ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍል በሳምንት ልዩነት ከፍ ያለ መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በሬክተር ስኬል 4.8 ሆኖ የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦፊዚክስ፣ ህዋ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በበና ፀማይ ወረዳ የተከሰተው ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ አጎራባች በሆነው አሪ ዞን እንዲሁም ባለፈው ሳምንት ተመሳሳይ ክስተት ያስተናገደው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሉ ዳውሮ ዞን ጭምር የደረሰ እንደሆነ ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ትናንት እሁድ ግንቦት 4/2016 ዓ.ም. የተከሰተውን የመሬት መንቀጥቀጥ የመዘገበው ከሌሊቱ 6 ሰዓት ከ36 ደቂቃ ላይ እንደሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሲሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ፕሮፌሰር አታላይ አየለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ በሬክተር ስኬል 4.8 ሆኖ መመዝገቡን የሚያስረዱት ፕሮፌሰር አታላይ፤ ይህ መጠን “መካከለኛ” የሚል ደረጃ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል። የትናንቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ልኬት ባለፈው ሳምንት በዳውሮ ዞን ከተመዘገበው 3 ሬክተር ስኬል ከፍ ያለ መሆኑን የሶሲሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊው አስታውሰዋል።
“ይን [የመሬት መንቀጥቀጥ] ዝቅተኛም፣ ከፍተኛ አይባልም። መካከለኛ ነው። [የሚያስከትለው] ውድመት እና ጥፋት ግን እንደ አካባቢው ቅርበት [የሚወሰን] ነው። ይህ ከተማ ውስጥ ቢፈጠር ብዙ ጉዳት ያደርሳል” ሲሉ የክስተቱ ሊያደርስ የሚችለውን የጉዳት ጠቅሰዋል።
ፕሮፌሰር አታላይ እንደሚገልጹት ክስተቱ የተመዘገበው በደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍል “ወይጦ ድልድይ ፖሊስ ጣቢያ” በተባለ አካባቢ ነው።
“ወይጦ” የተባለው አካበቢ የሚገኝበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ ወረዳ ብራይሌ ታዳጊ ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ ኦይታ ኡኖ ትናንት ሌሊት የመሬት መንቀጥቀጥ ማጋጠሙን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ “በተከታታይ ሁለት ጊዜ” መከሰቱን የሚናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፤ ክስተቱ “አስደንጋጭ” እንደነበር ገልጸዋል።
“ብዙዎቻችን በህይወት እንተርፋለን ብለን አልጠበቅንም ነበር” ሲሉም በሰዓቱ የተሰማቸውን አጋርተዋል።
በናይ ፀማይ ወረዳ የሚገኝበት ደቡብ ኦሞ ዞን ካሉት ስድስት ወረዳዎች እና አንድ የከተማ አስተዳደር ውስጥ በስድስቱ ውስጥ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱ እንደተረጋገጠ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ለቢቢሲ ተናግረዋል። እስካሁን ድረስ ከአንድ ወረዳ መረጃ እንዳልደረሳቸው የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ መረጃ በተገኘባቸው መዋቅሮች ጉዳት አለመመዝገቡን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ከደቡብ ኦሞ ዞን ተነጥሎ በዞንነት በተዋቀረው አሪ ዞንም የመሬት መንቀጥቀጡ መሰማቱን የዞኑ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምራት ተስፋዬ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የዞኑ ዋና ከተማ የሆነውን ጂንካን ጨምሮ በወረዳው በሚገኙት አራት ወረዳዎች እና ሁለት የከተማ መስተዳድሮች ክስተቱ ማጋጠሙን እንዳረጋገጡም ኃላፊው አስረድተዋል። በሁሉም መዋቅሮች የደረሰ ጉዳት አለመኖሩንም አክለዋል።
ባለፈው ሳምንት የመሬት መንቀጥቀጥ ባስተናገደው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሉ ዳውሮ ዞንም የትናንቱ የመሬት መንቀጥቀጥ መሰማቱን አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል። መንቀጥቀጡ የተከሰተበት ሰዓት በሌሎቹ አካባቢዎች ከተከሰተው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ የታርጫ ከተማ ነዋሪው አረጋግጠዋል።
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት በዳውሮ ዞን የተከሰተው እና በሬክተር ስኬል ሶስት ሆኖ የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ በወረዳው በሚገኙት 12 መዋቅሮች በሙሉ እንዳጋጠመ የዞኑ አስተዳደር ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።
በቀናት ልዩት ውስጥ የመሬት መንቀጥቀጥ ያስተናገዱት የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የስምጥ ሸለቆ አካል መሆናቸውን የሚናገሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሲሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊው ፕሮፌሰር አታላይ፤ ክስተቱ ከዚህ ጋር የሚገናኝ መሆኑን ገልጸዋል።