ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ የጋዛ ሰላም ንግግር በአፋጣኝ እንዲጀምር ለአደራዳሪዎች ጥሪ አቀረቡ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጋዛን ጦርነት ማስቆም ጥረት ላይ እየተሳተፉ ያሉ ሁሉም በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በግብፅ የሚደረገውን ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር እንዲያፋጥኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ንግግሩ ሐማስ ታጋቾችን መልቀቅ እና የጋዛን አስተዳደር ለምሑራን (ቴክኖክራት) መስጠትን ጨምሮ በትራምፕ ባለ 20 ነጥብ የሰላም ስምምነት ዕቅድ ላይ ከተስማማ በኋላ የሚደረግ ሲሆን፤ ቡድኑ በሌሎችም ጉዳዮች ላይም የመነጋገር ፍላጎት አለው።
ትጥቅ መፍታት እና በመጪው የጋዛ መንግሥት ላይ ምንም ተሳትፎ እንደማይኖረው የሰላም ዕቅዱ ቁልፍ ክፍል ላይ ቡድኑ ምላሽ አልሰጠም።
በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ንግግሩ "በጣም ውጤታማ" ነበር ያሉት ትራምፕ፤ "የመጀመሪያው ምዕራፍ በዚህ ሳምንት እንደሚጠናቀቅ ተነግሮኛል። እና ሁሉንም የምጠይቀው እንዲያፋጥኑት ነው" ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አክለውም፤ "ጊዜው በጣም አንገብጋቢ ነው ወይም ደም መፋሰስ ይቀጥላል" ብለዋል።
ትራምፕ ለጋዜጠኞች ታጋቾች በቅርቡ መለቀቅ ይጀምራሉ ብለው እንደሚያስቡ ገልፀዋል።
ትራምፕ የሰላም ዕቅዳቸው ማሻሻያ ይደረግበት ከሆነ ተጠይቀው፤ "ማሻሻያ አያስፈልገንም፤ ምክንያቱም ሁሉም ተስማምቶበታል፤ ይሁን እንጂ ሁሌም አንዳንድ ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ" ብለዋል።
"ለእስራኤል ትልቅ ስምምነት ነው፤ ለአረቡ ዓለም፤ ለሙስሊሙ ዓለም እና ለዓለም ትልቅ ስምምነት ነው። ስለዚህ በጣም ደስተኞች ነን" በማለት አክለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሐማስ ለዕቅዱ አዎንታዊ ምላሽ ከሰጠ በኋላ ትራምፕ "የቦንብ ድብደባው በአስቸኳይ እንዲቆም" ቢናገሩም እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን የአየር ድብደባ ቀጥላለች።
የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ ሾሽ ቤድሮሲያን እሁድ ዕለት ለጋዜጠኞች "በጋዛ ሰርጥ አንዳንድ ድብደባዎች ቢቆሙም፤ በዚህ ሰዓት እየተተገበረ ያለ የተኩስ አቁም የለም" ብለዋል።
በጋዛ ያሉ ጋዜጠኞች የእስራኤል የአየር ጥቃት መቀጠሉን እና እሁድ እና ምሽቱን ሙሉ በከተማዋ በርካታ የመኖሪያ ሕንፃዎችን ያወደመ የታንክ ጥቃት እንደነበረ ተናግረዋል።
በጋዛ የቢቢሲ ወኪል ዘጋቢ እሁድ ጠዋት በጋዛ ከተማ ውስጥ የፍንዳታ ድምፆችን መስማቱን እና በእስራኤል ድንበር አቅራቢያ ጭስ መመልከቱን ገልጿል።
በጋዛ የሚመራው ጤና ሚኒስቴር ባለፉት 24 ሰዓታት በእስራኤል ጦር ጥቃት 65 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማርኮ ሩቢዮ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ድብደባው መቆም አለበት ብለዋል።
"የቦምብ ድብደባ እየተፈፀመ ታጋቾችን ማስለቀቅ አትችልም። ይህ መቆም አለበት፤ ነገር ግን ሌሎች ጉዳዮችም መፈታት አለባቸው" ሲሉ ገልፀዋል።
"ታጋቾች በታቸለ ፍጥነት እንዲለቀቁ እንፈልጋለን" ሲሉም አክለዋል።
ባለ 20 ነጥቡ የሰላም ዕቅድ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም እና በመቶዎች ፍልስጤማውያን ምትክ 48ቱ ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚጠይቅ ነው።