ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመሬት መንሸራተት ምንድን ነው? መንስዔዎቹስ?
ከሰሞኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን የተከሰተው የመሬት መንሸራተት ከ229 በላይ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።
በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት የተቀበሩ ነዋሪዎችን ነፍስ ለማዳን እንዲሁም አስከሬኖቻቸውን ለማውጣት ጥረቶች ቀጥለዋል። የሟቾችም ቁጥር ከዚህ በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችልም ስጋቶች እየተገለጹ ነው።
እሁድ፣ ሐምሌ 14/2016 ዓ.ም. ሌሊት በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የመጀመሪያው መሬት ማንሸራተት አጋጠመ።
በዚህ መንሸራተት አራት ሰዎች መሞታቸውን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ለመገናኛ ብዙኃን ከሰሞኑ ገልጸዋል።
እነዚህ አራት ሰዎች ላይ የተጫነውን ናዳ ለማንሳት በማግስቱ ሰኞ ረፋድ ላይ ርብርብ እየተደረገ በነበረበት ወቅት መሬቱ ተደርምሶ ተጨማሪ ናዳ በማስከተሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ላይ አርፏል።
ሰኞ አራት ሰዓት ገደማ የአካባቢው ቀበሌ ሊቀመንበርን ጨምሮ፣ የፖሊስ አባላት እና በርካታ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች በነፍስ አድን ጥረት ላይ እያሉ ነው መሬት መንሸራተት አጋጥሞ በተጨማሪ ድንገተኛ ናዳ የበርካቶች ሕይወት ጠፍቷል።
እስካሁንም የ229 ሰዎችን አስክሬን ከናዳው ስር ማውጣት የተቻለ ሲሆን ፍለጋውም ቀጥሏል።
በደቡብ ኢትዮጵያ የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋዎች የሚከሰት ቢሆንም ይህንን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች የሞቱበት አደጋ ግን ገጥሞ አያውቅም ተብሏል።
ለመሆኑ የመሬት መንሸራተት ምንድን ነው? መንስዔዎቹስ?
ከሌሎች ተፈጥሯዊ ክስተቶች በበለጠ የመሬት መንሸራተት በስፋት እንዲሁም በየትኛውም የዓለማችን ክፍሎች ሊከሰት እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ዓለማችን እያጋጠማት ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እየተደጋጋሙ እና እየከፉ መምጣታቸውን ባለሙያዎች የጠቆሙ ሲሆን፣ ይህም ቀጣይነት አለው ይላሉ።
ከሰሞኑ በጎፋ ዞን ከተሰተው በተጨማሪ በዚሁ ዓመት በኢንዶኔዥያ፣ በኔፓል እና በፓፓዋ ኒው ጊኒ ተመሳሳይ አደጋዎች ተከስተው የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፈዋል።
በዚህ ጽሁፍ ላይ የመሬት መንሸራተት መንስዔዎችን፣ ዓይነታቸውን እንዲሁም እነዚህ ክስተቶች ቢያጋጥሙ እንዴት ራስን መጠበቅ ይቻላል የሚለውን እናያለን።
የመሬት መንሸራተት ምንድን ነው?
የመሬት መንሸራተት ክስተት የምንለው ከአንድ ተዳፋታማ አካባቢ ድንጋይ፣ አፈር ላይ ያሉ ደኖች፣ አፈር እንዲሁም ሌሎች ጥራጊዎች በፊት ከነበሩበት ወደ ቁልቁለት ቦታ ሲንሸራተቱ እና ስፍራውን ለቀው ሲሄዱ የሚከሰት ነው። ይህ ሂደት በድንገት ወይም ቀስ በቀስ ረዘም ላለ ጊዜ ሊከሰት ይችላል።
በአንድ ተዳፋታማ አካባቢ ያለው አፈር ወይም ድንጋይን በስፍራው ከሚያቆያቸው የስበት ኃይል በበለጠ ወደ ቁልቁለት የሚወስዳቸው ኃይል በዋነኝነት የስበት ኃይል የበለጠ ሲሆን እንደሆነ የብሪታንያ ጂአሎጂካል ሰርቬይ ድረ-ገጽ ያስረዳል።
የመሬት መንሸራተት ዋና መንስዔዎች ምንድን ናቸው?
ከመሬት መንሸራት መንስዔዎች መካከል በተዳፋታማ አካባቢዎች ከፍተኛ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት፣ በበረዶ መቅለጥ፣ በመሬት መሸርሸር፣ በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በእሳተ ገሞራ እንቅስቃሴ፣ በከርሰ መሬት ውስጥ ባለ የውሃ መጠን ለውጥ እና በሌሎች ሰው ሰራሽ ምክንያት በአንድ ወይም በእነዚህ ምክንያቶች ጥምረት ሊከሰት እንደሚችል ከአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
በውሃ አካላት ውስጥም የመሬት መንሸራተት የሚከሰት ሲሆን እነዚህም በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በውሃ ሞገድ መንስዔዎች ያጋጥማል። አንዳንዴም እነዚህ ክስተቶችን አውሎ ነፋስ የቀላቀለበት የሱናሚ ማዕበልን አስከትለው የባሕር ዳርቻ አካባቢዎችን ይጎዳሉ።
በዓለም ጤና ድርጅት መሠረት የመሬት መንሸራተት ችግር የሚያጋጥማቸው አካባቢዎች፦
- ገደላማ ኮረብታዎች እና ረባዳ ሸለቆዎች
- በሰደድ እሳት የተቃጠለ መሬት
- በሰው ሰራሽ ምክንያቶች በደን ተሸፍኖ የነበረ መሬት፣ መመናመን፣ መራቆት ወይም በግንባታ የተቀየሩ አካባቢዎች
- ወንዝ ወይም ምንጭ የሚያልፍባቸው አካባቢዎች
- ያቆሩ ውሃ በሚገኝባቸው ወይም በውሃ ምክንያት በተሸረሸሩ አካባቢዎች
የመሬት መንሸራተት ዓይነቶች
የመሬት መንሸራተት ፈጠን ካለ የድንጋዮች እና ፍርስራሾች በፍጥነት መናድ እስከ በርካታ መቶ ዘመናትን የሚቆይ የከፋ መንሸራተትን ይሸፍናል።
የመሬት መንሸራተቶች ውስብስብ ናቸው፤ ቀስ በቀስ የሚናዱ እንዲሁም በፍጥነት የሚናዱ መንሸራተቶችን እንደሚያጣምሩም ከአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
የመሬት መንሸራተት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ አምስት ዓይነት ተዳፋታማ እንቅስቃሴዎችን የሚሸፍን ሲሆን፣ እነዚህም መደርመስ (ፎልስ)፣ መገልበጥ (ቶፕልስ)፣ መንሸራተት (ስላይድስ)፣ መዘርገፍ (ስፕሬድስ)፣ መፍሰስ (ፍሎውስ) ይባላሉ። እነዚህም የመንሸራተት አይነቶች በሚንዱት አይነት የቋጥኝ ድንጋይ፣ ፍርስራሾች ወይም በመሬት እንደገና ይከፋፈላሉ።
የተወሰኑትን ምን ማለት እንደሆነ ጠቅለል አድርገን እንያቸው።
መደርመስ (ፎልስ) - ድንገተኛ በሆነ ሁኔታ ድንጋይ ወይም መሬት ከተዳፋታማ መሬት ሲንሸራተት ነው።
መገልበጥ (ቶፕልስ) - ከተዳፋታማ ቦታ ወደፊት መሬቱ ስፍራውን ለቆ አሽቆልቁሎ ሲገነደስ ነው።
መንሸራተት (ስላይድስ) - ድንጋይ፣ ደን የጫነ አፈር ከአንድ ስፍራ በእሽክርክሪት ወይም በአንድ አቅጣጫ አሽቆልቁሎ ሲሄድ ነው።
መዘርገፍ (ስፕሬድስ) - ይህ በተዳፋታማ አካባቢ፣ ውሃ ባቆሩ አካባቢዎች በተፈጠረ መሬት መንቀጥቀጥ ወይም ውሃ በሚፈስባቸው አካባቢዎች ላይ መሬታቸው በተሸረሸሩ አካባቢዎች የሚፈጠር ወደ ጎን የሚደረግ መንሸራተት ነው።
መፍሰስ (ፍሎውስ)- በጭቃ የተለወሱ ፍርስራሾች ወይም ጭቃ እና እንደ ፈሳሽ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው።
ራሳችንን ከመሬት መንሸራተት አደጋ እንዴት እናትርፍ?
በዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሠረት ከአውሮፓውያኑ 1998 እስከ 2017 ባለው ወቅት የመሬት መንሸራተት 4.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ላይ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ጉዳት አድርሷል። በነዚህም ዓመታት ውስጥ ከ18 ሺህ በላይ ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል።
አደጋው ድንገት ከተሰማዎት ሳይውሉ ሳያድሩ አካባቢውን መልቀቅ እንዲሁም ለጎረቤቶች እና ለባለሥልጣናት ማሳወቅን የአሜሪካው ቀይ መስቀል ይመክራል።
እንዲሁም በአካባቢው ያሉ ድምጾችን ነቃ ብለው እንዲያዳምጡም ይመክራል፤ ለምሳሌ ዛፎች በሚንቀጠቀጡበት ወቅት ቋጥኞች ኳኳታ በሚፈጠርበት ወቅት።
በወንዝ አቅራቢያ ለሚኖሩ ደግሞ “ድንገት የውሃ ፍሰት መጨመር ወይም መቀነስ ካጋጠመ እንዲሁም ውሃው ጥርት ካለ፣ ንጹህነት ወደ ጭቃ ከተለወጠ በደንብ አስተውሉ። እንደነዚህ አይነት ለውጦች አሉ ማለት የጥርጊያዎች እንቅስቃሴ አለ ማለት ስለሆነ በፍጥነት አካባቢውን መልቀቅ ነው” ይላል።
በአሜሪካ የሚገኘው የዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ እንዴት ከመሬት መንሸራተት መዳን ይቻላል በሚለው ላይ ጠቃሚ ምክሮች ላይ ጥናት አድርጓል።
ተመራማሪዎቹ በመኖሪያ ሕንጻዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ 38 የመሬት መንሸራተቶችን መረጃዎች ሰብስበዋል። አብዛኛዎቹ መረጃዎች ከአሜሪካ የተገኙ ቢሆንም ነገር ግን በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የተከሰቱ መንሸራተቶችን ዝርዝር አካቷል።
“አንዳንድ በጣም ቀላል እና ወጪ ቆጣቢ እርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል” የሚሉት ጥናቱን ከጻፉት አንዱ እና የሲቪል እና የአካባቢ ምኅንድስና ፕሮፌሰር የሆኑት ጆሴፍ ዋርትማን ናቸው።
በቀላሉ ካሉበት ፎቅ ወደ ላይኛው ፎቅ በመውጣት የመዳን ዕድልን በአስራ ሁለት እጥፍ ሊያሳድግ እንደሚችል ያስረዳሉ።
ሌሎች የሚለግሷቸው ምክሮች ደግሞ በሮች እና መስኮቶችን መክፈት እንዲሁም ድንገት ይህ ሁሉ ሳይሆን በናዳ ውስጥ ከተቀበሩ መንቀሳቀስ መቀጠል እና ድምጽ ማሰማትን አይርሱ ይላሉ።
የመሬት መንሸራተት ምን ያህል ጎጂ ነው?
“አንዳንድ የመሬት መንሸራተቶች ከሚሮጥ ሰው በላይ በፍጥነት ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ። አንዳንዴም ያለ ምንም ምልክት፣ ለቀናት፣ ለሳምንታት ወይም ከዚያም በላይ ሊከሰቱ ይችላሉ” ይላል የአሜሪካው ጂኦሎጂካል ሰርቬይ።
የመሬት መንሸራተት የውሃን ፍሰት በከፍተኛ ፍጥነት በመጨመር እንዲሁም በሚጠራርጋቸው ፍርስራሾች ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሕይወት መቀጠፍ እና የአካል ጉዳቶች እንደሚያስከትል የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
ከመሬት መንሸራተት ጋር ተያይዞ የተለመደው የሞት መንስዔ መታፈን ወይም ደግሞ መውጫ ማጣት ናቸው።
ነገር ግን ከመሬት መንሸራተቶች በኋላ የሚከሰቱ ጉዳዮችም ጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ። “የመሬት መንሸራተቶች በጤና ሥርዓት እንዲሁም መሠረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶችን እንደ ውሃ፣ ኤሌክትሪክ ወይም የመገናኛ መስመሮችን በእጅጉ ሊጎዳ ይችላል” ይላል የዓለም ጤና ድርጅት።
የተበላሹ የኤሌክትሪክ መስመሮች የኤሌክትሪክ አደጋ እንዲሁም የውሃ፣ የጋዝ እና የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦች መበላሸት ጉዳቶችን እንዲሁም የውሃ ወለድ በሽታዎችን ያስከትላሉ።
“በመሬት መንሸራተቶች ምክንያት ቤተሰባቸውን፣ ንብረታችውን ወይም ከብቶቻቸውን ያጡ እንዲሁም ሰብላቸው የወደመባቸው ሰዎች በአጭር እና የረዥም ጊዙ የአዕምሮ ጤና ችግር ሊጎዱ ይችላሉ” ይላል የዓለም ጤና ድርጅት።
የመሬት መንሸራተት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ይያያዝ ይሆን?
የአየር ንብረት ለውጥ እና የአየር ሙቀት መጨመር ተጨማሪ የመሬት መንሸራተቶችን ያስከትላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
“የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ለመሬት መንሸራተት ድግግሞሽ እንዲሁም መጠኑንን ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል” ይላል የአሜሪካው ጂኦሎጂካል ሰርቬይ።
እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ ይህ በተለይም የሚከሰተው በበረዷማ እና በተራራማ አካባቢዎች ነው።
“የበረዶ ግግሮች ሲቀልጡ ድንጋያማ ተዳፋታማ ስፍራዎች የበለጠ ያልተረጋጉ ይሆናሉ። ይህም የመሬት መንሸራተትን ያስከትላል” ይላል።
የአሜሪካው ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ ከተደጋጋሚ እና ከከፋ ሰደድ እሳት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ “በቅርብ ጊዜ በሰደድ እሳት የተቃጠሉ አካባቢዎች እሳቱ የአፈሩን እና ዕፅዋትን ባህርይ ስለሚቀይር የመሬት መንሸራተቶች ሊከሰቱ ይችላሉ” ብሏል።