ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት ከ50 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ ሌሎች 50 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ውስጥ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ 52 ሰዎች መሞታቸውን የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን አስታወቀ።
በዞኑ ለሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው የመሬት መንሸራተት ያጋጠመው በጋጮ ባባ ወረዳ ማዞ ዶይሳ ቀበሌ ውስጥ የካቲት 30 እና መጋቢት 1/2018 ዓ.ም. የጣለውን ዝናብ ተከትሎ ነው።
የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባጋራው መረጃ በጋጮ ባባ ወረዳ ማዞ ዶይሳ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ሕይወታቸው ካለፈ 52 ሰዎች በተጨማሪ እስካሁን የደረሱበት ያልታወቀ 50 ሰዎችን የመፈለግ ጥረቱ መቀጠሉን አስታውቋል።
የጋሞ ዞን የከተማና አስተዳደር ልዩ አማካሪ አቶ ተስፋጺዮን ዘነበ በዞኑ ደጋማ አካባቢዎች በጣለው "ወቅቱን ያልጠበቀ ከፍተኛ ዝናብ" የመሬት ናዳው መከሰቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የመሬት ናዳው የደረሰው መጋቢት 1 2018 ዓ.ም. "ከእኩለ ለሊት በኋላ ነው" ያሉት አቶ ተስፋጺዮን "ባልተለመደ እና ባልተጠበቀ መንገድ ከፍ ያለ ዝናብ ይጥል ነበር" ሲሉ ሁኔታውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ኃላፊው አክለውም በአካባቢው ይጥል የነበረው ዝናብ ረቡዕ መጋቢት 2 2018 ዓ.ም. ማለዳ ድረስ መቀጠሉን እና ይህም ሁኔታውን አስቸጋሪ ማድረጉን ተናግረዋል።
አቶ ተስፋጺዮን የ52 ሰዎች አስከሬን ከናዳው ውስጥ በቁፋሮ መውጣቱን ገልጸው የ50 ሰዎች ፍለጋ ቀጥሏል ብለዋል።
በዞኑ በርካታ ተዳፋት ቦታዎች እንደሚገኙ የገለፁት አቶ ተስፋጺዮን፣ አሁን የመሬት ናዳው በደረሰበት ስፍራ ግን ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት አደጋ ደርሶ እንደማያውቅ ተናግረዋል።
በዞኑ የመሬት ናዳ ይከሰትባቸዋል ተብለው በጥናት በተለዩ አካባቢዎች ነዋሪዎችን የማንሳት እና ወደ ሌላ ቦታ ወስዶ የማስፈር ስራዎች መሰራታቸውን የተናገሩት አቶ ተስፋጺዮን "ይህ አካባቢ ግን ከዚህ ዓይነት ግምት እና ስጋት ነጻ ስለነበር" ምንም ዓይነት እርምጃ አለመወሰዱን አስረድተዋል።
በጋሞ ዞን የጣለን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ ከባድ ጎርፍ እና የመሬት ናዳ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተሰግቷል።
የዞኑ ባለሥልጣናት በአደጋው የጠፉ 50 ሰዎችን የመፈለግ ጥረቱ አሁንም መቀጠሉ የገለጹ ሲሆን፣ በሕይወት ለተረፉትም እርዳታ የማሰባሰብ ሂደት ተጀምሯል።
ከባዱ አደጋው የደረሰው ከከባድ ዝናብ በኋላ ባጋጠመ የመሬት መንሸራተት ሲሆን፣ አካባቢው ተዳፋት በመሆኑ የሕይወት አድን ሥራውን ከባድ አድርጎታል።
አደጋው በተከሰተበት ሥፍራው የዞኑ ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ የፌደራል እና የክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተገኝተው በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎችን አጽናንተዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው የጋሞ ዞን በተደጋጋሚ በከባድ ዝናብ እና በጎርፍ ከሚጠቁ የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው።
በ2016 ዓ.ም. በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው ተመሳሳይ የመሬት መንሸራተት ከ200 ሰዎች በላይ መሞታቸው ይታወሳል።
በደቡብ ኢትዮጵያ የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋዎች የሚከሰቱ ሲሆን፣ በ2016 ከባድ ዝናብ ባሰከተለው የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሕይታቸውን አጥተዋል።