ሐማስ ለጋዛ የሰላም ዕቅድ ምላሽ ከሰጠ በኋላ የታጋቾች ቤተሰቦች ተስፋና ፍርሃት

በጋዛ የቤተሰቦቻቸው አባላት በሐማስ የታገቱባቸው ሰዎች የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱ እንዲያበቃ ያቀረቡት የሰላም ዕቅድ የሚወዷቸውን ወደ ቤታቸው ይመልሳል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ናምሮድ የተባለው ልጇ ከ20ዎቹ በሕይወት አሉ ከተባሉ ታጋቾች መካከል እንደሚገኝ የምታምነው ቪኪ ኮሀን ቅዳሜ ከእንቅልፏ ስትነቃ "በተስፋ እና በመጠበቅ" መካከል ሆና እንደነበር ትናገራለች።

ቪኪ ተስፋዋ "የሆነ ነገር ቢፈጠርስ በሚል ፍርሃት" የታጀበ ነው።

"አስተማማኝ ነገር የለም፤ አንዲሁም ዳግም ቅር መሰኘት አንፈልግም። ደግሞ ናምሮድን በቅርቡ አየዋለሁ፤ አቅፈዋለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።"

የ21 ዓመቱ ናምሮድ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በሐማስ ሲታገት የ19 ዓመት ወታደር ነበር።

በዚያን ዕለት ሐማስ 1,200 ሰዎችን ሲገድል በአጠቃላይ 251 ሰዎችን አግቷል።

አርብ ዕለት በሕይወት ያሉትንም ሆነ የሞቱትን ሁሉንም ታጋቾች ለመልቀቅ የተስማማው ሐማስ፤ አሜሪካ ባቀረበችው የሰላም ዕቅድ ላይ በተወሰኑ ጉዳዮች ተጨማሪ ድርድር እንደሚፈልግ ተናግሯል።

ሐማስ ምላሹን ካሳወቀ በኋላ ትራምፕ በትሩዝ የማኅበራዊ ትስስር ድረ ገጻቸው ላይ "መጨረሻ ላለው ሰላም ዝግጁ ናቸው ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ" በማለት እስራኤል "አሁኑኑ ጋዛን መደብደብ ታቁም፤ ኪዘያም ታጋቾቹ ደህንነታቸው ተጠብቆ እና በፍጥነት ማግኘት አንችላለን" ብለዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንኣሚን ኔታንያሁ ምሽቱን በሰጡት ምላሽ ደግሞ እስራኤል "ሁሉም ታጋቾች እንዲለቀቁ ትራምፕ ያስቀመጡትን የመጀመርያውን ዙር ዕቅድ አሁኑኑ ለመተግበር እየተዘጋጀን ነው" ብለዋል።

በሐማስ እና በእስራኤል መካከል በመጪዎቹ ቀናት በግብጽ ድርድሩ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።

ቅዳሜ ምሽት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቴል አቪቭ የጦርነት ማብቂያ ይሆናል ተብሎ የተገመተውን የትራምፕን የሰላም ስምምነት ዕቅድ በመደገፍ አደባባይ ወጥተዋል።

አደባባይ የወጡት እስራኤላውያን "ብቻችሁን አይደላችሁም፤ አብረናችሁ ነን" እያሉ መፈክር ሲያሰሙ የነበረ ሲሆን የታጋቾች ቤተሰቦች ደግሞ የወዳጅ ዘመዶቻቸውን በሰላም መመለስ ጠይቀዋል።

ማታን የተባለ ልጃቸው የታገተባቸው ኢያናቭ ዛንጓከር "ኔታንያሁ፤ የምንወዳቸውን እና ተስፋችንን አትውሰድብን" ሲሉ በማይክራፎኑ በመጮህ ንግግር አድርገዋል።

"ለአንተ ታጋቾች ብቻ ናቸው፤ ለእኔ ግን ልጄ ነው። ሕይወቴ ነው። ታጋቾቹ የዚህች አገር የልብ ምት ናቸው" ብለዋል።

ሊራን በርማን ደግሞ የወንድሞቹን ጋሊ እና ዚቭ መለቀቅ ጠይቋል።

"ተስፋ ሲመጣ ፍርሃት አዝሎ ነው። ስምምነቱ ይፈረም ይሆን? ወንድሞቼን ዳግም አያቸው ይሆን?"

"ሌላ ስምምነት እንዲጨናገፍ አንፈቅድም። ዳግመኛ በጭራሽ አይደረግም. . .አሁን ወይንም መቼም ነው መርሃችን" ሲል አክሏል።

ከኖቫል ፌስቲቫል ላይ ታግቶ የነበረው እና የተለቀቀው ኦማር ሼም ቶቭ "ወደ ቤታቸው መልሷቸው" የሚል መፈክር በማሰማት አደባባይ የወጡ ሰዎችን ሲመራ ታይቷል።

ትራምፕ ያቀረቡት የሰላም ዕቅድ ተፈጻሚ እንዲሆን እንዲያስገድዱ ጠይቋል።

"ይህ ስምምነት ተግባራዊ መሆን አለበት።ሐማስ እንዲፈርመው ማድረግ አለብን። ሁለት ዓመት ሆነው። ዓለም እየተመለከተ ነው" ሲል ለተሰበሰበው ሕዝብ ንግግር አድርጓል።

የታጋቾች እና ከዚህ በፊት የተለቀቁ ቤተሰቦች አባላት በቴልአቪቭ ለተሰበሰበው ሠልፈኛ ንግግር ሲያደርጉ ኔታንያሁ ደግሞ በቴሌቪዥን ለሕዝባቸው ንግግር አድርገዋል።

በዚህ ንግግራቸውም "በመጪዎቹ ቀናት" የታጋቾቹ መለቀቅን ይፋ አደርጋለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

ቅዳሜ ማለዳ ላይ ታል ሐይሚ የተባለ የአጎቱ ልጅ የተገደለበት እና አስከሬኑን ማግኘት ያልቻለው ኡዲ ጎረን ስምምነቱ ይፈረማል ብሎ ተስፋ ያደርጋል።

"ፕሬዚዳንት ትራምፕ በቁርጠኝነት እየሰሩ እና ሁሉንም የአረብ አገራትን እና የእስራኤልን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ ከጀርባቸው ማሰለፋቸውን እያየን ነው" ብሏል።

"ለእስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያኖች መልካም ጊዜ እየመጣ መሆኑን እርግጠኛ መሆን አለብን። አሁን ጊዜው የድርጊት ነው፤ የወሬ አይደለም"።

ይህ የእርሱ ሃሳብ በሌሎች የታጋቾች ቤተሰቦችም ተስተጋብቷል።

የኢታን ሆርን ቤተሰብ በሰጠው መግለጫ "ከበርካታ ከባድ ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢታን እና ሌሎች 47 ታጋቾች [በሕይወት ያሉ እና የሌሉ] በመጨረሻም ሊለቀቁ ለመሆኑ ልባችን ማመን ደፍሯል። በቅርቡ ወደ ቤታቸው ይመጣሉ" ብለዋል።

አክለውም ይሁን እንጂ "ተስፋችን በትልቅ ፍርሃት የተሞላ ነው" ሲሉ ስጋቱን ገልፀዋል።

"እስኪመለሱ ድረስ በረሃብ፣ በስቃይ ውስጥ እና የሞት አደጋ የተጋረጠባቸው ናቸው።"

ጊል ዲክማን የተኩስ አቁም ስምምነቱን ዕድል ማጣት ምን ማለት እንደሆነ በደንብ እንደሚያውቅ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የአጎቱ ልጅ ካርሜል ጋር ከኪቡትዝ በሪ ታግታ የተወሰደች ሲሆን ከዓመት በኋላ አስከሬኗ በጋዛ ዋሻ ውስጥ ተገኝቷል።

የእስራኤል ጦር እንዳለው ወታደሮቹ ከመድረሳቸው በፊት ካርሜል ከአምስት ሌሎች ታጋቾች ጋር ተገድላለች።

"ትናንት የተመለከትነው ሐማስ መልስ መስጠቱን ነው። በትራምፕ ስምምነት የተወሰነ እንደተስማሙ እና የተወሰነ ደግሞ እንዳልተስማሙ፤ ነገር ግን ለእኔ ትልቁ ነገር ይህን ለመተግበር ፍላጎት ያላቸው መሆኑ ነው" ይላል።

"ከዚህ በፊት በርካታ ያልተጠቀምንባቸው እድሎች ነበሩ" ይሁን እንጂ ይህ "ሂደቱ በጣም በጣም ጠቃሚ ምዕራፍ ነው። . . .እናም ይህን ጦርነት ለመቋጨት እንድንቃረብ ያደርጋል"።