አገራት ከክምችታቸው ለመጠቀም ቢስማሙም የዓለም ነዳጅ ዋጋ መጨመሩን ቀጥሏል

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዋና ዋና አገራት በኢራን ላይ የሚካሄደው ጦርነት ያስከተለውን ተጽእኖ ለመግታት በሚል ለድንገተኛ ጊዜ ካስቀመጡት ክምችታቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ለመልቀቅ ቢስማሙም የዓለም የነዳጅ ዋጋ ሐሙስ ዕለት ማሻቀቡን ቀጥሏል።

የዓለም አቀፍ ኢነርጂ ኤጀንሲ 32ቱ አባላት ከክምችታቸው 400 ሚሊዮን በርሜል እንደሚለቁ ቢናገርም አንድ በርሜል ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ በእስያ ገበያ 9 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 100 ዶላር ተሸጧል።

ረቡዕ ዕለት ኢራን በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ውስጥ በመርከቦች ላይ የምታደርሰው ጥቃት እየተባባሰ በመምጣቱ የነዳጅ ዘይት በበርሜል 200 ዶላር ሊደርስ እንደሚችል አስጠንቅቃለች።

የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ቃል አቀባይ ከአሜሪካ፣ ከእስራኤል ወይም ከአጋሮቻቸው ጋር የተገናኘ ማንኛውም መርከብ ዒላማ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

"የነዳጅ ዘይትን ዋጋ በሰው ሰራሽ መንገድ መቀነስ አትችሉም። ነዳጅ በበርሜል 200 ዶላር እንደሚደርስ ጠብቁ" ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

"የነዳጅ ዋጋ የሚወሰነው በክልሉ ደኅንነት ላይ ነው፤ እና እናንተ ለቀጠናው ዋነኛው የፀጥታ ችግር ምንጭ ናችሁ።"

በዚህ ጠባብ በሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ ስለሚጓጓዝበት ለዓለም ምጣኔ ሀብት ወሳኝ ነው።

የአይኢኤ አባላት ከዓለም አቀፍ የኃይል ምርት እና ፍጆታ ሁለት ሦስተኛውን ይወክላሉ።

አባል አገራቱ የለቀቁት የመጠባበቂያ ክምችት ከዚህ ቀደም ሩሲያ ዩክሬንን በወረረችበት ወቅት ኤጀንሲው ለዓለም ገበያ ከለቀቀው በእጥፍ የሚበልጥ ነው።

የአይኢኤ ውሳኔ "በታሪካዊ መልኩ ጉልህ" ቢሆንም "ጊዜያዊ ማስተነፈሻ" ብቻ ነው ሲሉ የሲንጋፖር የቴክኖሎጂ ተቋም ባልደረባ ማርቲን ማ ተናግረዋል።

የነዳጅ ዋጋ በአቅርቦቶች ላይ ስጋት እስካለ ድረስ ዋጋው እንደጨመረ ይቀጥላል፤ የቅርብ ጊዜ ጭማሪ ደግሞ ነጋዴዎች አሁንም "ለረጅም ጊዜ የሚቆይ" አለመረጋጋት ሊኖር እንደሚችል እንደሚጠብቁ ይጠቁማል ሲሉ አክለዋል።

የካቲት 21/2018 ዓ.ም. አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱ ወዲህ የዓለም የነዳጅ ገበያ በከፍተኛ ደረጃ አለመረጋጋት አሳይቷል።

የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በበርሜል 120 ዶላር ደርሶ ነበር። ይህም በዓለም ዙሪያ የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል።

የአሜሪካ አውቶሞቢል ማኅበር እንዳስታወቀው፣ ማክሰኞ ዕለት በአሜሪካ የነዳጅ ዋጋ በአማካይ በጋሎን ከ3.50 ዶላር በላይ ጨምሯል።

ከመካከለኛው ምሥራቅ በሚመጣው የኃይል ምንጭ ላይ ጥገኛ የሆኑ ብዙ የእስያ አገራት በተለይ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በዚህ ሳምንት በፊሊፒንስ፣ በታይላንድ እና በቬትናም በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ሰዎች ነዳጅ ለመቅዳት ረዥም ወረፋ ይዘው ታይተዋል።

የታይላንድ ባለሥልጣናት በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ ሠራተኞች ኃይል ለመቆጠብ ከቤት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል። ባለሥልጣናትም አስፈላጊ ያልሆነ የውጭ ጉዞ እንዳያደርጉ እየተከለከሉ ነው።

በፊሊፒንስ የኃይል አጠቃቀምን ለመቀነስ በሳምንት ለአራት ቀናት ብቻ ወደ ሥራ መግባት ይፋ ተደርጓል።