'በጋዛ ያለው መፈናቀል ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ያልታየ ነው'

ባለሙያዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት የጋዛ ሕዝብ "ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ባልታየና ባልተጠበቀ ሁኔታ" እየተፈናቀለ ይገኛል።

የጋዛ ነዋሪዎች ተፈናቅለው የሚሄዱበት ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ አያገኙም። ከአንድ ጊዜ በላይ ለመፈናቀልም ይገደዳሉ።

የሚፈናቀሉት እጅግ ጠባብ በሆነና በተጨናነቀ አካባቢ ውስጥ ነው። የግጭት፣ የግዳጅ መፈናቀልና የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት እንዲህ ያለ መፈናቀል የተለመደ አይደለም።

የተባበሩት መንግሥታት እንዳለው በሁለት ዓመቱ ጦርነት ከ2.1 ሚሊዮን የጋዛ ሕዝብ ከአሥሩ ዘጠኙ ተፈናቅለዋል። የጋዛ ድንበሮችም ተዘግተዋል።

እስራኤል የጋዛ ነዋሪዎች አንዳንድ አካባቢዎችን ለቀው እንዲወጡ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ትሰጣለች። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ይፈናቀላል።

እስራኤል ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ የምታሳስበው ሐማስ ላይ በሚሰነዘር ጥቃት ንጹኃን ዒላማ እንዳይሆኑ በሚል መሆኑን ትገልጻለች።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት በጋዛ በግዳጅ ማፈናቀል ይስተዋላል።

በአማካይ ጋዛ የሚኖሩ ቤተሰቦች ስድስት ጊዜ ተፈናቅለዋል። ዲኒሽ ሬፍዩጂ ካውንስል በ2024 ባወጣው መረጃ መሠረት 19 ጊዜ የተፈናቀሉ ቤተሰቦችም አሉ።

በቅርቡ እስራኤል እያደረሰች ባለው ጥቃት ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ለመፈናቀል ተገደዋል።

ሶሀ ሙስሌሕ ነርስ ስትሆን ሁለት ታዳጊ ልጆች አሏት። እንደ አብዛኞቹ የጋዛ ነዋሪዎች በጠባብ ቦታዎች ተፈናቅላ ለመኖር ተገዳለች።

እስራኤል በምታደርሰው ጥቃት መንደሮች ይፈራርሳሉ።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የአንትሮፖሎጂና የግዳጅ ማፈናቀል አጥኚ ፕ/ር ዳውን ቻቲ "በጋዛ ያለው መፈናቀል ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ያልታየ ነው። የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር ያሉበት ሁኔታም የከፋ ነው። በጋዛ ፍልስጤማውያን መሄጃ የላቸውም። ከአንድ አደገኛ ቦታ ወደ ሌላ አደገኛ ቦታ ይፈናቀላሉ" ይላሉ።

እስራኤል አጭር የጽሑፍ መልዕክት በመላክና በማኅበራዊ ሚዲያ የጋዛ ነዋሪዎች አንድን አካባቢ ለቀው እንዲወጡ ትነግራለች።

"ሰብአዊ ቀጠና" አለበት ወደምትለው አል-ማዋሲ ወደተባለ አካባቢ እንዲጓዙ እስራኤል ደጋግማ ብታሳስብም አካባቢውን በተደጋጋሚ ደብድባለች።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ የጋዛ ነዋሪዎችን ለመጠበቅ በሚል ከአንድ አካባቢ ለቀው እንዲወጡ መልዕክት ያስተላልፋል።

"ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ በተመረጡ ኮሪደሮች በኩል እንዲጓዙ ይደረጋል" ብሏል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር፤ ሐማስ "ከንጹኃን ጋር ይቀላቀላል" የሚል ሲሆን፤ ሰብአዊ እርዳታ የሚሰጥባቸውን አካባቢዎች ዒላማ ባያደርግም በአካባቢያቸው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሲኖር እርምጃ እንደሚወስድ ይገልጻል።

በአንዳንድ የጋዛ አከባቢዎች የሚገኙ ጊዜያዊ መጠለያዎችን የሳተላይት ምሥል በመመልከት እየደረሰ ያለውን መፈናቀል መረዳት ይቻላል።

ለምሳሌ አል-ማዋሲ አቅራቢያ ያለው ሐማድ ሲቲ የተባለው መንደር ግንቦት 2024 ላይ በድንኳን ተሞልቶ ነበር። 'ሰብአዊ ዞን' በሚልም ተለይቶ ነበር።

ሆኖም ሐምሌ ላይ ባዶ የነበረው አካባቢው በሰዎች ተሞልቷል።

እስራኤል ሁለት ጊዜ ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲወጡ አዛለች። በሁለቱም ጊዜ ድንኳኖች ቢነሱም ብዙም ሳይቆይ አካባቢው በሰዎች ተሞልቷል።

ሶሀ እና ቤተሰቧ በ2024 ወደ ዴይር አል-ባላሕ ሲጓዙ በሐማድ ሲቲ አቅራቢያ አልፈዋል።

"የምንጓዘው ራሳችንን ብቻ ይዘን ነው። እንደ አዲስ ሕይወት በየጊዜው እንጀምራለን" ትላለች።

ስምንት ጊዜ ሲፈናቀሉ በርካቶች አብረዋቸው ተፈናቅለዋል።

ወደ ካሀን ዩኑስ ከዚያም ወደ ደቡባዊው ራፋሕ ተፈናቅለዋል። ሆኖም እስራኤል በቦታው እግረኛ ጦር አሰማራች።

በነዋሪዎች መፈናቀል ምክንያት የጋዛ ከተሞች አንዴ ይጠባሉ፤ መልሰውም ይሰፋሉ።

በጦርነቱ መጀመሪያ አራት ወራት የጋዛ ሰርጥ ሁለት ሰሜናዊ ግዛቶች ከነዋሪዎች ሦስት እጅ አጥተዋል።

በ2024 የመጀመሪያዎቹ ወራት ራፋሕ ከጦርነቱ በፊት ከነበረው ሕዝብ አራት እጥፍ የሚሆኑ ሰዎች መጠለያ ሆናለች።

ኋላ ላይ ግን ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ እስራኤል አሳስባለች።

አሁን ላይ ራፋሕ በአብዛኛው ወድማለች። የሚኖሩትም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው።

አብዛኞቹ ነዋሪዎች ወደ ካሀን ዩኑስ እና ዴይር አል-ባላህ ሄደዋል።

በኢየሩሳሌም ሒብሩ ዩኒቨርስቲ የሆሎኮስት አጥኚ ፕ/ር ዳንኤል ባልትማን እንደሚሉት፤ በጋዛ ያለው መፈናቀል ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ይለያል።

"ለዚህም ምክንያቱ ተፈናቃዮች መፈናፈኛ ማጣታቸው፣ በተደጋጋሚ መፈናቀላቸውና ያሉበት ሁኔታ የከፋ መሆኑ ነው" ይላሉ።

በዩኒቨርስቲው የዓለም አቀፍ ሕግ መምህር ዩቫል ሻኒ እንደሚሉት፤ የጋዛ ንጹኃን ነዋሪዎች ግጭት ያሉባቸውን አካባቢዎች ባጠቃላይ ጥለው መውጣት አልቻሉም።

እስራኤልና ሐማስ "በኦፕሬሽናቸው የንጹኃንን ሕይወት ለአደጋ አጋልጠዋል" ይላሉ።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤልና ግብፅ ድንበሮቻቸውን እንዲከፍቱ ጫና ማሳደር አለመቻሉን ይተቻሉ።

በዩኒቨርስቲ ኦፍ ፍሎሪዳ የሆሎካስት አጥኚው ኖርማን ጄደብሊው ጎዳ "እንዲህ ያለው የግዳጅ መፈናቀል ያሳዝናል" ይላሉ።

"እስራኤል ሐማስ የያዛቸው ቦታዎች ላይ ጥቃት ስታደርስ ማስጠንቀቂያ ካልሰጠች ንጹኃን አብረው ይጎዳሉ" ይላሉ።

በግጭት ውስጥ ያሉ ሁሉም አካላት የሚስማሙባቸው 'ደኅንነታቸው የተጠበቁ ቦታዎች' ሊኖሩ እንደሚገባ ይገልጻሉ።

እስራኤል በአል-ማዋሲ ባዘጋጀችው ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ ሐማስ "ኦፕሬሽኖቹን ቀጥሏል" ሲሉም ይናገራሉ።

ባለፉት ጥቂት ወራት ከ80 በመቶ በላይ የሆነው የጋዛ ሰርጥ አካባቢ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር የዋለ ወይም ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ የተሰጠበት ነው።

ቁጥሩ ያለፈው ሐምሌ ላይ 88 በመቶ መድረሱን ተመድ አስታውቋል።

የጋዛ ነዋሪዎች ተፈናቅለው የሚኖሩባቸው አካባቢዎች እጅግ የተጨናነቁ ናቸው። 9 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 5 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው አካባቢ ላይ ይኖራሉ።

እነዚህ አካባቢዎች በፍርስራሸ የተሞሉ መሆናውቸውን ተመድ ይገልጻል። ይህም በበለጠ የዜጎችን እንቅስቃሴ ያግዳል።

በድንኳን ውስጥ የሚኖሩ የጋዛ ነዋሪዎች በነፍስ ወከፍ ያላቸው ቦታ ግማሽ ስኩዌር ሜትር ይሆናል። ይህ ማለት 4 ሜትር በ5 ሜትር በሆነ ቦታ ውስጥ 40 ሰዎች ይኖራሉ ማለት ነው።

የጋራ ማብሰያ፣ ውሃ ማከፋፈያ እና ክሊኒኮች ቢኖሩም ከተፈናቃዩች ቁጥር ጋር አይመጣጠኑም።

ተመድ እንደሚለው እስራኤል ወደ ጋዛ ምግብና እርዳታ እንዳይገባ "በስልታዊ መንገድ ታስቆማለች"።

ፍልስጤማውያን አሁን ያለውን ሁኔታ ከናቅባ ጋር ያነጻጽሩታል። ናቅባ ከ1948 እስከ 1949 በነበረው ጦርነት 750,000 ፍልስጤማውያን የተፈናቀሉበት ነበር።

በዩናይትድ ኪንግደም የፍልስጤም ልዑካን ኃላፊ ሑሳም ዞምሎት "በ1948 ምን እንደተከሰተ እናውቃለን። የእስራኤል ወታደሮች በግዳጅ ነዋሪዎችን ካፈናቀሉ በኋላ መመለስ ቀላል አይሆንም። አሁን እየሆነ ያለው እንደ ናቅባ ዓይነት ነው" ይላሉ።

"እስራኤላውያን የቀረውን ጋዛ እያወደሙ ነው። የተፈናቀሉ የጋዛ ነዋሪዎች መመለሻ የላቸውም። የጋዛ ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉ የሚደረገው ስልታዊ በሆነ መንገድ ነው" ሲሉም ያክላሉ።