ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኤችፒቪ ምክንያት ምላሱን ሊያጣ የነበረው የሁለት ልጆች አባት
የሁለት ልጆች አባት የሆነው ግለሰብ መንጋጋው ስር የወጣበት አነስተኛ እብጠት ወደ ካንሰር ከተቀየረ በኋላ ምላሱን ሊያጣ ነበር።
አንቶኒ ፔሪያም ለመጀመሪያ ጊዜ መንጋጋው ስር እብጠት መኖሩን ከተረዳ በኋላ ወደ ሐኪሙ ዘንድ ሄደ። እናም በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በጭንቅላቱ እና በአንገቱ ላይ ከሂውመን ፓፒሎማቫይረስ (ኤችፒቪ) ጋር የተያያዘ ካንሰር እንዳለበት ታወቀ።
ኤችፒቪ ቆዳን የሚያጠቃ የተለመደ የቫይረሶች ቡድን ነው። ቫይረሶቹ በበርካታ ሰዎች ላይ ችግር የማያመጡ ቢሆንም የተወሰኑ የቫይረሱ ዓይነቶች ግን ካንሰር ወይም የብልት ላይ ኪንታሮትን ሊያስከትሉ ይችላሉ።
አንቶኒ "የኤችፒቪ ቫይረስን ከማህፀን ካንሰር ጋር በተያያዘ ሰምቼው አውቅ ነበር። በተለይም በወንዶች ላይ እንደዚህ አይነት ካንሰር ሊያስከትል እንደሚችል አላውቅም ነበር" ብሏል።
ይህ ጽሑፍ አንዳንዶችን ሊረብሽ የሚችል ምስል ይዟል
አንቶኒ አክሎም "አሁን መብላትና ማውራት በመቻሌ እድለኛ እንደሆንኩ እቆጥረዋለሁ፤ ነገር ግን ብዙ ዘግይቼ ቢሆን ኖሮ ምላሴን ላጣ ወይም ልሞት እችል ነበር።"
በኤችፒቪ የተያዙ አብዛኛዎቹ ሰዎች ቫይረሱን ከሰውነታቸው እንደሚያስወግዱ የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት አስታውቋል።
ነገር ግን የብልት ኪንታሮት ሊያስከትል ወይም ወደ ካንሰር ሊለወጥ ይችላል። በአብዛኛው በወንዶች ላይ የጭንቅላትና የአንገት በሴቶች ላይ ደግሞ የማህፀን በር ካንሰርን ያስከትላል።
ብሔራዊ የጤና አገልግሎቱ ዕድሜያቸው 12 እና 13 ዓመት ዕድሜ ለሞላቸው ታዳጊዎች እና ለኤችፒቪ ከፍተኛ ተጋላጭነት ላላቸው ሰዎች ክትባት እንዲሰጥ ይመከራል።
"እብጠት መኖሩን ካወቅክ፤ ባይጎዳም እንኳ ምርመራ አድርጉ" ሲል ይመክራል።
"ይህ ዓይነቱ ካንሰር በተለይ በወንዶች ዘንድ በበቂ አልተወራም። ቀደም ብሎ የሚወሰድ እርምጃ በእርግጥ ሕይወትን ያድናል።" ብሏል።
ምንም ዓይነት ምልክቶች ባይታዩበትም እአአ በመጋቢት 2023 ያደረጋቸው የሲቲ ስካን፣ ባዮፕሲ እና ኤምአርአይ ምርመራዎች በሽታውን መኖሩን አረጋግጠዋል።
"በወቅቱ የሦስት ዓመት እና የስድስት ዓመት ልጅ ነበረኝ። የመጀመሪያ ሀሳቤ ስለ እኔ ሳይሆን ስለእነርሱ ነበር። ለእነርሱ በጣም ፈርቼ ነበር" ሲል የ41 ዓመቱ ጎልማሳ ተናግሯል።
አንቶኒ ከአንገቱ ላይ 44 እጢዎች (ሊምፍ ኖዶች) ተወግደዋል፤በምላሱ ግርጌ ላይ ያለው ዋናው ዕጢም በመጨረሻ በሮቦት እርዳታ በተካሄደ ቀዶ ሕክምና ተወግዶለታል።
"በጊዜ እንደደረሱበት ነግረውኛል" ብሏል።
"ከሊምፍ ኖዶች አንዱ ሊፈነዳ ተቃርቦ ነበር። ከዚህ በላይ ቢቆይ ኖሮ ሊሰራጭ ይችል ነበር።"
የራዲዮቴራፒ እና የኬሞቴራፒ ሕክምናው በጣም ከባድ ስለነበር አንቶኒ 22 ኪሎ ግራም እንዲቀንስ አድርጎታል።
ሁኔታውን ሲያስረዳ "ምራቄ ሁሉ ጠፋ" ብሏል።
"ሁሉም ነገር በአፌ ውስጥ ወደ ዱቄት እየተለወጠብኝ ስለተቸገርኩ መጠጣት እንኳን ከባድ ነበር።"
"በጣም ደካማ ስለነበርኩ በዊልቸር ነበር የምንቀሳቀሰው።"
አክሎም "በዊልቸር እየተገፋሁ ወደ ራዲዮቴራፒ ሕክምና መወሰዴ የአእምሮ ጤንነቴን መጉዳት ጀምሮ ነበር።"
"ግን ቤተሰቤ ይህንን ለማለፍ እንድችል ድጋፋቸውን ሰጡኝ፤ እናም 40ኛ የልደት በዓሌን ለማየት በሕይወት ለመኖር ፈለግሁ።"
ኤችፒቪ ምንድን ነው?
ኤችፒቪ በቆዳ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሲሆን ከ100 በላይ ዝርያዎች አሉት።
በመራቢያ አካላት አካባቢ በሚኖር የቆዳ ንክኪ፣ በሴት ብልት፣ በፊንጢጣ ወይም በአፍ ጋር በሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት እና የወሲብ ቁሳቁሶችን በመጋራት ሊተላለፍ ይችላል።
በዩናይትድ ኪንግደም ዌልስ የአገሪቱ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት የክትባት ፕሮግራም ያለው ሲሆን ዕድሜያቸው 12 እና 13 ዓመት ለሆኑ ታዳጊዎች ሲሰጥ በተሻለ ሁኔታ ይሰራል።
የዌልስ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ክትባቱ እአአ ከ2008 ጀምሮ በ20ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሴቶች ላይ የማኅጸን ካንሰር በሽታን በ90 በመቶ ቀንሷል ብሏል።
የጭንቅላት እና የአንገት ቀዶ ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ሳንዲፕ ቤሪ ወላጆች ልጆቻቸው ክትባቱን እንዲወስዱ እንዲያበረታቱ አሳስበዋል።
"የኤችፒቪ ክትባት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዓመታት ጥቅም ላይ ውሏል፤ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ ነው፤ እና በዌልስ ውስጥ ያለው ብሔራዊ የክትባት ፕሮግራም አካል ነው።"
"ወንዶችና ልጃገረዶች ጤናማ ሆነው እንዲቆዩ፣ ከኤችፒቪ ጋር የተያያዘ ካንሰርን ለመከላከል እና በአጠቃላይ የሕዝብ ጤናን ለማጠናከር ይረዳል።"
"ክትባቱ የሚሰጠው ለታዳጊዎች ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ የወሲብ ግንኙነት ከመጀመራቸው በፊት መሆን ስላለበት እና የበሽታ መከላከያ ሥርዓታቸው ጥሩ ምላሽ በሚሰጥበት ወቅት መሆን ስላለበት ነው።"