የጋዛ የሰላም ንግግር በቀጠለበት ሰዓት እስራኤል የሐማስ ጥቃት ሁለተኛ ዓመት መታሰቢያን አከበረች

የጋዛን ጦርነት ለመቋጨት በግብፅ ንግግር እየተካሄደ ባለበት ቀን በመላው አገሪቱ እስራኤላዊያን መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በሐማስ የተፈፀመውን ጥቃት ሁለተኛ ዓመት መታሰቢያ አክብረዋል።

በጥቃቱ 1,200 ሰዎች ሲገደሉ 251 ሰዎች ደግሞ ታግተው ወደ ጋዛ ተወስደዋል።

እስራኤል ለጥቃቱ በጋዛ በወሰደችው አፀፋዊ ወታደራዊ ዘመቻ ደግሞ ከ67 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የሐማስ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በሰጡት መግለጫ "በከባድ ሐዘን" ውስጥ እስራኤል "ተዓምራዊ መቋቋም" አሳይታለች ብለዋል።

"ደም የጠማቸው ጠላቶቻችን ክፉኛ መትተውናል፤ ነገር ግን አልሰበሩንም" ሲሉ ኔታኒያሁ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታግተው የተወሰዱ ዜጎችን ማስመለስ እና ሐማስን መደምሰስ እንዲሁም ጋዛ ከዚህ በኋላ ለእስራኤል ስጋት እንዳትሆን የያዙትን "ሁሉንም የጦርነቱን ግብ" ለማሳካትም ቃል ገብተዋል።

ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል ከሁለት ዓመት በፊት ያደረሰውን ጥቃት ያስታወሱት የመንግሥታቱ ድርጅት ፀሐፉ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ "የጨለማው ቀን ሽብር በሁላችንም አዕምሮ ውስጥ ለዘለዓለም ታትሟል" ብለዋል።

የእስራኤል መንግሥት ይፋዊ የመታሰቢያ በዓሉን ቀን በሚቀጥለው ሣምንት ለማክበር ቀን ቢቆርጥም ማክሰኞ ዕለት በመላው አገሪቱ የመታሰቢያ መርሃ-ግብሮች ተካሂደዋል።

በሐማስ ጥቃት የተገደሉ እስራኤላዊያን መታሰቢያ በቴል አቪቭ ተካሂዷል። በሟች ቤተሰቦች የተዘጋጀው መርሃ-ግብር በእስራኤል የቴሌቭዥን ጣቢያዎች የተላለፈ ሲሆን፤ ከሰዓታት ቀደም ብሎ ደግሞ በመላው አገሪቱ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተካሂዷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል እና ሐማስ የተደራዳሪዎች ቡድን በግብፅ የቀይ ባሕር ሪዞርት በሆነው ሻራም አል-ሼክ ለሁለተኛ ቀን ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

ስለ ድርድሩ በቅርበት የሚያውቁ አንድ የፍልስጤም ከፍተኛ ባለሥልጣን የመጀመሪያ ቀን የጠዋት ንግግሩ ያለ ተጨባጭ ውጤት መጠናቀቁን ገልፀው፤ እስራኤል ከጋዛ በምትወጣበት እና ከመጀመሪያው ዙር ስምምነት በኋላ እስራኤል ጥቃቷን እንደማትቀጥል ሐማስ መተማመኛ መጠየቅ ላይ አለመስማማት እንዳለ ጠቁመዋል።

ድርድሩ "ከባድ እና ገና ተጨባጭ ግኝት ያልተገኘበት" መሆኑን አክለው የተናገሩት ባለሥልጣኑ፤ አደራዳሪዎች በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ጠንክረው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ ተደራዳሪዎች ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጄሬድ ኩሽነር ረቡዕ ግብፅ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።

ሰኞ ዕለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለጋዜጠኞች "ስምምነት የመድረስ መልካም ዕድል አለን፤ እና የመጨረሻ ስምምነት ይሆናል" ብለዋል።

የሕዝብ አስተያየት መረጃ እንደሚያመለክተው 70 በመቶ እስራኤላዊያን በታጋቾች ለውጥ ጦርነቱ እንዲያበቃ ይፈልጋሉ።

ማክሰኞ ጠዋት በጋዛ ከተማ የተለያዩ ሰፈሮች እስራኤል አየር ጥቃት እና የከባድ መሳሪያ ድብደባ ማድረሷን እማኞች የተናገሩ ሲሆን፤ እስራኤል የአየር ድብደባዋን ቀጥላለች።