ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጂቡቲ የታጁራ ወደብን ኢትዮጵያ እንድታስተዳድር ለመስጠት አማራጭ ማቅረቧን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ገለጹ
በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የተነሳውን ውጥረት ለማርገብ ጂቡቲ ከወደቦቿ አንዱን ኢትዮጵያ በቀጥታ እንድታስተዳድር ለማድረግ አማራጭ ማቅረባቸውን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ኢትዮጵያ የባህር መዳረሻ እንድታገኝ አንደኛውን የጂቡቲ ወደብ “ሙሉ በሙሉ እንድታስዳድር” አገራቸው አማራጭ አቅርባለች ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ባደረጉት ልዩ ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።
ጂቡቲ ያቀረበችው ወደብ ከኢትዮጵያ በመቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የታጁራ ወደብ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚህ ቆይታቸው ገልጸዋል።
ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተደረሰ የባህር በር መግባቢያ ስምምነት የተነሳ ከሶማሊያ ጋር የተነሳውን ውጥረት ለማርገብ እንዲሁም የኢትዮጵያን የባህር በር መዳረሻ ችግር ለመቅረፍ ይህ አማራጭ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የባህር በር መዳረሻ እንድታገኝ የሚያስችላትን በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘውን ወደብ እንዲሁም አዲስ የተገነባ ኮሪደር እንድታስተዳድር ሃሳብ ቀርቧል ብለዋል።
ይህንን አማራጭ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኦማር ጉሌህ ለኢትዮጵያ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ የቀረበው የወደብ የማስተዳደር አማራጭ ለየትኛው የመንግሥት አካል፣ መቼ እንዲሁም በምን አይነት ስምምነት እንደሆነ ዝርዝር መረጃዎችን አልሰጡም።
ኢትዮጵያም የጂቡቲን ወደብ ለማስተዳደር ስለቀረበላት አማራጭ ያለችው ነገር የለም።
ሆኖም በአማራጭ ሃሳቡ ዙሪያ በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው የቻይና- አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ከሁለቱ መሪዎች ጋር ለመወያየት ዕድል እንደሚኖር ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
በ90 ሚሊዮን ዶላር በተገነባው የታጁራ ወደብ ኢትዮጵያ ከአራት ዓመት በፊት መጠቀም መጀመሯን የአገሪቱ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት በወቅቱ አስታውቆ ነበር።
ኢትዮጵያ በአፋር ክልል አለ የሚባለውን በቢሊዮን ቶኖች የሚገመት የፖታሽ ክምችትን እንዲሁም ለድንጋይ ከሰል እና የብረት ጭነቶችን በታጁራ ወደብ በኩል ወደ ውጪ ለመላክ እቅድ እንዳለ ተገልጿል።
በተለይም ከታጁራ ወደብ እስከ ወደቧ ከተማ በልሆ ድረስ ያለው 120 ኪሎ ሜትር መንገድ በ156 ሚሊዮን ዶላር የተገነባ ምቹ አስፋልት በመሆኑ በተሽከርካሪዎች ዘንድ ተመራጭ እንደሆነም በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
የባህር በር አልባዋኢትዮጵያ የገቢ እና ወጪ ንግዷን የምታካሂደው በጂቡቲ ወደብ በኩል ሲሆን ይህም አገሪቷን በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስወጣታል።
ኢትዮጵያ የንግድ መተላለፊያ ወደብ ለማግኘት እና የባህር ኃይሏን ለማጠናከር ካላት ፍላጎት የተነሳ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ስምምነት መፈረሟ ከሶማሊያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ ከቷታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ውጥረት ውስጥ የገቡት ሁለቱ አገራት በውይይት የያዙትን የሰፋ የአቋም ልዩነት የሚያጠቡበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል ብለዋል።
ጂቡቲ፣ ኬንያ እና ሌሎች የቀጣናው አገራት መድረኩን የማመቻቸት ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
ልዩነታቸውን የሁለቱም አገራት ሉዓላዊነት በተከበረበት ሁኔታ ሊፈታ እንደሚገባም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
አገራቱ የገቡበት ውጥረት የበለጠ ቀጣናውን ስጋት ውስጥ እንደሚከተው የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ወቅት በኤደን ባሕረ ሰላጤ እና በባብ አል ማንደብ ግዛት ከየመን ሁቲ ታጣቂ ቡድን ጥቃት እየደረሰብን ነው ብለዋል።
ጂቡቲ የተረጋጋች አገር ብትሆንም በጎረቤት አገራት ያለው ውጥረት የማይረግብ ከሆነ ለአገራቸውም ከፍተኛ ስጋት መሆኑን ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሁለቱም አገራት ውጥረት ከሚያባብሱ መግለጫዎች እና ትርክቶች እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ስትወዛገብ የነበረችው ግብጽ ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረሟ ኢትዮጵያን እንዲሁም የአፍሪካን ቀንድ ቀጣናን ስጋት ላይ ጥሏል።
ግብጽ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተገባው የባህር በር መግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ለገባችው ሶማሊያ በሁለት የጦር አውሮፕላኖች የጦር መሳሪያዎች መላኳን ተከትሎ ውጥረቶቹ ተካረዋል።
የሁለቱ አገራት ወታደራዊ ትብብር ስጋት ውስጥ የጣላት ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በዝምታ እንደማትመለከት አስታውቃለች።
የሶማሊያ መንግሥትንም “ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ስትል ከሳለች።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።
ኢትዮጵያ በምላሹ ለሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና በመስጠትም ከዓለም የመጀመሪያዋ አገር እንደምትሆንም የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ወረራ እንዲሁም ሉዓላዊነቴን የጣሰ ድርጊት ነው ያለችው ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከማቋረጧ በተጨማሪ ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች።