሪካ ወታደሮች ላይ የሚደርስባቸው ጉዳት ከጨመረ ጦርነቱን ለማስቆም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚኖረው የአገር ውስጥ ግፊት ሊጨምር እንደሚችልም አክለዋል።