በጋዛ የሚገኙት የሐማስ ወታደራዊ አመራር የተኩስ አቁም ዕቅዱን ተቃወሙ

በሐማስ እና በእስራኤል መካከል የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ጥረት እያደረጉ የሚገኙት አደራዳሪዎች በጋዛ የሚገኙትን የሐማስ ወታደራዊ አመራር ማነጋገራቸውን እና አዲሱን የአሜሪካ የተኩስ አቁም ዕቅድ እንደማይቀበሉት መናገራቸውን ቢቢሲ ከምንጮቹ ሰምቷል።

በጋዛ የሚገኙት የሐማስ ወታደራዊ አመራር፣ኢዝ አል ዲን አል ሃዳድ፣ ዕቅዱ የሐማስን መጨረሻ ለማፋጠን የቀረበ ነው ብለው እንደሚያምኑ እና ቡድኑ ተቀበለውም አልተቀበለው ለመዋጋት ቁርጠኛ መሆናቸው ተነግሯል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡት 20 ነጥቦች ያሉት የጋዛ የሰላም ዕቅድን እስራኤል ተቀብላለች።

ዕቅዱ ሐማስ ትጥቁን እንዲፈታ እና በወደፊቷ ጋዛ ላይ ምንም ድርሻ እንደማይኖረው ያትታል።

በኳታር የሚገኙት የተወሰኑ የሐማስ የፖለቲካ አመራሮች ዕቅዱን ለመቀበል ፍላጎት ያሳዩ ቢሆንም ነገር ግን ቡድኑ ያገታቸው ግለሰቦች በእጃቸው ስለሌሉ ተጽዕኗቸው እምብዛም ነው ተብሏል።

48 ታጋቾች በሐማስ እጅ ያሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከልም 20ዎቹ በሕይወት መኖራቸው ይታመናል።

በሐማስ ውስጥ ላሉ አመራሮች ሌላው በዕቅዱ ለመስማማት አዳጋች ያደረገባቸው በተኩስ አቁሙ በተስማሙ 72 ሰዓታት ውስጥ ሁሉንም ታጋቾች እንዲያስረክቡ የሚለው የዕቅዱ ክፍል ነው።

ይህ የሚሆን ከሆነ ሐማስ የሚደራደርበት ምንም ነገር በእጁ ላይ አይቀርም።

ምንም እንኳ ትራምፕ እስራኤል ለዕቅዱ ተገዢ ትሆናለች የሚል ዋስትና ቢሰጡም በሐማስ በኩል ግን ታጋቾቹን ከተረከበች በኋላ ወታደራዊ ዘመቻዋን አጠናክራ ትቀጥላለች የሚል ጥርጣሬ አለ።

በተለይ ደግሞ በዶሃ የሐማስ አመራርን ለመግደል ያለ አሜሪካ ይሁንታ እርምጃ መውሰዷ ጥርጣሬው ከፍ እንዲል አድርጎታል።

ከአሜሪካ እና ከአረብ አገራት የተውጣጣ "ጊዜያዊ ዓለማቀፍ አረጋጊ ኃይል" በጋዛ ይሰማራል መባሉ የሐማስ አመራሮች ይህ ሌላ ዓይነት ወረራ ነው በማለት ተቃውመውታል።

በተጨማሪም የትራምፕ አስተዳደር የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሲወጣ ግዛቱን ከእስራኤል እና ከግብጽ ጋር በሚያዋስነው አካባቢ ሊኖር የሚችለውን "የደህንነት ቀጠና" የሚያሳይ ካርታ ይፋ ካደረገ በኋላ ጥርጣሬ ተፈጥሯል።

ይህ የደህንነት ቀጠና ማን እንደሚያስተዳድረው በግልጽ ያልተቀመጠ ቢሆንም እስራኤል የምትሳተፍበት ከሆነ ግን ለአለመግባባት መነሻ መሆኑ አይቀርም።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚነሲእትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሰኞ ዕለት በዕቅዱ ላይ መስማማታቸውን ቢገልፁም ከዚያ በኋላ ግን በርካታ የዕቅዱን ነጥቦች ወደ ጎን ያደረገ ንግግር አድርገዋል።

በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት የቪዲዮ መልዕክት ላይ የእስራኤል ጦር በጋዛ የተወሰነ ክፍል ውስጥ እንደሚቆይ እና አገራቸው፣ "በኃይልም ቢሆን" የፍልስጤም አገርነትን እንደምትቃወም ተናግረዋል።

ይህ በትራምፕ የሰላም ዕቅድ ላይ ከሰፈረው በተቃራኒው የቆመ ነው።

በዕቅዱ ላይ የተቀመጠው "ጋዛ ከማንኛውም የሽብር ጥቃት ደህንነቱ የተጠበቀ እስክትሆን ድረስ የደህነንት ቀጠናዎች ይኖራሉ" የሚል ሲሆን ሁለቱም ወገኖች የሰላም ዕቅዱን ከተቀበሉ የእስራኤል ጦር ሙሉ በሙሉ አካባቢውን ለቅቆ ይወጣል።

በተጨማሪም ዐቅዱ ሙሉ በሙሉ ከተጠናቀቀ "ፍልስጤማውያን በተጨባጭ ራሳቸውን የማስተዳደር እና አገር የመሆን ጥርጊያ መንገድ ይከፍታል" የሚል አንቀጽ ሰፍሯል።

ሐማስ ከዚህ በፊት ሉዓላዊት ፍልስጤም እስካልተመሰረተች ድረስ ጦሬን አልፈታም ማለቱ ይታወሳል።

መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ሐማስ ድንገተኛ ጥቃት በደቡባዊ እስራኤል ሰንዝሮ 1200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 ሰዎችን ካገተ ወዲህ እስራኤል የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍታለች።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ በእስራኤል መከላከያ በጋዛ በፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 66,225 ሰዎች መገደላቸውን የሐማስ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።