ሩሲያ ቁልፍ ወደምትባለው የዩክሬን ከተማ መቃረብ ስትጀምር፤ ዩክሬን የሩሲያ ግስጋሴዋን ገታ አደረገች

የሩሲያ ኃይል ባለፉት ጥቂት ቀናት ቁልፍ ወምድትባለው የዩክሬን ከተማ የሚያደርገውን ግስጋሴ የቀጠለ ሲሆን ኪየቭ ደግሞ በሩሲያዋ ከርስክ ግዛት የነበራትን ጥቃት ገትታለች።

የሩሲያ ኃይሎች የዩክሬን ወታደሮች ለሎጂስቲክ የሚጠቁሙባትን ፖክሮቭስክ ከተማ ለመቆጣጠር ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ነው የቀራቸው።

በጦርነቱ አስፈላጊ የሚባለው የባቡር መስመር እና በርካታ ወሳኝ መንገዶች ያሏት ፖክሮቭስክ በምስራቁ ግንባር ለዩክሬን ወታደሮች ቁልፍ የአቅርቦት ማዕከል ናት።

የዩክሬን ኃይልን የሚተቹ ሰዎች ወታደራዊው ኃይል ወደ ሩሲያ ባደረገው ግስጋሴ ትልቅ ጥፋት ሠርቷል ሲሉ ይወቅሳሉ።

ተቺዎቹ እንደሚሉት የዩክሬን ጦር በምስራቅ ግንባር ያለውን ሠራዊት በማጠናከር ፈንታ ወደ ሩሲያዋ ከርስክ ግዛት ተጨማሪ ወታደሮች በመላኩ በርካታ ከተሞች ለሩሲያ ኃይል ተጋልጠዋል።

የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በአውሮፓውያኑ የካቲት 2022 ነው ሙሉ ጦራቸውን ይዘው ዩክሬንን የወረሩት።

የዩክሬን ጦር ሠራዊት ኃላፊ ጀኔራል ኦሌክሳንድር ሲርስኪ፤ ሩሲያ “የሚንቀሳቀስ ነገር ላይ ሁሉ” ጥቃት ሰንዝራለች ብለዋል።

“ሁኔታዎች በጣም ከባድ ሆነዋል” ሲሉ ረቡዕ ዕለት የተናገሩት ደግሞ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ናቸው።

ዩክሬናዊው የጦርነት ስትራቴጂ ተንታኝ ሚካይሎ ዢርኮቭ “ፖክሮቭስክን ካጣን የጦር ግንባራችን ከጥቅም ውጭ ሆነ ማለት ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ፖክሮቭስክ ቁልፍ የሆነችው ለምንድነው?

ፖክሮቭስክ፤ ሚርኖራድ ከተባለችው ከተማ ቀጥሎ የምትገኝ ናት። ከጦርነቱ በፊት በሁለቱ ከተማዎች ከ100 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ነበሩ። አሁን ሁሉም ቀየውን ጥሎ ሸሽቷል።

በዩክሬን ቁጥጥር ሥር ባለው የዶኔስክ ግዛት ሁለቱ ጠንካራ ይዞታዎች የሚባሉት እኒህ ከተማዎች ነበሩ።

ባለፈው የካቲት ደም አፋሳሽ ከሆነ የወራት ጦርነት በኋላ አቭዲቭካ የተሰኘችው የዩክሬን ከተማ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር መዋሏ አይዘነጋም። የፖክሮቭስክም ዕጣ ፈንታ ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል የሚሉ መላ ምቶች አሉ።

ከፖክሮቭስክ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አቭዲቭካ ለዩክሬን ወታደራዊ ኃይል ቁልፍ ከሚባሉ ከተማዎች መካከል ነበረች። ይህች ከተማ ፍርስርሷ ወጥቶ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ስትወድቅ ለዩክሬን ትልቅ ሽንፈት ነበር።

ከዚህ በኋላ ነው የሩሲያ ጦር ትኩረቱን ወደ ፖክሮቭስክ ያደረገው። ከፖክሮቭስክ ቀጥሎ ተራራ ላይ የተቀመጠችው ቻሲቭ ያር ዒላማ እንደምትሆን ይገመታል። ቅዳሜ ዕለት ቻሲቭ ያር በነበረ ከባድ ጦርነት አምስት ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።

ባለፉት ሳምንታት ፖክሮቭስክ ይኖሩ የነበሩ ዬክሬናዊያን ከተማዋን ጥለው እንዲወጡ በታዘዙት መሠረት የሸሹ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ከተማዋን ለቀው እንደወጡ ተነግሯል።

ሩሲያ እንዴት ልትገስግስ ቻለች?

ፖክሮቭስክ የተባለችው ከተማ ለሩሲያ ትልቅ ዒላማ ሆና ቆይታለች። የሩሲያ ኃይሎች በዝግታ ወደዚህች ከተማ ሲቃረቡ ቆይተዋል።

ተንታኞች እንደሚያምኑት ሩሲያ ከማዕከላዊው የጦር ቡድን አንድ ሶስተኛውን አሊያም 30 ሺህ ገደማ የጦር ሠራዊት እና ዝግጁ የነበሩ ተጠባባቂዎችን ይህችን ከተማ ለመያዝ ልካለች።

የሩሲያ ጦር በተገባደደው ሳምንት ኖቮሮዲቭካ የተባለችውን ከተማ የተቆጣጠሩ ሲሆን አንዳንድ ዩክሬናዊያን ከተማዋ በቁጥጥር ሥር መዋል አልነረባትም ሲሉ ቁጭታቸውን እየገለጡ ይገኛሉ።

የዩክሬን ፓርላማ አባል የሆኑት ማሪያና ቤዙላ “የከተማዋ ምሽጎች ባዶ ሆነዋል። በአንድ ወቅት 20 ሺህ የዩክሬን ወታደር የነበረባት ከተማ አሁን ባዶ ሆናለች” ሲሉ በፌስቡክ ገፃቸው ፅፈዋል።

የዩክሬን ጦር በፖክሮቭስክ ያለውን ጦር ለማጠናከር ሲባል ኖቮሮዲቭካ የነበረው ኃይል እንዲያፈገፍግ ማድረጉ እየተነገረ ነው።

ሩሲያ በጦርነቱ የበላይነቷን እያሳየች የመጣችው የታክቲክ ለውጥ በማምጣቷ በተለይ ደግሞ በጦርነቱ ጅማሪ የቫግነር ቅጥረኛ ወታደሮች የሚጠቀሙትን ስትራቴጂ በመጠቀማቸው እንደሆነ ይታመናል።

የዩክሬን ወታደሮች እንደሚሉት የሩሲያ ወታደሮች በቡድን በቡድን በመሆን በተደጋጋሚ ጥቃት በማድረስ ቦታቸውን ለቀው እንዲሄዱ እያደረጓቸው ነው።

ይህ የጦርነት ስትራቴጂ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል ቢሆንም በተደጋጋሚ ጥቃት እየተፈፀመባቸው ያሉት የዩክሬን ወታደሮች ማፈግፈግ ጀምረዋል።

በሌላ በኩል ዩክሬን ወደ ሩሲያዋ ከርስክ ግዛት የምታደርገውን ግስጋሴ በተለይ ባለፈው ሳምንት ገታ አድርጋለች።

ዩክሬን በሩሲያ ግዛት የተቆጣጠረችው ትልቁ ግዛት ሱድዛ ሲሆን የሕዝብ ቁጥሯ 5 ሺህ ገደማ ነው። በተቃራኒው ኖቮሮዲቭካ የተባለችው በያዝነው ሳምንት በሩሲያ ቁጥጥር ሥር የዋለችው ከተማ የሱድዛ ሶስት እጥፍ የሕዝብ ቁጥር አላት።

ባለፈው ማክሰኞ የዩክሬን ጦር አዛዥ በከርስክ ግዛት 594 የሩሲያ ወታደሮችን በቁጥጥር ሥር አውለናል ብለዋል። ነገር ግን ይህ ቁጥጥር ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጥ አልተቻለም።

ጥያቄው ዩክሬን በከርስክ ግዛት የምታደርገው ግስጋሴ ምስራቅ ዩክሬን ለሚደረገው ጦርነት ምን ያክል ፋይዳ አለው የሚለው ነው።